Thursday, April 3, 2014

ኢህአዲግ/ወያኔ ሕዝብ ለማፋጀት የገነባውን “የመርዝ ብልቃጥ”

ምርቃቱ የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ግጭት ከተጀመረበት 20ኛ ዓመት ጋር ገጥሟል
ኢትዮጵያን እየመራ የሚገኘው ኢህአዲግ/ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከቀን ወደ ቀን እርስ በርሱ እንዳይተማመን፣ እንዲነቃቀፍ፣ እንዲጠራጠር ከእዚህ ባለፈ ደግሞ ግጭት እንዲፈጠር እያደረገ 22 ዓመታትን ዘለቀ። ህዝቡ እለት ከእለት በገዢው መንግስት የሚወጠኑለትን የእርስ በርስ ማጋጫ ተንኮሎች እየተመለከተ ልቦናው በእጅጉ እየደማ ነው።
አንድ ወራሪ የውጭ ጠላት ሊሰራ የሚችለውን ያህል ህዝብን ከሕዝብ ጋር የማጋጨት ሥራ ኢህአዲግ/ወያኔ በትክክል ሰርቶበታል። የሃገሪቱን ፌድራል አስተዳደር በየትኛውም ዓለም ያልታየ ቋንቋን መሰረት ያደረገ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ደገሰላት። ፌድራላዊ አስተዳደር በዘመናዊው ዓለም አንዱ እና አማራጭ የአስተዳደር ዘይቤ ይሁን እንጂ በየትኛውም ሀገር መሰረት የሚያደርገው የመልክዓ ምድርን አቀማመጥ እና ታሪካዊ አሰፋፈርን ነው። እርግጥ ነው ጣልያን ሀገራችንን በወረረ ዘመን አሁን ወያኔ የሚጠቀምበትን የክልል አስተዳደር የመሰለ ቋንቋን መሰረት ያደረገ የአስተዳደር መዋቅር ዘርግቶ ነበር።
አንዳንዶች የአሁኑ ቋንቋን መሰረት ያደረገ አስተዳደር የብሔር ብሄረሰቦችን መብት ከማስከበር አንፃር የሚመስላቸው የዋሃን አይጠፉም። ግን ፈፅሞ አላማው ይህ ላለመሆኑ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል።እርግጥ ነው የህዝብ ባህል ማለትም ቋንቋው፣ አለባበሱ፣ ታሪኩ ወዘተ ሊጠበቅለት እና ከለላ ማግኘት አለበት። ይህ ከለላ በማግኘት መብት  ስም ወንጀል ሲሰራ፣ ቁርሾ በባትሪ እየተፈለገ ሲራገብ እና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ሲውል ነው ወንጀሉ።
ኢህአዲግ/ወያኔ ሕዝብ እርስ በርሱ በጎሳ ሲጋጭ መፍትሄ ለመፈለግ ከመነሳት ይልቅ ጉዳዩን ሲያባብስ እና ቤንዚን ስያርከፈክፍ ማየት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕለት ከዕለት የሚመለከተው ድራማ ሆኗል። ለእዚህም ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ለእዚህ ፅሁፍ ግን ሁለት ምሳሌዎችን እንጥቀስ -
  1. በዩንቨርስቲዎች ውስጥ ወጣቶች ‘አንተ የእገሌ ነህ አንተ የእንቶኔ ነህ’ ተባብለው ፀብ ሲነሳ ጉዳዩ የመጪው ትውልድ እና የአሁኑ ትውልድ አደገኛ አቅጣጫ ነው ብሎ የችግሩን ስር ለመፍታት ከመጣር እና የጉዳዩን አስከፊነት  በመገናኛ ብዙሃን ከመግለፅ እና ከማስተማር ይልቅ ፖሊስ ይልቁን ከአንድኛው ወገን ቆሞ ሌላውን ሲያስር እና ሲቀጣ መመልከት ዘግናኝ ተግባር ነው።
