Thursday, March 13, 2014

አባ መላ እና መላ ያጣው ንግግራቸው

March 12, 2014
በዳጉ ኢትዮጵያ
አቶ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) በቅርቡ ስላደረጉት የአቋም ለውጥ ለቢንያም ከበደ (ቤን) የሰጡትን ቃለ መጠይቅ አነበብኩት፡፡ ላልተጠበቀው የ180 ዲግሪ የአቋም ለውጥ በመንስኤነት ከጥቅመኛ ፖለቲከኝነት እስከ የጠበቁትን አለማግኘት በርካታ ምክንያቶች እየተጠቀሱ በብዙዎች ትንታኔ እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ እኔ በዚህ ረገድ ምንም ለማለት አልፈልግም፡፡ ይልቁንስ በቃለ ምልልሳቸው ኢሳትን በተመለከተ በሰነዘሯቸው አንዳንድ የተሳሳቱ ነጥቦች ላይ ጥቂት ብል እመርጣለሁ፡፡ የትኩረት ነጥቦቼን በተናጠል ተራ በተራ እዘረዝራለሁ፡፡
ESAT interview with Aba Mela (activist)
“ምንም አይነት የዜና ምንጭ የሌላቸው”
አቶ ብርሃኑ ስለኢሳት ከተናገሯቸው ነጥቦች የመጀመሪያው “ኢሳት ምንም አይነት የዜና ምንጭ የለውም” የሚል ነው፡፡ እውነት ለመናገር ራሳቸው አቶ ብርሃኑም በዚህ ንግግራቸው የሚያምኑበት ከሆነ አስቂኝ ነው፡፡ እንዴ አቶ ብርሐኑ፡- መቼም የጠቅላይ ሚኒስትርዎትን ሞት ቀድመው የሰሙት ከኢቲቪ አልያም ከፋና አይደለም፡፡ የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነውን አስፀያፊ ንግግር ከዝግ የካድሬዎች ስብሰባ ላይ ቀድቶ አየር ላይ ያዋለው የሰሞኑን ወዳጅዎ (መቼም እርስዎ በዚህ ተለዋዋጭ አቋምዎ ዘላቂ ወዳጅ አይኖርዎትም ብዬ ነው) አቶ ቢንያም አይመስለኝም፡፡ ኸረ ስንቱ ስንቱ… ከጉራ ፋርዳ የአማራ ተወላጆች መፈናቀል እስከ የኦህዴድ ውስጣዊ ህንፍሽፍሽ… ኢሳት ይህን ሁሉ ከህዝብ ተደብቆ የነበረ መረጃ አደባባይ ያወጣው ያለአንዳች የመረጃ ምንጭ ነው ካሉን በአመክኒዮ ሳይሆን በስሜት እንደሚነዱ በራስዎ ላይ እየመሰከሩ ነው፡፡

