Tuesday, December 10, 2013

የታላቁ የሰላም አባት የማንዴላ ስንብት በሶዌቶ




ለእውቁ የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ለኔልሰን ማንዴላ በርካታ የዓለም መሪዎች፤ ቤተሰቦቻቸው፤ ወዳጆቻቸው እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ከመላው ደቡብ አፍሪቃ የመጣ ህዝብ በተገኘበት ሶዌቶ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኝ ስታድዮም ዛሬ ይፋ ስንብት ተደረገ ። በቅርብ ጊዜ የዓለም ታሪክ በርካታ የሃገር መሪዎች በአንድ ላይ በተሰባሰቡበት በዚሁ ስነ ስርዓት ከተገኙት የዓለም መሪዎች መካከል የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ና የኩባው ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ ይገኙበታል ።3 የቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶች ጆርጅ W ቡሽ ፣ ቢል ክሊንተንና ጂሚ ካርተር እንዲሁም የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲቪድ ካምረን የቻይናው ምክትል ፕሬዝዳንት ሊ ዩዋንቻው የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙንም ነበሩ ። በስነ ስርዓቱ ላይ የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ መዝሙር በኳየርና በወታደራዊ የማርሽ ባንድ ተዘምሯል ። በስፍራው አርፈደው የደረሱትን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ና ባለቤታቸውን ምሸል ኦባማን በደስታ የተቀበለው ስታድዮም የተገኘው ህዝብ መሪው ጄኮብ ዙማ ሲመጡ ግን በማንጓጠጥ ጩኽት አሰምቷል ። ስነ ስርዓቱ በአንድ ሰዓት ዘግይቶ ነበር የተጀመረው ። ለወቅቱ ያልተለመደ ብርድ በነበረበትና ከባዱ ዝናብ እየጣለ በተካሄደው የስንብት ስነስርዓት ላይ የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአፍሪቃውያን ባህል በአንድ ሰው ቀብር ላይ ዝናብ ሲጥል አምላክ በደስታ ይቀበለዋል ፤ የመንግሥት ሰማያት በሮችም ይከፈታሉ እንደሚባል ተናግረዋል ። ማንዴላ ጥቁሮችና ነጮች በመካከላቸው እርቅ እእንዲወርድ ይቅር እንዲባባሉና ጥላቻን እንዲቀብሩ ዘረኝነትን እንዲያስወግዱ ያሳመኑ ሃገሪቱም ልዩ ልዩ ባህሎች ዘሮችና ሃይማኖች በአንድ ላይ የሚኖሩባት ሃገር እንድትሆን ያበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ኦባማ በበኩላቸው በታሪክ ትልቁን ስፍራ የሚይዙ ካሏቸው ከማንዴላ ተግባር ሰዎች ዓለምን እንዴት መለወጥ እንደሚችሉ መነሳሳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል ።
« በታሪክ ገጾች ብቻ ሳይሆን በህይወታችን በየዕለቱና ውሎ ምን ማድረግ እንደሚቻል አሳይተውናል ።

የተመድ ዋና ፀሃፊ ባንኪሙ ማንዴላን የዓለማችን ታላቅ መምህር ና ለነፃነት ለእኩልነትና ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ መስዋዕትነት የከፈሉ ናቸው ብለዋል ።
« ማንዴላ ከፍተኛ መስዋዕትነት ነው የከፈሉት ። ለነፃነት ለእኩልነት ዴሞክራሲና ፍትህ ምንኛውንም መስዋዕትነት ለመከፍለ በየዕለቱ ዝግጁ ነበሩ ።»
ኔልሰን ማንዴላ ረዥም ጊዜ ከወሰደ ህመም በኋላ ባለፈው ሀሙስ ነበር ጆሃንስበርግ ውስጥ በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ያረፉት ። የኖቤል የሰላም ተሸላሚው ማንዴላ ባለትዳርና በህይወት ያሉ የሶስት ሴቶች ልጆች የ18 የልጅ ልጆችና የ12 የልጅ ልጅ ልጆች አባት ነበሩ ። አስከሬናቸው በዋና ከተማይቱ ፕሬቶሪያ ከነገ ረቡዕ እስከ አርብ ድረስ ለህዝብ ስንብት በክብር እንዲቀመጥ ከተደረገ በኋላ ምሥራቅ ኬፕታውን በሚገኘው በትውልድ መንደራቸው በኩኑ መንደር እንደሚቀበሩ ተዘግቧል ። በቀብሩ ስነስርዓት ላይ 5 ሺህ ያህል ህዝብ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ።

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.