  2. ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት የእርሻ ቦታ ”የእገሌ ዘር ነህ” ተብሎ በክልል መስተዳድሮች ጭምር ሲባረር ለጉዳዩ እንደ መንግስትነት ለመዳኘት ሳይሆን የሚሞከረው እንደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ አባባል ”ቀድመው ባልተወለዱበት ሀገር መስፈር የለባቸውም” እንደ አቶ አለምነህ የብአዴን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደግሞ ”የትዕቢት ልጋግ” ነው የሚሉ መልሶችን መስማት እራስ ያማል። መሪዎቻችን እንዲህ እያሉ ከጉርዳፈርዳ እስከ አሶሳ፣ ከአሶሳ እስከ ሐረር፣ ከሐረር እስከ ጅጅጋ፣ ከጅጅጋ እስከ ቦረና ጉጂ፣ ድረስ በብዙ አስር ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በኢህአዲግ/ወያኔ የጎሳ ፖለቲካ ተሰደዱ፣ ተገደሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን መንግስት ጉዳዩን እንደ ትልቅ ችግር ሳይሆን እንደ አንድ የማስተዳደርያ ዘዴ እንደቆጠረው በ እርግጠኝነት መረዳት ይቻላል።
በያዝነው ሳምንት  በሃያ ሚልዮን ብር ወጪ የሚመረቀው የመርዝ ብልቃጥ 
በአርሲ ዞን በሂቶሳ ወረዳ ከሃያ ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሰራውን  ''አኖሌ ሐውልት'' እና ሙዝዬም
ኢህአዴግ በአርሲ ዞን በሂቶሳ ወረዳ ከሃያ ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሰራውን ”አኖሌ ሐውልት” እና ሙዝዬም
የእርስ በርስ ግጭቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገሩ የሚጥረው ኢህአዲግ/ ወያኔ ለእርስ በርስ ጦርነቶች እየመረጠ ሃውልት ሲሰራ ከርሞ በእዚህ ሳምንት ደግሞ ለየት ያለ የጥፋት ድግስ የሚሆን ከመቶ አመታት በፊት ለመፈፀሙ ምንም አይነት የታሪክ ማስረጃ የሌለው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በአርሲ ዞን በሂቶሳ ወረዳ ተፈፅሟል ያለውን የታሪክ ምሁራን ያላረጋገጡትን የፈጠራ ታሪክ ከሃያ ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሰራውን  ”አኖሌ ሐውልት” እና ሙዝዬም  በእዚህ በያዝነው ሳምንት እንደሚመረቅ ኢቲቪ ዛሬ መጋቢት 22/2006 ዓም የዜና እወጃው ላይ አስታወቀ። የፈጠራው ታሪክ ከመቶ ዓመታት በፊት የአፄ ምኒልክ ሰራዊት የኦሮሞ ሴቶችን ጡት ቆርጦ ነበር እና ማስታወሻነቱ ለተቆረጡት ጡት እና እጅ ይሁን” ይላል የሃውልቱ የመሰራት ምክንያትን ኦህዴድ /ኢህአዲግ/ወያኔ ሲናገር። አሳዛኝ የደረስንበት የዝቅጠት ዘመን። በየትኛውም ሀገር ውስጥ በቀደሙ መሪዎች ያውም ከመቶ አመታት በላይ ለሆነው ታሪክ ቀርቶ የቅርቦቹም ቢሆን ለተሰሩ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ለመጪው ትውልድ የሚያቆይ የእልቂት ድግስ ከፋች ሃውልት አይሰራም። የሚጠጣ ውሃ፣ የምበላው ምግብ ለሌለው ሕዝብከ 20 ሚልዮን ብር በላይ አውጥቶ መበተን ምን የሚሉት ፈልጥ ነው?
አንድ መንግስት ሕዝብ ከህዝብ ጋር አብሮ የሚኖርበትን ዘዴ ሲቀይስ ልዩነትን እያጎላ ሳይሆን አንድነትን እያሳየ እና እያጎላ ሕዝብ በፍቅር እና በስምምነት እንዲኖር ይጥራል እንጂ እንዴት ከአሁኑ ትውልድ አልፎ ለመጪው ትውልድ ቂም ለማውረስ ተግቶ ይሰራል? ይህ ተግባር ማንን ይጠቅማል? ለመሆኑ ያለፉ ነገስታት በወቅቱ በነበረው የቅጣት መንገዳቸው ሁሉ የቀጡትን የቅጣት አይነት እየዘረዘርን ሃውልት ብንሰራ የቱን ከየቱ እንመርጣለን?
