Wednesday, April 9, 2014

ምስክሮችን ከአደጋ ለመጠበቅ የቀረበ የሀሳብ መርሀ ግብር፣

April 9, 2014
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ፍትህ እንደገና ዘገየችን?
እ.ኤ.አ በዚህ ዓመት በጃኗሪ ወር መጨረሻ አካባቢ “ኬንያታ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ/ICC): ዘግይቶ መቅረብ ፍትህ እንደተነፈገ መቆጠር የለበትምን?“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ ትችቴ ላይ ICC የኡሁሩ ሙጋይ ኬንያታን ጉዳይ አስመልክቶ በሄግ እያደረገ ያለው ተደጋጋሚ የፍትህ ሂደቱን የማዘግየት ስራ፣ በቀጠሮ የማሳለፍ እና “የውሸት ማስረጃዎች” እንዲሁም “የሀሰት ምስክሮች” በማቅረብ እንደገና የመታየት ዕድል ለመፍጠር እየተነገረ እና በተግባር እየተፈጸመ ያለው አጠቃላይ ወደኋላ የመንሸራተት ሁኔታ እንቅልፍ ባያሳጣኝም ክፉኛ ያሳሰበኝ መሆኑን በግልጽ አሳዉቄ ነበር፡፡ በዚህ ድርጊት ላይ ምናልባትም የሆነ የማታለል ስራ እየተካሄደ ያለ መስሎ ታይቶኛል፡፡ ይኸ ነገር ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም ለማለት ባይዳዳኝም የጥርጣሬ ጠረኑ ግን እየሸተተኝ ነው፡፡ ኬንያታ ከተከሰሱበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ነጻ በመሆን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት/አይይሲ መዳፍ ስር እንዲወጡ መድረኩ እየተመቻቸ ነውን? የኬንያታ የፍርድ ሂደት በICC ውሳኔ እንደገና ለሌላ የጊዜ ቀጠሮ እንዲተላለፍ መደረጉ በጉዳዩ ላይ ጥርጣሬን በመፍጠር በአሁኑ ጊዜ ከቀድሞው የበለጠ አሳስቦኛል፡፡
International Criminal Court
ባለፈው ሳምንት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት/ICC የኬንያ ፕሬዚዳንት የሆኑትን የኡሁሩ ኬንያታን የፍርድ ሂደት እንደገና በማስተላለፍ እ.ኤ.አ ለኦክቶበር 7/2014 ቀጠሮ ሰጥቶበታል፡፡ እንደ ICC የፍርድ ሂደት ችሎት መግለጫ ከሆነ “ቀጠሮውን የማስተላለፉ ዋና ዓላማ ለጉዳዩ ዋና ውንጀላዎች ናቸው ተብለው በፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል እንዲቀርቡለት ተጠይቀው የነበሩትን የማስረጃ ሰነዶች አሟልቶ ለማቅረብ እንዲቻል ለኬንያ መንግስት ተጨማሪ ውሱን የሆነ የጊዜ ገደብ እድል ለመስጠት ነው፡፡“ ኬንያታ ከሌሎች ተከላካዮች ጋር የኬንያታ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑትን ዊሊያም ሩቶን ጨምሮ እ.ኤ.አ በ2007 መጨረሻ እና በ2008 መጀመሪያ አካባቢ ድህረ ምርጫ ውዝግብን ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ በሰው ልጆች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በበላይነት ሲመሩ እና ሲያስፈጽሙ ነበር በሚል ውንጀላ በርካታ ክሶች ተመስርተውባቸዋል፡፡ ከምርጫው ጋር ተያይዞ በተነሳው ሁከት ምክንያት ከ1,100 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ እና 600,000 ሰዎች ደግሞ እንደተፈናቀሉ ይታመናል፡፡ በዚያው ዓመት በጃኗሪ ወር “አንድ ምስክር እራሱን ከምስክርነት ካገለለ እና ሌላው ደግሞ የሀሰት መረጃ እንዲሰጥ ከተፈቀደለት በኋላ“ የICC አቃቤ ህግ በኬንያታ ላይ የቀረቡትን መረጃዎች ለመመርመር እንዲችል የሶስት ወራት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር፡፡
የኬንያታ ጉዳይ ለፍርድ ይደርስ ይሆን? የመጥፎ ዜና እንዲሁም የአፈታሪኮች መርዶ ነጋሪ መሆንን እጠላለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ፍትህ እውነታን ፊትለፊት ለመጋፈጥ የማትችል እርባና የለሽ ሆናለች፡፡ እስከ አሁንም በማህጸን ውስጥ ያለች ህጻን ናት! ኡሁሩ ኬንያታ በሄግ የICC የችሎት ክፍሎች ውስጥ በፍጹም ሊቆሙ አይችሉም፡፡ ይህ ጉዳይ የተበላ ዕቁብ ነው፡፡ ግድያም ሆነ በሌሎች በሰው ልጆች ላይ ፈጽመዋል ተብለው በተወነጀሉባቸው ጉዳዮች በምንም ዓይነት መንገድ ፍርድ አይቀርቡም፡፡ ከፍርድ አምልጠዋል:: ይህንን እርሱት! ይልቁንስ ወደ ሌሎች ነገሮች እንለፍ…

ጉዳዩን መካድ፣ ማዘግየት፣ መከላከል እና ማጥፋት፣
