Saturday, June 7, 2014

የደህንነት ኃይሎች በጋዜጣ አዙዋሪዎች ላይ እርምጃ መወሰድ ጀመሩ

June 5, 2014
(ነገረ-ኢትዮጵያ፣ ሰበር ዜና) – በቅርቡ ገዥው ፓርቲ የግሉን ሚዲያ ለማፈን እንዲያስችል ጋዜጣ አዙዋሪዎችና አከፋፋዮችን በጥቃቅንና አነስተኛ ለማደራጀት የሚያስችል አሰራር እንደጀመረ ታውቋል፡፡ በዚህ አሰራር መሰረት ገዥው ፓርቲን የሚተቹ ጋዜጦችና መጽሄቶች ከገበያ በማስወጣት በቀጣዩ ምርጫ የሚደርስበትን ጫና ለመቀነስ እንደፈለገም ሲነገር ቆይቷል፡፡
ይህ በአዙዋሪዎች ላይ ሊወሰድ የታቀደው እርምጃ ዛሬ አመሻሹ ላይ የጀመረ ሲሆን በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ጋዜጣ አዙዋሪዎች በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች ታግተው አምሽተዋል፡፡ በእገታው ወቅት የደህንነት ኃይሎች ‹‹ለማዞር የተደራጃችሁበትንና ፈቃድ የተሰጣችሁበትን ወረቀት አምጡ›› በማለት ወደ ጣቢያ ሊወስዱዋቸው እንደነበርና አዙዋሪዎቹም ‹‹መደራጀት አይጠበቅብንም፣ ጣቢያም አንሄድም›› ብለው የደህንነቶቹን ትዕዛዝ መቃወማቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም መንግስት የሚተቹትን ጋዜጦችና መጽሄቶች እንዲያዞሩ እንደማይፈልግና እሱ በሚፈልገው እያደራጀ መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ እርምጃው መጠነ ሰፊ መሆኑን የጠቆሙት ታጋቾቹ ‹‹መንግስት ይህንን ለመተግበርም በእኛ ብቻ ሳይሆን ጋዜጣ በምናስነብብባቸው ካፌዎች ላይም ጫና ተጀምሯል፡፡ ካፌዎቹ ለአንድ ሰው ከአንድ ጋዜጣ በላይ እንዳንሰጥና አንዳንዶቹም ጭራሹን እንዳናስነብብና እንዳንሸጥ እየከለከሉን ነው፡፡›› ያሉት አዙዋሪዎቹ እስካሁን ይወሰዳል የተባለው እርምጃ ዛሬ በግልጽ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
Reading newspapers in Addis Ababa, Ethiopia

Friday, May 16, 2014

ዝክር ለግንቦት 7 1997 እና ለግንቦት 7 ቀን 2000 ዓ.ም

May 16, 2014
ዘንድሮ፣ የታሪካዊው ግንቦት 7 ቀን 1997 አገር ዓቀፍ ምርጫ ዘጠነኛ ዓመት እና ንቅናቄዓችን የተመሠረተበት ስድስተኛ ዓመት የምንዘክረው ከመችውም በላይ አገራችን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሁና ነው። ወያኔ የማይገዛትን አገር እንዳትኖር ለማድረግ እማትወጣው አረንቋ ውስጥ ከመክተት የማይመለስ ኃይል መሆኑን ዛሬ በአምቦ፣ በጉደር፣ በጊምቢ እና መሰል ቦታዎች በተግባር እያስመሰከረ ነው።
Ginbot 7 logo
የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ፍላጎቱን የመግለጽ አንፃራዊ ነፃነት አግኝቶ የነበረበት የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ምርጫን ስናስብ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ መመዘናችን አይቀርም። ያኔ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እጁ መዳፍ ቀርባ ትታየው የነበረችው ድል እስከዛሬ አልጨበጣትም። ትግሉ ግን ቀጥሏል። የዛሬው ትግላችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከያኔው በበለጠ ከታሪክና ከራስዋ ጋር የታረቀች አገር የመመሥረትን ርዕይ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት መስጠትን የሚጠይቅ ሆኗል።
ወያኔ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለአለፉት አርባ ዓመታት ሲያብላላው የቆየው፤ በመንግሥት ሥልጣን በቆየባቸው ሃያ ሶስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በፓሊሲ ደረጃ ሲያስፈጽመው የቆየውን የዘር ፓለቲካ አስከፊ ውጤት አሁን እየታየ ነው። ይህ የዘር ፓለቲካ ራሱ ወያኔን ያጠፋዋል። ችግሩ ግን የዘር ፓለቲካ ወያኔን ነጥሎ አያጠፋም፤ ከወያኔ ጋር አገራችንንም ሊያጠፋ ይችላል። ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ የዘር ፓለቲካ የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። በጎረቤት አገራት ውስጥ ያየነውን ዓይነት የእርስ በርስ እልቂት ወደ አገራችን ለማምጣት ህወሓትና ኦህዴድ ተግተው እየሠሩ ነው። ሌሎች የወያኔ ተቀጥላ ድርጅቶችም የዚህ ትልቅ የጥፋት ፕሮጀክት አካል ናቸው።
የግንቦት 7 1997ቱ ብሩህ ተስፋ በፋሺስቱ ወያኔ የግፍ አፈና ሲጨልም፤ ያ ተስፋ እንዲያንሠራራ በግንቦት 7 2000 ዓ.ም. የተቋቋመው ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዛሬ የኢትዮጵያን ተስፋ ለማጨለም ከተነሱ ኃይሎች በተፃራሪ በመቆም የሕዝብና የአገር አለኝታነቱ ማረጋገጥ ይኖርበታል።