Saturday, March 15, 2014

አንድነት – የአማራውን ሕዝብ ክብር የደፈሩና ያዋረዱ አምባገነን ገዥዎች ለፍርድ ይቅረቡ!!!(መግለጫ)

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

«ጉድ ሳይሰማ…» እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በስርዓቱ እየተፈፀመበት ካለው ጭቆናና በደል፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ገፈፋ፤ አፈናና ስደት፤ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት በተጨማሪም በአምባገነን ገዥዎች እየተዋረደ፣ በአደባባይ እየተሰደበና ሰብዓዊ ክብሩ እየተጣሰ ይገኛል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖም ሀገራችን ላይ ያለው ስርዓት ህዝቡን የሚያዋርድ፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ስልጣኑን የሚያስቀድም፣ ለህዝብ ጆሮ የሚሰጥ አስተዋይ መሪ የሌለው ነው፡፡

ለዘመናት ያልተፈቱ ችግሮችና በመሪዎቹ የሚፈጠሩ ችግሮች ትከሻውን ያጎበጡት የኢትዮጵያ ህዝብም ስርዓቱን ከነችግሩ መሸከሙ አልበቃ ብሎ መሪ ነን በሚሉት እየተበሻቀጠና ለውርደት እየተዳረገ ይገኛል፡፡

ፓርቲያችን በትኩረት እየተከታተለው ያለውና ሰሞኑን የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይና በኢሳት ይፋ የተደረገው የአማራ ክልል ም/ ፕሬዘዳንትና የብአዴን ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን፣ የአማራውን ህዝብ በአደባባይ መሳደባቸውንና ማዋረዳቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች መለቀቃቸውና የክልሉ መንግስት ለማስተባበል እንኳ ዝግጁ አለመሆኑ የሚያሳየው ንቀትንና ጥላቻን ብቻ ሳይሆን እንመራዋለን የሚሉት ህዝብ ትከሻ ላይ ተቀምጠው ፀረ ህዝብ አቋም እንደሚያራምዱ ነው፡፡ ፓርቲያችን የብአዴን/ኢህአዴግ ባለስልጣን በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀሙትን ክብር የሚነካ አሳፋሪ ድርጊት በቸልታ ሊመለከተው እንደማይችል አስረግጦ ለመናገር ይወዳል፡፡ ፀረ ህዝብ አቋም የሚያራምዱ አምባገነኖችንም ከህዝብ ትክሻ ለማውረድ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡ አንድነት በቅርቡ በጉራ ፈርዳና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በዜጎች ላይ የተወሰደው የማፈናቀል ተግባር ስርዓቱና የስርዓቱ መሪዎች የፈጠሩት ችግር እንጅ የአካባቢው ሕዝብ የፈጠረው እንዳልሆነ ያምናል፡፡
አቶ አለምነው መኮንን የተባሉት ባለስልጣን የአለቆቻቸውን የዘወትር አባባል በማስረገጥ እመራዋለሁ የሚሉትን የአማራ ህዝብ «ሰንፋጭ የሆነ ትምክህተኝነት የተጠናወተው፣ ትምክህተኝነቱን ያልተወ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ መርዝ ንግግር የሚናገር ወዘተ» ካሉ በኋላ «የትምክህት ልጋጉን ማራገፍ አለበት» በማለት እንደሌሎች ብሄረሰቦች ሁሉ ለዚች ሀገር ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል ዋጋ የከፈለውን የአማራ ክልል ህዝብ ዋጋ በማሳጣትና የሌሎች ጠላት አድርጎ በማቅረብ የማጥላላት ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
ፓርቲያችንም ይህንን አሳፋሪና የዜጎችን ክብር የደፈረ የባለስልጣኑ አባባል በቸልታ የሚታይ ሆኖ አላገኘውም፡፡
ስለዚህ፡-

1. ግለሰቡ በዚህ የተዛባ አመለካከቱ ለአማራ ክልል ህዝብ መሪ ሊሆን ስለማይችል በአስቸኳይ ከፓርቲና ከመንግስት ኃላፊነቱ እንዲነሳና ለህዝቡ ይፋ እንዲደረግ፤
2. ህዝቡን ያዋረደው ባለስልጣን ላይ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ግን የግለሰቡ አመለካከት የብአዴንና የክልሉ መንግስት አቋም አድርገን የምንወስድ መሆኑ እንዲታወቅ፤
3. አንድነት ፓርቲ ፀረ-ህዝብ አቋም ያለው ግለሰብ ባደረገው የህዝብ ጥላቻ ንግግር (Hate speech) ተነስቶ ለሕግ የሚያቀርብ መሆኑ እንዲታወቅ፤
4. ፓርቲያችን ህዝቡን በማስተባበር በባህርዳር ከተማ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠራና ድርጊቱን የማውገዝና እንዲቆም የማድረግ ርምጃ የሚወስድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
ስለዚህ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የክልሉን ህዝብ እየመራው ያለው ብአዴን/ኢህአዴግ ለህዝብ ክብር የሌለው ድርጅት መሆኑን አውቆ ከፓቲያችን ጎን በመቆም እንዲታገለው ጥሪ እናቀርባለን፡፡


ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም
Link;_https://www.andinet.org/
Posted by Bethel Solomon

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.