ኡሁሩ ሙጋይ ኬንያታን ወደ ሄግ የፍትህ አደባባይ ለማምጣት የሚደረገው ትግል ከባድ ቢሆንም ሽንፈትን ለማመን ወይም አምኖ ለመቀበል በፍጹም አልሞክረውም፡፡ የICCን አቃቤ ህግ እና የእራሱን የICCን ሀሳብ እጋራለሁ፡፡ ከትዕይንቱ ጀርባ ባሉት ኃይሎች ምክንያት ብዙ ተፀኖ ይሰማቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ኬንያታ “ምናባዊ ፕሬዚዳንት“ (በአፍሪካውያን/ት ትርጉም መሰረት “ከሰው ህጎች እና ከአምላክ በላይ” ናቸው፡፡ እርሳቸው የማይነኩ ፍጡር ናቸው፡፡ ICC ፍርድ ቤት ፣ የICC አቃቤ ህግ፣ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እና የምዕራቡ ዓለም በአጠቃላይ በአፍሪካ አምባገነን ገዥዎች በተያዘው የሸፍጥ ስራ ብቻ አይደለም ተበሳጭተው የነበሩት ነገር ግን “ዘር አደና“ የሚል የሚቆጠቁጥ ክስ በሚያቀርቡት ጥቂት የአፍሪካ “መሪዎች” ጭምር እንጅ፡፡ እ.ኤ.አ ከ2013 አጋማሽ ጀምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ መሪዎች ኬንያታ በሰው ልጅ ላይ በፈጸሟቸው ወንጀሎች ላይ  ህዝብ የሚኖረውን የሀሳብ አቅጣጫ ለማስቀየስ በማሰብ የዘር አደና የሚል እርባናየለሽ የጩኸት ከበሯቸውን በመደለቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት ተዘዋዋሪ ሊቀመንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ንዴት እና ስሜታዊነት በተቀላቀለበት አኳኋን ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እና የICC አቃቤ ህግ በጥቁር አፍሪካውያን መሪዎች ላይ የሚያካሂደው “የዘር ማደን” ዘመቻ መቆም አለበት የሚል ክስ በጩኸት አሰሙ፡፡ አቶ ኃይለማርያም እና የውጭ “ጉዳይ ሚኒስትራቸው” እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2013 በአፍሪካ ህብረት ልዩ ጉባኤ ላይ የዘር አደና ካርድን በICC ፊት ላይ በመምዘዝ የአፍሪካ የህብረቱ አገሮች በደቦ “ከሮም ስምምነት” እራሳቸውን እንዲያገሉ የማድረግ የትውና ሙከራ አደረጉ፡፡ ይህ ክስተት ለአፍሪካ እጅግ አሳፋሪ ሁኔታን ያመላከተ ወቅት ነበር፡፡ በዚህም መሰረት አፍሪካውያንን እያሳደደ ከሚያድነው (ዘር አዳኝ) ፍርድ ቤት ለማዳን እና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ የሚል ሀሳብን መሰረት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ስብሰባቸውን አደረጉ፡፡ መሪዎቹ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በተጻራሪ በመቆም ባዶ፣ የተጋነነ እና እራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ጩኸትና እምቢልታ አሰሙ፡፡ ሆኖም ግን ከሮማ ስምምነት እራስን ማግለል የሚለው “የብዙህን ስምምነት መጣስ” ጩኸትና ሴራ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ከሮማ ስምምነት በደቦ እንወጣለን የሚለው ስሜታዊነት እና እብደት የተሞላበት ማስፈራሪያ ባዶ ጩኸት ከመሆን ባለፈ የፈየደው ነገር የለም፡፡
ኬንያታ በዓለም አቀፉ የጸረ ሽብር ዘመቻ በአፍሪካ ቀንድ “ቁልፍ ሚና” የሚጫወቱ ሰው ናቸው፡፡ ኬንያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጭካኔ የተሞላበት እና አረመኒያዊ የሽብር ጥቃት ሰለባ ሆናለች፡፡ ያልታሰበበት የህግ ውጤት የኬንያታን እርዳታ ጠይቋል፡፡ ኃያላኑ መንግስታት የጸረ ሽብርተኝነት  “አጋሮቻቸው” አንዱ የሆነውን (በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል አጋሮቻቸው አላልኩም) በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸምን ወንጀል በአደባባይ እየተዋጋ ያለውን ሰው እራሱ በጸረ ሽብርተኝነት ተከስሶ ለፍትህ አደባባይ እንዲቀርብ አይፈቅዱም፡፡ ቀጣዩ ባለወር ባለሳምንት ማን ሊሆን ይችላል? የሱዳኑ ኦማር አልባሽር ሊሆኑ ይችሉ ይሆን? (ኦማር አልባሽር እ.ኤ.አ በ2009 ICC በመሰረቱት ክስ ላይ ንቀትን በማሳየት እንዲህ ብለው ነበር፡ “የICC አቃቤ ህግ፣ የፍርድ ቤቱ ዳኞች እና ማንም ፍርድ ቤቱን የሚደግፍ ሁሉ በእኔ ጫማ ስር ያሉ መሆናቸውን በሙሉ ንገሯቸው፡፡“(ይህንን ሲሉ “እራሳችሁ በኔ ጫማ ሄዳችሁ አዩት ማለታቸው አይደለም” ማለታቸው አይደለም፡፡ የዩጋንዳው ዮሪ ሙሴቬኒስ? የሩዋንዳው ፓውል ካጋሜስ? የዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤስ? የካሜሮኑ ፓውል ቢያህስ? የኢኳቶሪያል ጊኒው ቴኦዶሮ ኦባንግ ጉማስ? በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ ኢትዮጵያን እያዋከበ ያለው የወንጀለኛ ቡድንስ?
