በኬንያና በዚምባብዌ የታሠሩ ኢትዮጵያውያን ይከሰሳሉ ተባለ
በህገወጥ መንገድ ወደ ኬንያና ወደ ዚምባብዌ ድንበር ሲያቋርጡ ተይዘው የታሰሩ መቶ ያህል ኢትዮጵያውያን ክስ ይጠብቃቸዋል ተባለ፡፡
ሰሞኑን ወደ ናይሮቢ ሊገቡ ሲሉ በፖሊስ የተያዙት ሀምሳ ሶስት ወጣት ኢትዮጵያውያን ህጋዊ ፓስፖርት እንደሌላቸውና ከአማርኛ ውጪ በእንግሊዝኛ መግባባት እንደማይችሉ የሳምራ ፖሊስ ኮማንደር ኤል ሙታሚያ ተናግረዋል፡፡ ከስደተኞቹ ጋር፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚያካሂዱ ደላሎች ናቸው የተባሉ ኬንያዊያንም ታስረዋል፡፡
በሌላ በኩል የዚምባቡዌን ድንበር አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊሄዱ የነበሩ ሰላሳ ስምንት ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ ፖሊስ ተይዘዋል፡፡ ወጣት ስደተኞቹ ወደ ዙምባብዌ የገቡት በህገወጥ መንገድ ስለሆነ ክስ ይመሰረትባቸዋል ሲል ፖሊስ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ በኬንያና በዙምባቡዌ ለታሰሩ ስደተኞች ከመንግስት እገዛ ይደረግላቸው እንደሆነ ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው፣ “መንግስት ሁልጊዜም ዜጐቹን የመርዳት ፍላጐት አለው፤ በየአገሩ ያሉ ኤምባሲዎቻችንም በዚህ ፖሊሲ መሰረት እየሰሩ ነው” ብለዋል፡፡
በቅርቡ የወጣው የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚለው በየአመቱ ከሀያሺ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያዊያን በኬንያ በኩል ደቡብ አፍሪካ ይገባሉ፡፡ (አዲስ አድማስ)
አውራምባ ታይምስ አገሯ ገባች
ኢህአዴግ ለህይወቴ ያሰጋኛል በሚል አሜሪካን አገር ከላላ አግኝቶ የነበረው የአውራምባ ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ አቶ ዳዊት ከበደ አገሩ መግባቱ ተገለጸ። ዳዊት በ1997 ምርጫ ወቅት ከታሰሩት ጋዜጠኞች ጋር እስር ቤት ነበር። ከሌሎች የሙያ ባልደረቦቹ ጋር ከእስር ሲፈታ ሌሎች በሙያቸው ለመስራት ጠይቀው ፈቃድ ሲከለከሉ ዳዊት ግን ዳግም የጋዜጣ ፈቃድ ማግኘት ችሎ ነበር። ከእስር መልስ ከሁለት ዓመት በፊት ከዳዊት ጋር ኢህአዴግን በመሸሽ የተሰደደችውን አውራአምባ ታይምስን ወረቀት አልባ በሆነ መልኩ አቋቁሞ የነበረው ዳዊት ወደ አገር ቤት ለመመለሱ የሰጠው ምክንያት የዲያስፖራው ጽንፈኛ አስተሳሰብና መወቀስን አለመውደድ አንደሆነ አስታውቋል። ጋዜጠኛነት አሸባሪነት በሆነባት ኢትዮጵያ ዳዊት ሥራው ያለው እዚያ ነው ቢልም “ዳያስፖራውን በጥብጦ ሲያበቃ ተልዕኮውን አሳክቶ ተመለሰ” ብለውታል፡፡ በስፋት የተቃውሞ አስተያየት የሚሰነዝሩበት ክፍሎች ግን “ስለከሸፈበት አገሩ ተመልሶ ኢህአዴግን ተቀላቀለ፤ አድዋ ገባ” ብለውታል።
ኢዴፓ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እውቅና ጠየቀ
በገዥው ፓርቲ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢዴፓ ባካሄደው ግምገማ፣ ኢሕአዴግ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለና እያጠናከረ ከመሄድ ይልቅ፣ ይበልጥ እየተዳከመ እንዲመጣ ማድረጉን ገልጿል፡፡ ገዢው ፓርቲ ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከር ምንም ዓይነት ተጨባጭ ዕርምጃ እየወሰደ እንዳልሆነና ይህም በአገሪቱ የጽንፈኝነት ፖለቲካና አክራሪነት የበለጠ እየተጠናከረ እንዲመጣ አድርጓል ይላል የኢዴፓ ግምገማ፡፡