የሃውልቱ ምርቃት እንደ ትልቅ የሀገር ልማት ዛሬ ኢቲቪ ቀድሞ ዛሬ ይናገረው እንጂ ወቅቱ የሩዋንዳው እልቂት የተጀመረበት 20ኛ አመት ጋር ገጥሟል። በሚያዝያ 7/1994 ዓም  እስከ ሐምሌ/1994 ዓም እ ኤ አቆጣጠር የቆየው በቱትሲዎች እና በሁቶዎች መካከል የተደረገው እልቂት ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ሕዝብ ሕይወት ቀጥፏል። የሩዋንዳው እልቂት በአንድ ሌሊት ድንገት የደረሰ ጉዳይ አይደለም። በሂደት አልፎ አልፎ በተነሱ ቁርሾዎች ጥርቅም ሳብያ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። የዛሬ የባለ ሃያ ሚልዮን ሃውልት ገንቢዎችም ሆኑ አስገንቢዎች መዘንጋት የሌለባቸው  በሰሩት ሥራ ሁሉ የሚጠየቁበት ቀን እንደሚመጣ መጠራጠር አይገባም። የመርዝ ብልቃጡም ይሰበራል የፍርድ ቀኑም ይቆረጣል።
(ምንጭ: ጌታቸው በቀለ ጉዳያችን)
Link;-http://www.goolgule.com/inaguration-of-anole-waqo-monument/

የማለዳ ወግ… በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል… (ነብዩ ሲራክ)

April 3, 2014
ግፍ ከበዛበት ወህኒ የአክብሮት ስላምታየ ይድረሳችሁ! (ነብዩ ሲራክ፣ ከሳውዲ አረብያ ውህኒ ቤት)
Nebiyu Sirak
ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ
እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ለአፍታ ያህል እድሉን አግኝቸ ወህኒ የመውረዴን እውነታ ላስረዳችሁ ግድ አለኝ ። ዛሬ አስረግጨ የምነግራችሁ ወህኒ የመውረዴ ምክንያት ሚስጥር ግምሽ እድሜየን ህግና ስርአቷን አክበሬ የኖርኩባትን የሳውዲት አረቢያን ህግ ተላልፊ አይደለም ! የስደተኛው ጉዳይ ያገባኛል በሚል የማቀርበው መረጃ ቅበላየ የማይመቻቸው ፣ ያመማቸው ከተሴረውና እየተሴረ ካለው እገታ ጀርባ ስለመኖራቸው አልጠራጠርም ። … ዛሬ በዚህ ዙሪያ ብዙ አልልም!
አላወቁትም እንጅ ክፉዎች ጠቅመውኛል ፣ ያላየሁትን እንዳይ አድርገውኛል። መንገዱ የከፋ ቢሆንም በወሰዱኝ መንገድ ተመርቸ እሰማው የነበረውን የወገኖቸ የወህኒ የከፋ ኑሮና ህመም ፣ በተቆርቋሪ ጠያቂ ማጣት ፣ በፍትህ መነፈግ እይሆኑ ያሉትን ከመስማት ማየት ማመን ነውና በአካል ማየት ችያለሁ !
ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት በግፍ ለተደበደበው፣ ሁለት አይኑን ላጣውና “አይሆኑ ከሚሆን ቢሞት ይሻላል” ተብሎ የፎቶ መረጃው ሳይቀር በእጀ የገባውን ወጣት ምንዱብ የወህኒ ህይወትን ተጨባጭ ታሪክ ከአይን እማኞች ቃርሜያለሁ! እሱም ያለው ከታሰርኩበት የቅርብ ርቀት ነው ።… አትጠራጠሩ አገኘውም ይሆናል !
በዚህ የጭንቅ ሰአት ከእኔና ከቤተሰቦቸ ጎን ሆናችሁ አለኝታነታችሁን ለገለጻችሁልኝ ምስጋናየ ከፍ ያለ ነው ! ዛሬ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ አንገባም ። በመላ አለም የምትገኙ ወገኖቸ ያሳያችሁኝ ድጋፍና መቆርቆር ከጨለማው ቤት ደርሶኝ ጽናት አጎናጽፎኝ ሰንብቷል። ይህም በአረብ ሃገር ስደተኛ ዙሪያ ሳቀርነው ለነበረው መረጃ ያገኘሁት ክብርና ሞገስ ሆኖ መከራውን አስረስቶኛል: ) ምስጋናየ አይለያችሁ!
ወገኖቸ ወዳጆች ፣ ዛሬ ሰላም መሆኔን ብቻ ተረዱ ብየ እንጅ በሰፊው ስለሚሆነው አቅም በፈቀደ መጠን እናወራለን ! ዝምታው ከናፈቅኳቸው ልጆቸ ፣ ከቤተሰቦቸና ከእናንተ ጋር የሚያደርሰው መንገድ ውል እንዲይዝ የሚደረገው ሙከራ ውል እንዲይዝ የሚተጉ ወገኖችን ሂደት ላለማደናቀፍ ብቻ ለመረጋጋት ሲባል ብቻ ነው !
በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል ፣ በንጋቱ ጮራ ታግዘን የምናወጋው የማለዳ ወግ ናፍቆኛል: ) ይህን ለማድረግ የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ደግሞ ልቤ ብርቱ ነው …
ሰላም ለሁላችሁ !
ነቢዩ ሲራክ
ከአንዱ የሳውዲ ወህኒ ቤት
Link:-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11664/


ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! መጠላለፍ ወደየትኛው ገደል እየመራን ነው? (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

April 3, 2014
የአዲስ አበባን መኪናዎች በተለይም በጫት የሚሽከረከሩት ታክሲዎችን በማንኛውም መስቀልኛ መንገድ ላይ ለአምስት ደቂቃ ቆሞ የተመለከተ ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ‹እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም!› በሚል መመሪያ መኪናዎቹ ተቆላልፈው እንዲቆሙ ማድረግ ነው፤ እንደሚመስለኝ የአባቶቻችንን ዕዳ እየከፈልን ነው፤ ዱሮ በደጉ ዘመን ሁለት ኢትዮጵያውያን መስቀልኛ መንገድ ላይ ሲገናኙ አንተ-እለፍ አንተ-እለፍ እየተባባሉ የሰማዕታቱንና የቅዱሳኑን ስም እየጠሩ ይገባበዙ ነበር! ይህ ባህል በጠንካራ የሥልጣኔ ላጲስ ተደምስሶ ጠፍቶ በምትኩ እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም መንገዱን ሁሉ መቆላለፍ አዲስ የመጠላለፍ ባህል እየተተከለ ነው፤ የመጠላለፍ ባህል የሚታየው በባቡር መንገዶች ላይ ብቻ አይደለም፤ በብዙ ነገር መጠላለፍ ባህል እየሆነ ነው! የዚህ ዝንባሌ መጨረሻው አሸናፊ የሌለበት ሙሉ ጥፋት ነው።
Prof. Mesfin Woldemariam
Prof. Mesfin Woldemariam
በመንገዶች ላይ ጥቂት በጫት የሚነዱ መኪናዎች በመቶ የሚቆጠሩ መኪናዎች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ይችላሉ፤ ሲያደርጉም በየቀኑ እየታየ ነው፤ በማኅበረሰባዊና በፖሊቲካ ግንኙነትም አንድ ሰው የሚዘራው መርዝ የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅድለት ፍጥነት የማኅበረሰቡን አባላት ያዳርሳል፤ እንቆቅልሹ እንደሚለው ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! ማለት መርዝ፣ እሳት፣ ተላላፊ በሽታ በሕዝቡ ላይ ማሰራጨት ከአምስትና ከአሥር ዓመታት በኋላ ውጤቱ ምን እንደሚሆን መገመት አያቅትም።
ድብብቆሽ አይጠቅምም፤ሁለት ነገሮችን በግልጽ ማውጣት አለብን፤አንደኛ በአሜሪካና በአውሮፓ መሽጎ ፍርሃቱንና ሽቁጥቁጥነቱን ለመሸሸግ መርዙን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚረጨው ለምንድን ነው? አገዛዙ ይህንን የሚያደርግበት ምክንያት ግልጽ ነው፤ ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴ ነው፤ ከአገዛዙ ጋር በሚደረግ ትግል ከታች ሆነው ከሥልጣን ውጭ የሆኑ ዜጎች በሥልጣን ላይ ከተቀመጡት ጋር እየተቆራቆዙና እየተጋጩ ናቸው፤ ይህንን እኔ የላይና-የታች ግጭት (vertical conflict) የምለው ነው፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግ ጋር የሚደረገው ትግል ይህ ነው፤ ይህንን ለማክሸፍ ወያኔ/ኢሕአዴግ ትግሉን ከላይና-ታች አውጥቶ ወደጎን-ለጎን ግጭት (horizontal conflict) ሊለውጠው ይፈልጋል፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግም ውጭ በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት የደነዘዙ ሰዎችም ትግሉን ጎን-ለጎን ሊያደርጉት እየሞከሩ ናቸው።