ኬንያታ እንደ ላይቤሪያው ቻርለስ ቴለር፣ እንደ ኮትዲቯሩ ሎሬንት ባግቦ ወይም ደግሞ እንደ ቻዱ ሁሴን ሃብሬ ከፕሬዚዳንትነት የስልጣን ወንበራቸው ላይ ሰለሌሉ ለፍትሕ  ቀርበዋል፡፡ እነዚህ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል የፈጸሙ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች የሚካሄደው የፍትህ ሂደት ትክክለኛ ፍትሀዊ ጨዋታ ነው፡፡ ከስልጣናቸው ተወግደዋልና፡፡ እንደ ኬንያታ ሁሉ ጠቃሚነት ያለው ዓላማን ሊያሳኩ አይችሉምና፡፡ እነዚህ ግፈኞች በአሁኑ ጊዜ በICC እስር ቤት በቁጥጥር ስር ሆነው የፍርድ ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡
ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ የICC የፍትህ ወይዘሪት በአንድ እጇ የፍትህ ሚዛንን በሌላኛው እጇ ደግሞ ጎራዴን በመጨበጥ “በሰው ልጆች ላይ ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ የአፍሪካ ቅምጥ ፕሬዚዳንቶችን እና ጠቅላይ ሚኒስትሮችን እንዴት ነው ወደ ፍትህ አደባባይ ለማምጣት የሚቻለው? (ወይዘሪት ፍትህ በእርግጠኝነት አይነ ስውር ነች ወይስ ደግሞ ሆን ብላ ዓይኗን ጨፍናለች?) ለዚህ መልሴ አጭር እና ቀላል ነው፡፡ ቅምጥ የአፍሪካ ገዥዎችን በተንፈላሰሰው ቤተመንግስታቸው ላይ ሆነው የሚንደላቀቁትን በአሁኑ ጊዜ ከስልጣናቸው ተወግደው በICC እስር ቤት በቁጥጥር ስር ያሉትን የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች አንደሚዳኙት መዳኘት ነው፡፡ ወይዘሪት ፍትህ አውቀሽ የጨፈንሽውን አይንሽን ግለጭ እናም የICCን የፍትህ ሂደት በተገለጠው አይንሽ በመመልከት ትክክለኛውን ፍትህ ስጭ፡፡ በአፍሪካ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ምርጫን በመዝረፍ ወይም ደግሞ በወንጀለኝነት እንዳይጠየቁ የህግ ከለላ ተደርጎላቸው ተቀናቃኞቻቸውን በጅምላ በመግደል ወደ ስልጣን በሚመጡ የአፍሪካ ወንጀለኛ ወሮበሎች የተሞላ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ “ፕሬዚዳንት ወይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር” መሆን ማለት ለመግደል፣ ለማሰቃየት፣ እና ያለምንም ተጠያቂነት በሰው ልጆች ላይ ወንጀል ለመፈጸም የፈቃድ ሰርቲፊኬት እንደማግኘት ያህል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ታምራዊ በሆነ መልኩ ኬንያታን ወደ ICC የፍትህ አደባባይ ማቅረብ የሚቻል ከሆነ (ምንም አሳማኝ ነገር ባይኖርም) በዘመናዊት የአፍሪካ ታሪክ የህግ የበላይነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያስቀምጥ ታላቅ የመርህ ክስተት ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመግዛት ላይ ያለ እያንዳንዱ የአፍሪካ አምባገነን መሪ እና ወደፊትም በአምባገነንነት ወንበሩ ላይ ፊጥ ለማለት የሚቋምጡት ህሊናየለሾች ተቀናቃኞቻቸውን እና ሰላማዊ ዜጎችን ለማስገደል፣ ለማሰቃየት እና ወደ እስር ቤት ለማስጋዝ ወሮበላ አገልጋዮቻቸውን ከመላካቸው በፊት ሁለት ሶስት ጊዜ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡
ወደ ሌላ ከማለፌ በፊት በኬንያታ ምክትል በሆኑት ዊሊያም ሩቶ ላይ ICC እያካሄደ ስላለው የፍትህ ትወና ዓይነቶች ትንሽ ማስታወሻ ልስጥ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሩቶ የፍርድ ሂደት በመታየት ላይ ነው፣ ሆኖም ግን አንዳንድ ጊዜ በፍርድ ቤቱ በግንባር አይገኙም ወይም ደግሞ ብዙ ጊዜ አይታዩም፡፡ ይህ ታላቅ ፌዝ ነው ሩቶ በአንክሮ ሊያስበቡት ይገባል፡፡ የዊሊያም ሩቶ በፍርድ ሂደቱ ላይ አለመቅረባቸው ICCን የማታለል ዘይቤ በግልጽ ያመላክታል፡፡ ባለፈው ሳምንት የICC ዋና አቃቤ ህግ ማዳም  ፋቱአ ቤንሱዳ ሩቶ በየቀጠሮው ጊዜውን በማክበር በፍርድ ሂደት ችሎቱ ላይ እንዲገኙ ለማስገደድ አልቻሉም፡፡ ሩቶ ምንም እንደማይሆኑ በእራሳቸው ላይ የመተማመን ሁኔታ ይታይባቸዋል ምክንያቱም የእርሳቸው ጉዳይ ከሌሎች ከብዙዎች ጋር ኬንያታን ጨምሮ ያሉበት ስለሆነ ነው፡፡ የፍርድ ሂደቱን ኬንያታ ጊዜ ማቃጠል አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ለእርሳቸው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ተውኔት ነው፡፡