“በአሁኑ ወቅት በአገራችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሙስና፣ የፖለቲካ ጽንፈኝነትና አክራሪነት ለዘለቄታው ዕድገት ብሎም ለሰላምና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት በመሆን፣ አገራዊ አደጋ እየሆነ መጥቷል፤” ይላል ኢዴፓ ገዢው ፓርቲን በገመገመበት ወቅት የደረሰበትን ድምዳሜ ሲገልጽ፡፡
ኢዴፓ በጉባዔው ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ተችቷል፡፡ ተቃዋሚዎች የኢዴፓን የተቃዋሚነት ሚናና ህልውና የካዱና፣ በሕዝቡ ዘንድ በበጎ መንፈስ እንዳይታይ ሆን ብለው ሴረኛ አሉባልታዊ ዘመቻ የሚያካሂዱ መሆናቸውን መገንዘቡን ገልጿል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የወቅቱ ትግል ተጠናክሮ ለድል እንዳይበቃ ዋነኛ እንቅፋት መሆናቸውን ገልጾ ሕዝቡ የእነዚህን ተቃዋሚ ኃይሎች ትክክለኛ ማንነት እንዲገነዘብ ጠይቋል፡፡
በመቀጠልም ተቋዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ቆም ብለው መመርመርና ካለፈው ስህተታቸው መማር ካልቻሉ በስተቀር፣ በትብብር ለመሥራት ሙከራ እንደማያደርግና ከዚህ ተግባራቸው ተላቀው ዕውቅና እንዲሰጡት ኢዴፓ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ የጠቅላላ ጉባዔውን አቋም ከገለጸ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ማብራርያ ሰጥቷል፡፡ ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል ከፀደቀ ጊዜ ጀምሮ መነጋገሪያነቱ ያልቀዘቀዘው የፀረ ሽብርተኝነት ጉዳይ ላይ ኢዴፓ ያለውን አቋም እንዲገልጽ የቀረበው አንዱ ነው፡፡የፓርቲው አዲሱ ፕሬዝዳንት አቶ ጫኔ ከበደ እንደገለጹት፣ ኢዴፓ የፀረ ሽብር ሕጉን ይደግፋል፡፡ ሥልጣን ቢይዝ የፀረ ሽብር ሕጉ እንደሚያስፈልገው አቶ ከበደ ገልጸው፣ ነገር ግን መሻሻል ያለባቸው ነጥቦች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
መሻሻል ካለባቸው ነጥቦች መካከልም ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ ይዘት ያላቸው ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ነጥቦች ሕጉ አቅጣጫውን እንዲስት ማድረጋቸው አቶ ጫኔ ገልጸዋል፡፡ለዚህም ማሳያው ጋዜጠኞችና መብታቸውን የሚጠይቁ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡ (ሪፖርተር)
አየር ሃይል አዲስ አዛዥ ተመደበለት
የአቶ መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ ለስልሳ ከፍተኛ መኮንኖች የጀነራልነት ሹመት ያደለው ኢህአዴግ በመከላከያና በደህንነት ተቋማቱ ሃላፊዎች ዙሪያ ሹም ሽር እንደሚያደርግ በተለያዩ መንገዶች ሲገለጽ መሰንበቱ ይታወቃል። በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የአንድ ብሄርና የህወሃት አባላት ብቻ አመራሩን መያዛቸው ቅሬታ መፍጠሩም በስፋት እየተነገረ ይገኛል።
ይህንን ተከትሎ ኢህአዴግ የጀነራሎች አዲስ ሹም ሽር ማካሄዱን አዲስ አድማስ ምንጮቹን ገልጾ አስታወቀ። ጋዜጣው እንደጠቆመው የአየር ሃይል አዛዥ በመሆን ሜጀር ጀነራል አደም መሀመድ ተሹመዋል። በቀድሞው የአየር ሃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሞላ ሀይለማርያም ምትክ የተሾሙት ጀነራል አደም የአየር ሀይል ፓይለት የነበሩና በሱዳን አቢዬ ግዛት የሠላም አስከባሪ ሀይል ምክትል አዛዥነት ያገለገሉ፣ እንዲሁም የመከላከያ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ እንደነበሩ ጋዜጣው አመልክቷል።
