Saturday, April 5, 2014

“ኧረ እኔስ ጨነቀኝ”

ሰውየው ያገባት ሚስቱ ቤተሰቦቿ ሃብታሞች ነበሩ። እሱ ደግሞ መናጢ የሚባል ደሃ ነበር። አንድ ቀን የማይቀረው ሞት የሚስቱን አባት ነጠቀና ቀብር ወጡ። አስከሬን እየተከተሉ ሲያለቅሱ ባል ሚስቱ ጎን ሆኖ ልክ እንደሷ “አባቴ አባቴ” በማለት ያለቅስ ጀመር። ሚስትም ” የት የወለደህን ነው አባቴ የምትለው” በማለት አፍታ ወስዳ ባሏን ገሰጸችው።
ባል ለቅሶውን ቀየረና “አባቷ፣ አባቷ …” በማለት ያስነካው ጀመር። ይህን ጊዜ ሚስት አሁንም ለቅሶዋን ቆም አድርጋ “የበላኸው ጨማ፣ የጠጣኸው ጠጅ አያንቅህም? አባቷ አባቷ የምትለው” አለችው። ባልም ደንግጦ ላፍታ ዝም በማለት ካሰበ በኋላ “አረ እኔስ ጨነቀኝ፣ አረ እኔስ ጨነቀኝ … ” በማለት እያለቀሰ የባለቤቱን አባት ሸኘ። ይህ አጠር ተደርጎ የቀረበ የቀድሞ ምሳሌ ነው።
ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ይወዳሉ። አገራቸውን በልጅ፣ በሚስት፣ በእናት፣ በአባት፣ በቤተሰብ … እየሰየሙ አንጎራጉረዋል። ተቀኝተዋል። ተደርሰዋል። ፎክረዋል። አቅራርተዋል። በዚህች አገራቸው ጉዳይ ለሚመጣ ማናቸውም ችግር “ቀልድ የለም” በማለት ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ተፋልመዋል። ወድቀዋል። ባንዲራቸውን ከፍ አድርገው ዘምረዋል።
በአንድ ወቅት ተፈጥሯል ተብሎ ከተመሰከረልን “የባንዳነት ገድል” ውጪ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ጠላት ሲመጣብን፣ ወራሪ ሃይል ሲያድምብን፣ አገራችንን ሊደፍሩ የሚቃጣቸው ሲነሱብን መተባበርና አንድ መሆን ልዩ ባህላችን ነው። የምንኮራበት ስጦታችንም ነው። ጠላትን ለመመከት በተደረገ ጥሪ በገዢዎቹ አኩርፎ “ወዲያ በሉ” የሚል ትውልድ አገራችን አላበቀለችም። ጠላትን ደቁሶና አሳፍሮ የሚመልስ ትውልድ እንጂ!!
ህወሃት እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብና አገር ወደ ጎን በማለት ከሻዕቢያ ጋር ፍቅር ተጣብቶ በቀልን በዘራበት ወቅት፣ ኢትዮጵያን የሚወዱ ዜጎችን በጠላትነት እየፈረጀ ሲወነጅል፣ የብሔር መርዝ እየዘራ አብሮ የኖረ ህዝብ ሲያጋጭ፣ አገርን ዘርፎ ለዘራፊ አሳልፎ ሲሰጥና የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም የህዝብ ሃብት ላይ ለጠቅላይ ሲጫወት፣ “ያገባናል” በማለት ለአገራቸው የሚከራከሩትን በጠራራ ጸሐይ ሲገል፣ ሲያስርና ሲያንገላታ ቆይቶ ራሱ በፈጠረው ችግር ህጻናትን በጀት ሲያስቆላ “ዞር በል” ያለው አልነበረም። ይልቁኑም ከዳር እስከዳር በመነሳት በባድመ ጦርነት ፈንጂ ላይ በመሮጥ አገርንና ህዝብን የሚያኮራ ገድል ለመፈጸም ተችሏል።
“ጦርነትን እንሰራዋለን” የሚሉት ህወሃቶች ግራ ሲገባቸው፣ እንደ ህወሃት ተግባርና ተንኮል ሳይሆን ለአገር ቅድሚያ በመስጠት ሻዕቢያን በመደቆስ ድል ከተቀዳጁ በኋላ ዳግም ክህደት ተፈጽሞባቸው ውሉ ባልታወቀ ጦርነት ወገኖቻችን አሁን ድረስ በጦር ሜዳ እሳት ዳር ተጥደው ይገኛሉ። ይህ የሚሆነው ህወሃት ሊንደው ሌት ተቀን የሚባትትበት የቀደመው የአገር ፍቅር የትብብር መንፈስ እንጂ ሌላ ኢህአዴግ የፈጠረው ውለታ ይዟቸው አይደለም። ይህ በጎ ታሪካችን ነው። አገር ወዳድ የሆንን በሙሉ እንኮራበታለን። እንመካበታለን።