ከሙያ ስነምግባር ውጭ በሆነ መልክ የኡሁሩን የመከላከያ ቡድን እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ የፍርድ ሂደቱን በማዘግየት እና የICCን ዋና አቃቤ ህግ በማስገደድ ዓይነት መልኩ ሰይጣናዊ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ በእርግጥ “የወንጀለኞች መከላከያ መጽሐፍ” የሚለውን ለዘመናት የቆየውን ለመከላከል የህግ ባለሙያ ሶስት ህጎችን የሚገልጸውን እንደገና አድሰዋል፡ 1ኛ) መካድ (ክሶችን)፣ 2ኛ) ማዘግየት (የፍርድ ሂደቱን)፣ እና 3ኛ) ማስረጃዎችን በመደበቅ እና ለምስክሮች ጉቦ መስጠት) የሚሉት ናቸው፡፡ የኬንያታ የመከላከያ ጠበቆች ሌላ 4ኛ ህግ ጨምረዋል፣ ይህም ከላይ ከ1-3 የተዘረዘሩት ህጎች ጉዳይ ትኩረት እንዳያገኝ እንዲሳሳ እና በመጨረሻም እንዲተን ማድረግ ነው፡፡ የICC ዋና አቃቤ ህግ የሆኑት ለምርመራው ወሳኝ የሆኑትን በጣም ጠቃሚ የሆኑ ማስረጃዎችን እንዳያገኙ እጅግ በጣም አስቻጋሪ የሆነ ሁኔታን በመፍጠር አዲስ ዓይነት የአጨዋወት ዘይቤን ተጫውተዋል (ኳሷን በመደበቅ)፡፡ የኬንያታ የህግ ባለሙያዎች እና የኬንያ ዋና ጠበቃ የሆኑት ጊሁ ሙጋይ የኬንያታ የገንዘብ ዝውውር ፍሰት ግልጽ እንዳይሆኑ ለመከላከል እና ኬንያታ በቀጥታ ወይም በሌላ ሶስተኛ ወገን በኩል ወደፊት የሚመሰክሩት ምስክሮች እንዳይመሰክሩ፣ እንዲክዱ ወይም ከጊዜ ብዛታ “ድርጊቱን እንዲረሱት” ለማድረግ ገንዘብ ወይም ደግሞ ጉቦ ሰጥተው ወይም በሌላ በኩል እንዲሰጥ አድርገው ለlCC ዋና አቃቤ ህግ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎች እንዳይገኙ በማድረግ የተመዘገቡ የባንክ ማስረጃዎች እንዳይገኙ ጥረት በማድረግ የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል፡፡
ኬንያታ እና ሩቶ ከICC ያለምንም ቅጣት እና በሮማ ደንብ ላይ የውሸት ማስመሰያ ተውኔት በመፈጸም በመሄዳችሁ (በመለቀቃችሁ አላልኩም) “እንኳን ደስ ያላችሁ” ለማለት የመጀመሪያው ለመሆን እፈልጋለሁ፡፡ ጠቅላላው የአፍሪካ ህብረት ሽባ አመራር እስከ አሁን ድረስ ማድረግ ያልቻለውን ለማድረግ ችለዋል፡፡ “የICC ወይዘሪት ፍትህ” ዓይኗን ጨፍና እና እጆቿን ታስራ ቆማለች እና ሸፍጠኞቹ እራሳቸውን ለማሸሽ ችለዋል፡፡
ፍትህን ማዛባት በምንም ዓይነት መልኩ የኬንያታ እና የሩቶ ብቻ አይደለም፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካም ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ተዋቂው ወሮበላ ወንጀለኛ ጆን ጎቲ ባለፉት አመታት ብዙ የማጭበርብር ስራዎችን በመስራት፣ በግድያ፣ ህግን በመጣስ፣ በጠለፋ፣ በህገወጥ የገንዘብ ብድር፣ በቁማር፣ ፍርድ ቤት በማወክ እና ምስክር በማስፈራራት ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በህግ እየታየ ነበር፡፡ ሶስት ጊዜ ክሱን ውድቅ አስደርጓል፡፡ አንድ ጊዜ የተከፈተበትን ክስ ለማዘጋት ለአንዱ የዳኞች አባል 60 ሺህ ዶላር ጉቦ ከፍሏል፡፡ የጎቲ የመከላከያ ጠበቆች ቀጣይነት ባለው መልክ በቤተሰብ ላይ የተፈጸመን ወንጀል እና የመንግስትን የህግ ጉዳይ በግላዊ ጥላቻ ነው በሚል ክህደት አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም ጎቲ በእርሱ የበታች ሹም በሆነው የማፊያ ቡድን አባላትን ህግ ወይም የወሮበሎችን የስነምግባር መመሪያ በጣሰው በሳልቫቶር ምስክርነት በብዙ ከባድ ወንጀሎች ክስ ተመሰረተበት፡፡ ለዚህ ሳምንት ትችቴ ያመጣኝ ዋናው ነጥብ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው…
ICC ምስክሮች የተቀነባበረ የደህንነት መከላከያ መርሀ ግብር አስፈላጊነት፣