“የዜና ምንጫቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው”
ይህ ነጥብ ደግሞ አስቂኝነቱ ያመዝናል፡፡ ኢሳት የኢቲቪን ዜና “ትዊስት እያደረገ የመጀመሪያውን መጨረሻ የመጨረሻውን መጀመሪያ” አድርጎ የሚያቀርብ ከሆነ አራተኛው የኢቲቪ ቻናል ሆነ ማለት ነው፡፡ የኢቲቪን ዜና ዳግም የሚያሰራጭ (Rebroadcast) ጣቢያ ከሆነ ደግሞ እኔን ጨምሮ በሚሊዮን የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን አማራጭ የመረጃ ምንጭ ባላደረግነው ነበር፡፡ ለምን ቢሉ ኢቲቪን ዲሽ መትከል ሳያስፈልገን፤ አንዱ የስርጭት ሞገድ ሲዘጋ በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠር ብር ከእለት ጉርሳችን ነጥቀን ለዲሽ አስተካካዮች ሳንከፍል መከታተል እንችላለን፡፡ እውነቱን ለመናገር የኢሳት የተሰሚነት ሚስጥር እርስዎ ከተናገሩት ተቃራኒው ነው፡፡ ከአሰልቺውና ከእውነት ከተጣላው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮፖጋንዳ የሚያስጥል አማራጭ አድርጎ ኢሳት ራሱን ማቅረቡ ነው የተሰሚነቱ ምክንያት፡፡ እስኪ ለዛሬ ለእውነት ታማኝ ለመሆን ይሞክሩና የኢቲቪንና የኢሳትን የዜና ፕሮግራሞች ይከታተሉ፡፡ ኢቲቪ የሐረር የውኃ ችግር እንደተቃለለ “አንዳንድ ነዋሪዎችን” እማኝ አድርጎ ሲዘግብልዎት ኢሳት ግን በህዝቡ አዕምሮ ውስጥ የሚብሰለሰለውን የሐረር የግንብ መደዳ ሱቆች ቃጠሎ ክስተት ተጎጂዎቹን እያነጋገረ ያስደምጥዎታል፡፡ እርስዎ በሐረር ከተማ ቢኖሩ አሊያም በከተማው ውስጥ የሚኖር አንዳች የቅርብ ዘመድ ካለዎት  የኢቲቪን “ሐረር ሠላም ነው ምንም አልተፈጠረም” የዘወርዋራ ፕሮፖጋንዳ ለመስማት የሚያስችልዎት አንዳች ፍላጎት ይኖርዎ ይሆን?
“ተአማኝነት የሌለው”
በቅርቡ የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የአቶ አለምነውን ስድብ-አዘል ንግግርና የፓርቲያቸውን የዝምታ ስምምነት በመቃወም በባህር ዳር ከተማ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት ደማቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሒዶ ነበር፡፡ ሠልፈኞቹ ለተቃውሞ የወጡበትን የአቶ አለምነውን ንግግር የሰሙት በሌላ በማንም ሚዲያ ሳይሆን በኢሳት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ500 ኪ.ሜ ርቀት የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኢሳት የሰሙትን መረጃ አምነው ለተቃውሞ የባህር ዳር ከተማን ጎዳናዎች አጥለቅልቀዋል፡፡ ተአማኝነት ማለት እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ማለት ይሆን?
“ኢሳት ከግንቦት ሰባት ውጪ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን አያስተናግድም”
አቶ ብርሐኑና እኔ የምንሰማው ሁለት የተለያዩ ኢሳቶችን ካልሆነ በቀር በየእለቱ የኢሳት ፕሮግራሞች የአንድነት፣ የሠማያዊ፣ የአረና ወዘተ እንቅስቃሴዎችና መግለጫዎች ሰፊ ሽፋን የሚያገኙት በኢሳት ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኩት የባህር ዳር የአንድነት ፓርቲና የመኢአድ የተቃውሞ ሠልፍ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኘው በኢሳት ነበር፡፡ ኢቲቪማ በሠልፉ ተደናግጦ ስለሰልፉ አንዳች ቃል ሳይተነፍስ ይልቁንስ “መድረክ አንድነትን ከአባልነት ማገዱን” እያጋነነ ሲዘግብልን ነበር፡፡ “ተቃዋሚዎች ተከፋፈሉ” ነው መልዕክቱ፡፡ ሁለት ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (አንድነት ፓርቲና መኢአድ) በትብብር መሬት-አርዕድ የተቃውሞ ሠልፍ ማድረጋቸው ሳይሆን አንድ ፓርቲ ለጊዜው ከመድረክ መታገዱ ለገዢው ፓርቲ የሚጠቅም ዜና ስለሆነ ሽፋን ያገኛል- በኢቲቪ መስፈርት፡፡
“በኢሳት ከግንቦት ሰባት ውጪ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሽፋን አያገኙም” ለሚለው የአቶ ብርሐኑ አስተያየት ራሱ ገዢው ፓርቲ ከሳምንታት በፊት በሐገር ውስጥ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መሪዎች በኢሳት መግለጨ መስጠታቸው ህገወጥ ነው ሲል መክሰሱና አንድነትና ሠማያዊ ፓርቲም “ይህን ማድረግ መብታችን ነው”ሲሉ በጽኑ መቃወማቸው ጉልህ ማስተባበያ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ግንቦት ሰባት “ከኤርትራ በማገኘው ድጋፍም ጭምር ተጠቅሜ የአገዛዝ ስርዓቱን አወርዳለሁ” ሲል በሰጠው መግለጫ ላይ ጊዚያዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ተቃውሞ ማሰማቱን ከዋና ፀሐፊው አንደበት የሰማነው በዚሁ በኢሳት እንደነበት አቶ ብርሐኑ አይዘነጉትም ብዬ አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ የያዙትን የፖለቲካ አቋም በማናቸውም ምክንያት ትቶ የአቋም ለውጥ ማድረግ ሊከበርለት የሚገባ የማንም ሰው መብት ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ የተቀላቀሉት ካምፕን ደስ ለማሰኝትና ድርጎ ቢጤም ለማግኘት በማሰብ የባሰ ትዝብት ላይ የሚጥል ንግግር መናገሩ ፋይዳው ብዙም አይታየኝም፡፡ አገዛዙ እንደሆነ ደጋፊህ ነኝ ብሎ ለሚመጣለት (በተለይም ከተቃዋሚው ጎራ) ከህዝብ አንጡራ ሐብት ላይ ዘግኖ ላለመስጠት የሚያስችል አንጀት እንደሌለው የታወቀ ነውና አቶ ብርሐኑም ያሰቡትን ለማግኘት ብዙ መቀባጠር የሚኖርብዎት አይመስለኝም፡፡ አበቃሁ!
lINK;-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11385/
Posted by;.Bethel Solomon

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.