በሌላ በኩል አስደንጋጭ ታሪክ አለን። ለመልካም ነገር የመተባበር ችግር አለብን። አገርን ለመታደግና በሰለጠነ መንገድ ልዩነትን የመቻቻል ጣጣ አለብን። በልዩነት ውስጥ ተባብሮ አገርን ወደ መልካም ጎዳና የማሸጋገር ራዕይና ፈቃደኛነት የለንም። የዛሬ አርባ ዓመት አካባቢ የግራው ፍልስፍና አራማጆች ነን በሚሉ የተሰበከው “በጠላቶቻችን መቃብር ላይ …” የሚል ለአንዱ ህልውና የሌላው መጥፋት ግዴታ እንደሆነ የታመነበት አስተሳሰብ እስካሁን ግራ አጋብቶን አለ፡፡ በንጉሱም፣ በደርግም ሆነ በዘመነ ኢህአዴግ ሊታረቅ ያልቻለው ይህ በሽታችን “በሞተ ስርዓትና አገዛዝ” እንድንመራ አስገድዶናል። ይህ በሽታችን ስር ከመስደዱ የተነሳ የአገራችንን ሁኔታና አካሄድ እንደ አልቃሹ ሰውዬ “አረ እኔስ ጨነቀኝ” የሚያሰኝ ሆኗል።
እርስ በርስ የመጠላለፍና አንዱን በሌላው ላይ የማሳደም፣ ራዕይና አርቆ አሳቢነት፣ ከሁሉም በላይ ቀናነት የጎደለው የተቃውሞ ፖለቲካ መንደር ለሁሉም ወገኖች ዋስትና በሚሰጥ መልኩ አለመቃኘቱ የአገሪቱን ህልውና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል። በዚሁ ሳቢያ ህወሃት የዘራው የጥላቻ መርዝ የሚያረክስ መስመር የሚዘረጋልንና በተበዳዮችና በበዳዮች ዘንድ ክብር የሚሰጠው “ተተኪ” መሪ ማግኘት አቅቶን፤ ያሉን ተቃዋሚ ሃይሎችም “በጠላቶቻችን መቃብር ላይ …” በማለት ካልፈረሰ በስተቀር መገንባት አይቻልም በሚል ግራ የገባው ዲስኩር ሰክረው ሁለት አስርት ዓመታት “አረ እኔስ ጨነቀኝ” እያልን ለመኖር ተገደናል።
ኢህአዴግ ወላልቋል። አሁን ከብበውና አንቀው ከያዙት ችግሮች አንጻር፣ እንኳን ለማይወዱት በስሙ ለሚምሉበት ግልገሎቹና ባሮቹ ዋስትናቸው ሊሆን እንደማይችል እየተነገረ ነው። ሙስናው፣ ድህነቱ፣ ፖለቲካዊ ንቅዘቱ፣ ማርጀቱ፣ በቡድን መከፋፈሉ፣ የተሳፈረበት የግፍ ባቡር ነዳጅ መጨረሱ፣ በከፍተኛ ደረጃ መተማመን የማይችሉበት ደረጃ ለመድረሳቸው ምስክር ሆኗል። ይኸው አደገኛ ወቅት አገር ወዳዶችን እያስጨነቀ ነው። አገር በቡድንና በደቦ ይመራል በሚል ዘባተሎ ምክንያት በየቀኑ የሚሰማው የስርኣቱ የመደንበር ምልክት ህግና ህጋዊነት ማክተማቸውን የሚያረጋግጥ ሆኗል። በህወሃትም ሆነ በኢህአዴግ ደረጃ አለቃና ታዛዥ መለየት አልተቻለም። የበላይና የበታች ተቀላቅሎ አቤት ማለት ያዳገተበት ወቅት ላይ ተደርሷል። “ህግ ፈረሰ፤ መንግስት ፈረሰ” ነውና !!
አሁን ያለንበት ወቅት በለውጥ ቋፍ ላይ ነው። ከውስጥም ከውጪም ራሱ ህወሃትና ድቃይ ድርጅቶቹ ዘንድ ፍርሃቻ አይሏል። በትራፊ ዘመን ከህሊናቸው ጋር ለመታረቅ የሚመኙም አሉ። ባለቀ ወቅት አገራችን እንዳለች እንድትቀጥል እርቅን የሚሹ ኢህአዴጋዊያን ጥቂት አይደሉም። የህዋሃት ሰዎችም ቢሆኑ ከዚህ የስጋት ርእደት ውጪ እንዳልሆኑ እየተሰማ ነው። በሁሉም ደጅ “አረ እኔስ ጨነቀኝ” የሚሉ በዝተዋል። ያጣነውና የተቸገርነው ለበጎ ተግባር የሚያስተባብር ጀግና ብቻ ነው። በወዳጅም፣ በጠላትም፣ በመሃል ሰፋሪውም፣ በአብዛኛው አድፋጮችም (silent majority)፣ በህወሃት ቁንጮዎችም ሆነ ሌሎች ስማቸው ባልተጠቀሱት ዘንድ ተቀባይነት ያለህ፣ ያለሽ፣ ያላችሁ፣ የጸዳችሁ፣ ያልተነካካችሁ፣ “እንከበራለን” የሚል ጽኑ እምነት ያላችሁ “አረ እኔስ ጨነቀኝ” ለሚሉ ወገኖች ድረሱ!!
ሁሉንም ወገን ነጻ የሚያወጣ ማን ነው? ማን ናት? ለሰብዓዊነት የቆመ … እንደ ሴትየዋ እንደ ራስህ ሳይሆን እኔ እንደምልህ … ከሚል የትዕዛዝና የታቃዋሚ መንግሥትነትና አምባገነንነት የራቀ፤ ራሱን ጨምሮ ሌላውን ነጻ የሚያወጣ እምነት ለኢትዮጵያ!
Link:-http://www.goolgule.com/so-worried/

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.