የኬንያታን ጉዳይ በተመለከተ የICC ምስክሮች የተቀነባበረ የደህንነት መከላከያ መርሀ ግብር አስፈላጊነት ወቅታዊ እና አስገዳጅ ሁኔታ ነው፡፡ ኬንያታ ከሙንጉኪ (የኬንያ የማፍያ ቡድን) ጋር የሸፍጥ ስራ ይሰራሉ እየተባሉ የሚወነጀሉ ሲሆን እንደ ዋነኛው በዓለም ላይ ታዋቂነት ካለው የማፍያ ቡድን ሁሉ ከባድ ወንጀል የተመዘገበበት አታላይ ድርጅት ነው፡፡ ኬንያታ ከሙንጉኪ (ይህ ዓይነት ድርጅት በእርግጠኝነት ስለመኖሩ ባይረጋገጥም) ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ክደዋል፡፡ እርሳቸው እና የአፍሪካ ህብረት መሰሎቻቸው የICC የክስ ሂደት በዘር  ጥላቻ የተሞላ ነው በማለት ደምድመዋል፡፡ እንደ ሎስአንጀለስ ታይምስ ዘገባ ከሆነ ሙንጉኪ “በዓለም ትልቁ እና በጣም አደገኛ የወሮበላ ስብስብ እንዲሁም ዘግናኝ አደጋ የሚያደርስ እና የኬንያን ህዝብ በማስፈራራት የሚዘርፍ ወሮበላ የሌባ ስብስብ ነው” በማለት ገልጸውታል፡፡ የICC ዋና አቃቤ ህግ “ከሙንጋኪ አመራሮች ጋር ብዙ ጊዜ ይገናኙ እንደነበር አንዳንድ ጊዜም በመንግስት ቢሮ በኬንያ ነጩ ህንጻ ይገናኙ እንደነበር ለዚህም በሪፍት ቫሊ ከተማ ጥቃት ለመሰንዘር ዕቅድ ይነድፉ ነበር“ እንዲሁም በአንድ ስብሰባ ላይ ኬንያታ 3.3 ሚሊዮን የሚሆን የኬንያ ሺልንግ (36 ሺህ የአሜሪካ ዶላር) ጥቃቱን እንዲፈጽሙ ኃላፊነት ለሰጧቸው ሰዎች አከፋፍለዋል” የሚል ውንጀላ አቅርበውባቸዋል፡፡
በኬንያታ ጉዳይ ላይ ምስክሮችን የማወክ እና ምስክርነት እንዳይሰጡ ማስፈራራት እየተደረገባቸው እንደሆነ በርካታ ማስረጃዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ እ.ኤ.አ ዴሴምበር 19/2013 የICC ዋና አቃቤ ህግ የሆኑት ማዳም ፋቱአ ቤንሱዳ በይፋ እንዲህ ብለዋል፣ “ዴሴምበር 4 ቁልፍ የሆነ ሁለተኛ ምስክር በወሳኙ የፍርድ ሂደት ወቅት ለፍርድ ቤቱ የሀሰት መረጃ እንደሰጠ አምኗል፡፡ ይህ ምስክር በአሁኑ ጊዜ ከምስክርነት ዝርዝሩ ውስጥ ተወግዷል… የእኔን መረጃ በጥንቃቄ በመመልከት እና የሁለቱን ከምስክርነት መወገድ የሚያስከትለውን እንደምታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአሁኑ ጊዜ በሚስተር ኬንያታ ላያ ያለው ጉዳይ የፍርድ ሂደቱን ሊያስቀጥል የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ ከፍተኛ የመረጃ መኖርን አያሟላም የሚል ድምዳሜ አለኝ… ስለዚህም ሌሎች ተጨማሪ ማስረጃዎችን የማግኘት ጥረቶችን ለማሳካት እንዲሁም ደግሞ የሚገኙት መረጃዎችም ቢሆን የመስሪያ ቤቴን የምርመራ ሂደት ዝቅተኛውን መስፈርት ማሟላት አለማሟላታቸውን በሚገባ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል፡፡“ ከማዳም  ቤንሱዳ መግለጫ ግልጽ የሆነ ነገር አይታይም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሁለቱ ምስክሮች ለምን የሀሰት ምስክርነት እንደሰጡ የሚታወቅ ነገር የለም፣ እንዲሁም የICC ዋና አቃቤ ህግ ቢሮ ፋይሉን ወደ ጎን ከማድረጉ በፊት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሌሎቸ መረጃዎችን ለመመርመር እንዳልቻለ ሲታሰብ ሂደቱ በሙሉ ግልጽ አይደለም፡፡
ሆኖም ግን በኬንያታ ላይ የቀረቡት ምስክሮች የምስክርነት ቃላቸውን እንዳይሰጡ ማስፈራሪያ እና ጉቦ የተሰጣቸው መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በፌብሯሪ 2013 ዋና አቃቤ ህግ ወ/ሮ ቤንሱዳ ከኬንያታ ጋር የተገናኙ ምስክሮች ጉቦ ተሰጥቷቸዋል ወይም ደግሞ የምስክርነት ቃል እንዳይሰጡ እና በጉዳዩ ላይ ምስክር ሆነው እንዳይቀርቡ ክፍያ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ማዳም ቤንሱዳ እንዲህ በማለት ገልጸዋል፣ “ሜይ 2012 በተደረገው ቃለ መጠይቅ 4ኛው ምስክር ከምስክርነት እራሱን እንዲያገል እና በኡሁሩ ላይ የምስክርነት ቃል እንዳይሰጥ የከሳሾች ተወካዮች ከሆኑ ሰዎች ገንዘብ እንደተሰጠው እና እንደተቀበለ ተናግረዋል… የጉቦ አሰጣጥ መርሀ ግብሩን ለማመቻቸት ምስክሩ የኢሜይል አድራሻውን እና የባንክ አካውንቱን ሰጥቶ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ይህን ያህል የተገለጸ እያለ ፍርድ ቤቱ ምስክሩን መጠቀሙ አስፈላጊ አይደለም፡፡“ አይን ያወጣ ድፍረት በተቀላቀለበት ሁኔታ የኬንያታ የመከላከል ቡድን ICC ጉዳዩን ወደ ኬንያ ባለስልጣኖች እንዲመራ እና ማስረጃ የሚሆኑ ምስክሮችም በዚያው መሰረት ቀርበው ማስረዳት እንዲችሉ ተከሳሾችም እራሳቸው ባመኑት ወንጀል መሰረት የህጉ ሙሉ ተፈጻሚነት እንዲኖረው በማለት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ዋና አቃቤ ህግ ቤንሱዳ ስለምስክሮች ማስፈራራት እና የማደናቀፍ ስራዎች መስራት ሁኔታ ያሳሰባቸው መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ለምስክሮች ደህንነት ጥበቃ ሲባል የእራሳቸው የፍርድ ቤት ክፍል እንዲሰጣቸው፣ እንዲሁም የድምጽ እና የምስል ማዛባትን፣ የማስመሰያ እና መረጃዎችን ለመለየት የተለየ የካሜራ አጠቃቀምን በስራ ላይ ማዋል የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