የፖሊቲካ ትግልን የሚመሩ ሰዎች በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት ስሜት እየተሳቡ ትግሉን የላይና-የታችነቱን ጠብቀው በተደራቢነት የጎን-ለጎን ትግሉን ይጨምሩበታል፤ ይህ ሲሆን ሀሳብ፣ ጉልበትና ሀብት ይከፋፈላል፤ ይበታተናል፤ ወደዓላማ ለመድረስም ያስቸግራል፤ ወያኔ ወደመጨረሻው ላይ ኢሕአዴግ ብሎ የሰየመውን ቀፎ አስቲፈጥር ድረስ በስሙ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያነሣ ነገር አልነበረውም፤ ወያኔን ለድል ያበቃው የማታለያ ስሙ እንደሆነ በበኩሌ አልጠራጠርም፤ ከሃያ ሁለት ዓመታት የጎሣ ሥርዓት በኋላ ኢትዮጵያ ቆስላለች እንጂ አልሞተችም፤ የአሐዝ ማስረጃ ለማቅረብ ባልችልም በብዙ ጎሣዎች መሀከል ጋብቻ እንደዱሮው እየቀጠለ ነው፤ ይህንን የቆየ የዝምድና ሰንሰለት ለመበጠስ የሚጥሩም አሉ።
ኒው ዮርክ ተቀምጦ ትኩስ ውሻ (ሆት ዶግ!) እየበላ ለእስላም ኦሮሞዎች የመገዳደያ መመሪያ የሚሰጥ ሰው የመንፈስ ጤንነቱን እጠራጠራለሁ፤ ይህንን የኒው ዮርክ ቀረርቶ ተከትሎ ሌላ የመጠላለፍ አዋጅ ሰማን፤ ቴዎድሮስ ካሣሁን ለአጼ ምኒልክ ስለዘፈነ ከበዴሌ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለማስታወቂያ የገባው ውል ሥራ ላይ ከዋለ የበዴሌን ቢራ አንጠጣም ተባለና ማስታወቂያው ተሰረዘ ይመስለኛል፤ ማን እንዳሸነፈ ወደፊት ጊዜ ይነግረናል፤ አሁን ደግሞ ሌላ ማዘዣ ሰማሁ፤ ‹‹የስ›› በሚለው ውሀ ጠርሙስ ላይ እንስራ የተሸከመችው ኮረዳ መስቀል አድርጋ ነበር፤ ልጅቱ ከነመስቀልዋ የምትታይበትን ውሀ እስላሞች አንገዛም ስላሉ ነጋዴዎቹ መስቀሉን አወለቁባት! ይህንን ማዘዣ ላወጣው አክራሪ እስላም ወረባቦ ቅዳሜ ገበያ ሄዶ እንዲጎበኝ አሳስበዋለሁ፤ ዛሬ ተለውጦ እንደሆነ አላውቅም እንጂ እኔ ብዙ ጊዜ ተመላልሼ እንዳየሁት የወረባቦ ኮረዶች ሁሉ ትልልቅ መስቀል በአንገታቸው ላይ ይታይ ነበር፤ መስቀል የእምነት መግለጫ ይሆናል፤ አያጠራጥርም፤ ግን መስቀል ጌጥም ይሆናል! መስቀል የናዚ ምልክትም ሆኖ ነበር! ለማናቸውም የዚህ ዓይነቱን መጠላለፊያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገምዱ ሰዎች ዓላማቸው ማንንም ለመጥቀም ሳይሆን ፍቅርንና ሰላምን ለማደፍረስ ነው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ መሠረታዊ ትምህርት ክፉን በክፉ አትመልሱ ነውና ለተበጠሰው መስቀል አጸፋውን ለመመለስ ማሰብ አይገባም።
ከኒው ዮርክ የተሰማው ቀረርቶም ሆነ የመስቀል ማስወለቁ ጉዳይ የተከሰተበትን ጊዜ ልብ ልንለው ይገባል፤ እስላሞች ስለነጻነት የሚያደርጉት ንቅናቄ በጣም እየጋለ በመሄድ ላይ እያለ ክርስቲያኖችም የዜግነት ግዳጃቸው አድርገውት ድጋፋቸውን በሚሰጡበት ጊዜ ነበር፤ ይህ መሆኑ ጥርጣሬን ይጋብዛል፤ የገጠመውን የእስላሞችና የክርስቲያኖች ሰልፍ በማደፍረስ ወይም በመክፈል የሚጠቀም ማን ነው? የሚጎዳውስ ማን ነው? ሁሉም የትግል አጋፋሪዎች ለዚህ ጉዳይ የሚያስፈልገውን ክብደት ቢሰጡት ትግሉ በጎን-ለጎን እንዳይሄድና እንዳይዳከም ይረዳል፤ ከዚያም በላይ አክራሪነት የሚባለውና የሚያስከትለውም ሽብርተኛነት የሚመጣው እንዲህ እያለ ነው፤ እግዚአብሔር ከዚያ ያውጣን!
Link:-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11666/