በሌሎች የመከላከያ የስራ ምድብ ቦታዎች ላይ የአዛዦች የምደባ ለውጥ ተደርጓል። አዲስ የሀላፊነት ምደባ ከተሠጣቸው ውስጥ ሌተናል ጀነራል ሠአረ መኮንን፣ ሌተናል ጀነራል አበባው፣ ሜጀር ጀነራል ዮሀንስ ወልደጊዮርጊስ፣ ሜጀር ጀነራል ገብራት አየለ እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ያስታወቀው አዲስ አድማስ የሃላፊዎቹን የሹመት ምድብ ቦታ አላስታወቅም።
በርሊን፤ የሜርክል የእጅ ስልክና አሜሪካ
የጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል የእጅ ስልክ በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የስለላ ተቋም ተጠልፏል የሚለዉ ዜና እያነጋገረ ነዉ። ዩናይትድ ስቴትስ ድርጊቱን እንዳልፈፀመች በመጥቀስ አስተባብላለች። ጉዳዩ በአውሮጳ መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ጀርመን የመራሂተ መንግስቷ ስልክ ሳይሰለል አይቀርም በሚል በበርሊን የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደርን ዛሬ ለማነጋገር መጥራቷ ተዘገበ። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ በጀርመን ለአሜሪካኑ አምባሳደር ጆን ኤመርሰን በዚህ ረገድ የጀርመንን ግልጽ አቋም እንደሚያቀርቡም ተገልጿል። የጀርመን መገናኛ ብዙሃን የአሜሪካን የስለላ ተቋም NSA የመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን የእጅ ስልክ ሳይጠለፍ አልቀረም የሚል መረጃ ይፋ አድርገዋል። ዋሽንግተን ግን አስተባብላለች። ይህ ከተሰማ በኋላም ሜርክል ራሳቸዉ ለፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ስልክ በመደወል የተባለዉ እዉነት ከሆነ ፍፁም ተቀባይነት የለዉም ማለታቸዉን ቃል አቀባያቸዉ ሽቴፈን ዛይበርት ገልጸዋል። የመከላከያ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዚየር በበኩላቸዉ፤ “የሰማነዉ እዉነት መሆኑ ከተረጋገጠ በጣም መጥፎ ነዉ። አሜሪካዉያን እዉነተኛ ጓደኞቻችን ነበሩ አሁንም ናቸዉ፤ ሆኖም እንዲህ ሊቀጥል አይችልም።”
ኋይትሃዉስ ኦባማ ትናንት ከሜርክል ጋር ባደረጉት የስልክ ዉይይት የአሜሪካን የስለላ ተቋም እሳቸዉን እንደማይሰልል ማረጋገጣቸዉን ቢገልጽም ከዚህ ቀደም ስለመደረጉ ያለዉ የለም። የኋይት ሃዉስ ቃል አቀባይ ኤይ ካርኔ፤
“እኔ ልገልጽ የምንችለዉ ፕሬዝደንቱ ዩናይትድ ስቴትስ መራሂተ መንግስቷን በወቅቱ እንደማትሰልል፤ ወደፊትም እንደማትሰልል እንዳረጋገጡላቸዉ ነዉ። ዩናይትድ ስቴትስ ከጀርመን ጋ ሰፊ የጸጥታ ችግሮችን በተመለከተ ላለን የቀረበ ትብብር ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች።”