በግልጽ የሚታየው የኬንያታ ምስክሮች ክህደት ያልተቋጩ እና እንቆቅልሽ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድዱናል፡፡ ምስክሮች የምስክርነት ቃላቸውን እንዳይሰጡ እንዲወጡ ተደርገዋል፣ ይህ የተደረገው “የሀሰት የምስክርነት ቃል” በመስጠታቸው ምክንያት ብቻ አይደለም ምክንያቱ ግን በፍርድ ቤቱ ችሎት አካባቢ ከታዩ እና የምስክርነት ቃላቸውን ከሰጡ የተወሰኑ እና ፈጣን የበቀል እርምጃዎች እንዳይወሰዱባቸው ስለፈሩ ነው፡፡ የክህደት ምስክርነት መስጠታቸው እንደ እውነት መወሰድ የለበትም ነገር ግን በኬኒያ ባለስልጣኖች ምክንያታዊ የሆነ የማይቀር ማሰቃየት እና ፍትሀዊ ያልሆነ የፍርድ ሂደት ስለባ ስለሚሆኑ ነው፡፡ በኬንያ መንግስት የሚወሰዱባቸውን መጠነ ሰፊ የብቀላ እርምጃዎች በመፍራት ምስክሮች በድንገት ህይወታቸውን ለማዳን ሲሉ የሀሰት ምስክርነት ለመስጠት ቢወስኑ ማንንም ሊያስገርም ይችላልን?
ባለፈው ሁምሌ የዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፕሮግራም ዓለም አቀፍ ማህበር “ምስክሮች በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፊት“ በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ መሰረት በችሎት ፊት የሚታዩ ጉዳዮችን በሚመለከት ICC የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለማስወገድ “የምስክሮችን መብቶች መጠበቅ፣ መደገፍ እና ማረጋገጥ” የሚል ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ ዘገባው በ ICC የምስክርነት ጥበቃ ጥረቶች እና አገልግሎቶች በማለት በርካታ ጉድሎቶቹን ነቅሶ አውጥቷል፡፡ እነዚህም ጉድለቶች “የመንግስትን ትብብር ማግኘት፣ የምስክሮችን አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ፍላጎቶች ማሟላትን፣ የሎጂስቲክስ ማሟላትን፣ ሄግ በሰላም የሚሄዱበትን ሁኔታ የማመቻቸት እና በምርመራ እና በችሎት ሂደት ወቅት ግለሰቦችን ወደፊት ከሚፈጠሩ ማስፈራራቶች ወይም ጣልቃገብነቶች መጠበቅ“ ያካተቱ ናቸው፡፡ ዘገባው በዝርዝር የሚከተሉተን ግኝቶች አካትቷል፡፡
የምስክርነት ቃል የሰጡ የICC የህግ ምስክሮች የህጋዊነት ሁኔታ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ የICC የህግ ሰነዶች ለምስክሮች ደህንነት ጥበቃ የሚሰጡ ቢሆንም እነዚህ ምስክሮች የምስክርነት ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ምን ይሆናሉ ለሚለው ጥያቄ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው፡፡ ይህ ሁኔታም የምስክርነት ቃል እንዳይሰጡ ለታገዱ ሰዎችም ይሰራል በእራሳቸው ተነሳሽነት የምስክርነት ቃል ለመስጠት የሚቀርቡትን ምስክሮች እንኳ ጨምሮ ማለት ነው፡፡ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የዓለም አቀፉ የጠበቆች ማህበር የICC ምስክሮች ተቋርጦ የቆየ አስቸጋሪ የህግ ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ ለማግኘት የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ከበርካታ ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ICC ወይም ኔዘርላንድ የሚከተሉት የወደፊት ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከምስክርነት የታገዱ ሰዎች (ከዚህ ቀደም ምስክር ይሁኑ ወይም አይሁኑ) በደህንነት ስጋት ምክንያት ወደ አገራቸው ለመመለስ የማይችሉ ሰዎች ሁኔታ በግልጽ መቀመጥ አለበት፡፡ የጠበቆቹ ማህበር ICC የመንግስታት ፓርቲዎች እና የሀገር ውስጥ የመንግስት ስራ ምስክሮች ከጥገኝነት ጋር በተያያዘ መልኩ ለታገዱ ሰዎች ከእያንዳንዳቸው የሰብአዊ መብት አኳያ ታይቶ በአንድነት የጋራ ፖሊሲ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡
አንዳንድ ምስክሮች ICC ድረስ በመገኘት የምስክርነት ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ጥገኝነት በሚፈልጉበት ወቅት የህግ ቅዠቶች ይገጥሟቸዋል፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ የጠበቆች ማህበር ዘገባ ከሆነ እ.ኤ.አ በ2011 ቶማስ ሉባንጋ ዲሎ፣ ጀርማይን ካታንጋ እና ማቴው ኑጆሎ ቹይ የተባሉ የመከላከያ ምስክሮች የምስክርነት ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ICC በመቅረብ ከመመስከር ጋር በተያየዘ መልኩ ያላቸውን የህጋዊነት ከባድ ጥያቄ በማንሳት “በኔዘርላንድ የጥገኝነት ጥያቄ” አቅርበው ነበር፣ ዘገባው “እነዚህ የጥገኝነት ጥያቄዎች ወደ ሂግ የሚሄድባቸው እና ግራ የሚያጋቡ በሀገር ውስጥ፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት ህጎች ጋር የሚደራረቡ እና የሚመሰቃቀሉ እንዲሁም ስለእነዚህ ምስክሮች ሰብአዊ መብት ግዴታዎችን ማን እንደሚወስድ እና የግዴታዎችስ ደረጃ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ“ በመዘርዘር አጠቃሏል፡፡
ICC የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ የመመዝገቢያ ሊስት ይይዛል፡፡ ሆኖም ግን ይህ መርሀ ግብር መሰረታዊ ጉድለት ይንጸባረቅበታል፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ የጠበቆች ማህበር ዘገባ ከሆነ “የጥቃት ሰለባዎች እና የምስክሮች መከታተያ ቡድን/ክፍል የአሰራር መዋቅር መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ምዝገባው ለመከላከያ ምስክሮች በቂ የሆነ የስራ ድጋፍ አያደርግላቸውም… እናም ለዚህ ድጋፍ መስጠቱ አስፈላጊ ነው… የምስክሮችን የቦታ መቀያየር ሁኔታ ማጠናከር ያስፈልጋል…“ የጠበቆች ማህበር ዘገባ የሚከተሉትን የመፍትሄ ሀሳቦች ያቀርባል፣ “ምዝገባው ከመንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን የምስክሮችን ቦታ መቀያየር አቅም ለማጎልበት ዕድሎች መፈለግ አለበት፡፡ ቀልጣፋ የሆነ ብሄራዊ የደህንነት መርሀ ግብር ያላቸው ብዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምስክሮችን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር በሚደረጉ ጉዳዮች ከICC ጋር ትብብር መፍጠር አለባቸው፡፡ የጠበቆች ማህበር ምዝገባው መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተጠናክሮ ለመስራት በሮማ የትብብር አሰጣጥ ደንብ መሰረት ቋሚ ያልሆኑ ስምምነቶችን በመዋዋል ምዝገባው እንዲቀጥል ማበረታታት አለበት፡፡“
ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምስክሮች ደህንነት መከላከያ የቀረበ ሀሳብ መርሀ ግብር፤
በስልጣን ላይ ያሉ በሰው ልጆች ላይ በተፈጸመ የወንጀል ክስ የአፍሪካ መሪዎችን በህግ ለመዳኘት ያለው ትልቁ ችግር (እና ወደፊትም የሚኖረው) በሚከሰሱ የአፍሪካ መሪዎች አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ታማኝነት ያላቸው ምስክሮችን ፈልጎ ማግኘት እና ቀና ትብብራቸውን ከማግኘቱ ላይ ነው፡፡ የኬንያታ የህግ ጉዳይ እንደሚያሳየው በእራሳቸው ፈቃድ ከህግ ፊት በመቅረብ በአፍሪካ “ተቀማጭ ፕሬዚዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች” እንዲሁም በሌሎችም በሰው ልጅ በተፈጸሙ ወንጀሎች የሚጠረጠሩ ወንጀለኞች ላይ በመቅረብ ሊመሰክሩ የሚችሉ ታማኝ የሆኑ ምስክሮችን ፈልጎ ከማግኘት ይልቅ የበረዶ ኳስ ከገሀነም ፈልጎ ማግኘት ይቀላል፡፡ ውጤታማ እና ጠንካራ የሆነ የምስክሮች ደህንነት መከላከል መርሀ ግብር ያለመኖር የICC ስስ ብልት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የሮማ ደንብ እንዲኖር ከተፈለገ በአፍሪካ ዘራፊ ወሮበላ መሪዎች እና በሌሎች አምባገኖች አማካይነት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸምን ወንጀል በማጥፋት ምስክሮችን የማስፈራራት፣ የማዋከብ ጉቦ የመክፈል እና ቃለ መሀላን አፍርሶ የምስክርነት ቃል የመስጠት ዕኩይ ተግባራትን  የICC ዋና አቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤቱ እራሱ ውጤታማ የምስክሮች ደህንነት ዘዴዎችን መቀየስ እና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
