ለእውቁ የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ለኔልሰን ማንዴላ በርካታ የዓለም መሪዎች፤ ቤተሰቦቻቸው፤ ወዳጆቻቸው እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ከመላው ደቡብ አፍሪቃ የመጣ ህዝብ በተገኘበት ሶዌቶ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኝ ስታድዮም ዛሬ ይፋ ስንብት ተደረገ ። በቅርብ ጊዜ የዓለም ታሪክ በርካታ የሃገር መሪዎች በአንድ ላይ በተሰባሰቡበት በዚሁ ስነ ስርዓት ከተገኙት የዓለም መሪዎች መካከል የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ና የኩባው ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ ይገኙበታል ።3 የቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶች ጆርጅ W ቡሽ ፣ ቢል ክሊንተንና ጂሚ ካርተር እንዲሁም የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲቪድ ካምረን የቻይናው ምክትል ፕሬዝዳንት ሊ ዩዋንቻው የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙንም ነበሩ ። በስነ ስርዓቱ ላይ የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ መዝሙር በኳየርና በወታደራዊ የማርሽ ባንድ ተዘምሯል ። በስፍራው አርፈደው የደረሱትን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ና ባለቤታቸውን ምሸል ኦባማን በደስታ የተቀበለው ስታድዮም የተገኘው ህዝብ መሪው ጄኮብ ዙማ ሲመጡ ግን በማንጓጠጥ ጩኽት አሰምቷል ። ስነ ስርዓቱ በአንድ ሰዓት ዘግይቶ ነበር የተጀመረው ። ለወቅቱ ያልተለመደ ብርድ በነበረበትና ከባዱ ዝናብ እየጣለ በተካሄደው የስንብት ስነስርዓት ላይ የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአፍሪቃውያን ባህል በአንድ ሰው ቀብር ላይ ዝናብ ሲጥል አምላክ በደስታ ይቀበለዋል ፤ የመንግሥት ሰማያት በሮችም ይከፈታሉ እንደሚባል ተናግረዋል ። ማንዴላ ጥቁሮችና ነጮች በመካከላቸው እርቅ እእንዲወርድ ይቅር እንዲባባሉና ጥላቻን እንዲቀብሩ ዘረኝነትን እንዲያስወግዱ ያሳመኑ ሃገሪቱም ልዩ ልዩ ባህሎች ዘሮችና ሃይማኖች በአንድ ላይ የሚኖሩባት ሃገር እንድትሆን ያበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ኦባማ በበኩላቸው በታሪክ ትልቁን ስፍራ የሚይዙ ካሏቸው ከማንዴላ ተግባር ሰዎች ዓለምን እንዴት መለወጥ እንደሚችሉ መነሳሳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል ።
« በታሪክ ገጾች ብቻ ሳይሆን በህይወታችን በየዕለቱና ውሎ ምን ማድረግ እንደሚቻል አሳይተውናል ።