ስለሜርክል ሞባይል መጠለፍ የተሰማዉ የNSA በቀድሞዉ ባልደረባ ኤድዋርድ ስኖዉደን ጉዳዩን አጋልጦ በርካቶች መራሂተ መንግስቷ ነገሩን ያደባብሳሉ የሚል ጥርጣሬ እየተሰነዘረ ባለበት ወቅት ነዉ። የስልካቸዉ መጠለፍ ያስቆጣቸዉ ሜርክል በሳምንቱ መጀመሪያ ከ70 ሚሊዮን በላይ የስልክና ኢሜል ልዉዉጦች መጠለፋቸዉ ካናደዳት ፈረንሳይ መሪ ፍራንስዋ ኦሎንድ ጋ በጉዳዩ ላይ ዛሬ እንደሚነጋገሩ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ከብራስልስ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ብራስልስ ላይ የተሰባሰቡት የአዉሮፓ ኅብረት አባል መንግስታት መሪዎች የግለሰብ ዜጎችም ሆነ የመሪዎች የግል ጉዳይ ላይ የሚደረግ ስለላ ተቀባይነት እንደማይኖረዉ አመልክተዋል። የፈረንሳይ የዜና ወኪል የኅብረቱ የፍትህ ኮሚሽነር ቪቫነ ሬዲንግ ቃል አቀባይ ኮሚሽነሯ መረጃን የመከላከል ርምጃ የአንጌላ ሜርክል የእጅ ስልክንም ሆነ የግለሰብ ዜጎችን የኢሜል ልዉዉጥ ላይ በእኩልነት ተግባራዊ ልሆን ማለታቸዉን ዘግቧል። ኮሚሽነሯ የኅብረቱ ጉባኤ ማብራሪያ የሚጠይቅበር ሳይሆን ርምጃ የሚወስድበት ጊዜ አሁን ነዉ ማለታቸዉም ተጠቅሷል። ከወራት በፊት ለአዉሮፓ የመረጃ መከላከል ህግ እንዲጸድቅ ቀርቦ 28 አባል መንግስታት በጉዳዩ ልዩነት ስለነበራቸዉ ታግዷል። የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽነር ሆሴ ማኑዌል ባሮሶም በበኩላቸዉ አዉሮጳዉያን የግለሰብን የግል ጉዳይ ማክበርን እንደመሠረታዊ መብት ይመለከቱታል ነዉ ያሉት። የኅብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ዛሬ እና ነገ የኤኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ጉባኤ ለማካሄድ የተሰባሰቡ ሲሆን የጀርመን መራሂተ መንግስት ስልክን የመጠለፍ ወሬ ትኩረታቸዉን ወደሌላ ሳይስብ እንዳልቀረ እየተነገረ ነዉ። (ከጀርመን ሬዲዮ የተወሰደ)
ሶስት የአማራ ክልል አመራሮች ታገቱ
የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ በአማራ ክልል ላኩማ ወረዳ ሁለት የሚሊሽያ ሀላፊዎችንና አንድ የወረዳ አስተዳዳሪን በቁጥጥር ስራ ማገቱን ኢሳት ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ ም አስታወቀ።
ንቅናቄው ቀደም ሲል 22 የፖለቲካ አመራሮች በላኩማ ወረዳ በሚገኘው በሰላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በስብሰባ ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ መልቀቁን ገልጾ፣ ሶስቱን አመራሮች ግን አሁንም ድረስ በቁጥጥር ስር አድርጎ እንደሚገኝ
ኢሳት አመልክቷል። የተያዙት አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት ፓለቲከኞች ዋነኛ እና የአካባቢውን ህብረተሰብ በመበደል የሚታወቁ እንደሆነ ንቅናቄው አመልክቷል፡፡
አቶ አልዩ ጋሹ የላኩማ ወረዳ አስተዳደር ስብሳቢ፣ አቶ አንበሱ በዙ የሰገላ ወረዳ ሚሊሺያ ዘርፍ ሀላፊ፣ እንዲሁም አቶ ኢያና ካሳ የባምበል ወረዳ ሚሊሽያ ዘርፍ ሀላፊ ሶስቱም በቁጥጥር ስር የሚገኙ ሀላፊዎች እንደሆኑ ንቅናቄው መግለጹኢነ ያመለከተው ኢሳት ዜናውን ከገለልተኛ አካል አለማረጋገጡን ጠቁሟል።
ላኩማ ወረዳ ብዙ የሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ያለባት ስፍራ እንደሆነች የገለጸው ንቅናቄው ከዚህ በፊት የአካባቢውን ሰዎች ሲያጉላላ የነበረ ሀላፊ እርምጃ ተወስዶበት እንደነበር አስታውሷል፡፡ ንቅናቄው በክልሉ ባሉ ህዝቦች ላይ የሚፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሰቃይ እንዲቆም መጠየቁንና የጎጃም ዞን ዋና የህወሀት ባለስልጣን በነበሩት አቶ ዳኘ ገብረማርያም ላይ በቅርቡ እርምጃ መወሰዱን መዘገቡን ኢሳት በዜናው አመልክቷል።
source: goolgule.com
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.