እንግዲህ የጆን ጎቲ እና የኡሁሩ ኬንያታ ጉዳዮች የሚገጣጠሙት ሁኔታ እዚህ ላይ ነው፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መንግስት ጎቲን ለመክሰስ ችሎ ነበር (ሶስት ቀዳሚ ዋና ውድቀቶች ቢኖሩም) ምክንያቱም ሳሚ (“እብሪተኛው”) የጎቲ የበታች የስራ ኃላፊ የሆነው ግራቫኖ በጎቲ ላይ የምስክርነት ቃል ሰጥተዋል፡፡ በዓረፍተ ነገሩ ማጠር እና የምስክሮች ደህንነት መከላከያ መርሀ ግብር መኖር ምክንያት ግራቫኖ እንደ ቢጫዋ ወፍ ዘመረ፡፡ የግራቫኖ ምስክርነት ከተደመጠበት ጊዜ ጀምሮ በደርዘኖች የሚቆጠሩ በጥባጭ ወሮበሎች ከዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ጋር ያላቸውን ስምምነት አቋረጡ እናም በበጥባጭ አለቆቻቸው ላይ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠት ጀመሩ፡፡ ይህም ሁኔታ በደርዝን የሚቆጠሩ እምነቶችን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ በጣም በጥባጭ የሆኑ በቁጥጥር ስር የዋሉ ወሮበሎችን የስምምነት ሂደት አፈራረሰ፡፡
በኬንያታ የክስ ጉዳይ ላይ የቀረበው ውንጀላ እና የተያዘው ማስረጃ በግልጽ እንደሚያሳየው የሸፍጡ ተባባሪዎች በከፍተኛ የስልጣን እከን ላይ ያሉት የኬንያ ባለስልጣኖች ብቻ አይደሉም ነገር ግን በዝቅተኛ የስልጣን እርከን ላያ ያሉ በስውር የሚንቀሳቀሱ የወንጀኞች አባላት ጭምር ናቸው፡፡ አስገዳጅ እና አሳማኝ የምስክርነት ቃል የሚመጣው በሰው ልጅ ወንጀል ሲፈጸም በሚመለከቱት ሁልጊዜ የአፍሪካ የማፊያ መሪዎች ቆሻሻ ስራ አስፈጻሚ ከሆኑት በዝቅተኛ የስልጣን ደረጃ ካሉት ከታችኛው የኃላፊነት ቦታ ነው፡፡ በከፍተኛ የስልጣን እርካብ ላይ ባሉት የአፍሪካ መሪዎች ላይ የሚደረግ የወንጀል የፍትህ ሂደት ጥሩ በሆነ መልኩ ስኬትን ተጎናጽፏል ለማለት የሚቻለው በጣም አስገዳጅ ምስክርነት እና ማስረጃዎች ሊመጡ ወይም ሊገኙ የሚችሉት ከተፈናቀሉ የጦር አበጋዞች፣ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ካሉ ኃላፊዎች እና በገንዝብ ክፍያ ቆሻሻ ስራውን እንዲሰሩላቸው ከሚመድቧቸው ህሊና ቢሶች፣ ከዘራፊ ፖሊሶች እና ከደህንነት ሰራተኞች እንዲሁም ህብረተሰቡን የጥቃት ሰለባ ከሚያደርጉ ሌሎች ወንጀለኞች ናቸው፡፡ የICC ዋና አቃቤ ህግ ዒላማ ማድረግ ያለበት የአፍሪካ መሪዎችን የአለቆችን አለቃ ብቻ አይደለም ሆኖም ግን የመንገድ ላይ አሳዳጆችን እና የእግር ወታደሮችን ጭምር እንጅ፡፡
ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የምስክርነት መከላከል መርሀ ግብር በኋላ ጥንቃቄ የተሞላበት ምስክሮችን ለማግኘት እና ጥሩውን የአሰራር ሂደት ለማስቀጠል እንዲቻል የICC ዋና አቃቤ ህግ የእራሳቸውን “ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምስክሮች ደህንነት መከላከል መርሀ ግብርን” ማጠናከር ይኖርባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአሜሪካው የምስክሮች መከላከል መርሀ ግበር (አምመመ) በተደራጁ ወንጀለኞች ከፍትህ ሂደቱ በፊት፣ በሂደቱ ወቅት እና በኋላ ማስፈራራት ለሚደርስባቸው እና አደጋ ውስጥ ለሚወድቁ ምስክሮች ውጤታማ የመከላከል አግልግሎት ይሰጣል፡፡ በመርሀ ግብሩ መሰረት ምስክሮች እና ቤተሰቦቻቸው አዲስ ዓይነት ማንነት ይሰጣቸዋል፣ አዲስ ሰነድ ይሰጣቸዋል እናም የተለየ ቅያሬ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1971 መርሀ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ምስክሮች እና የቤተሰብ አባላት በአምመመ መርሀ ግብር ተጣቀሚ ሆነዋል፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ “95 በመቶ የሚሆኑት በመርሀ ግብሩ ያሉ ምስክሮች ወንጀለኞች ናቸው፡፡” በአምመመ እ.ኤ.አ በ1970 በV ስር በተደራጀ የወንጀሎች ቁጥጥር አዋጅ ትርጉም እና ስምምነቶችን ለዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቆጥሮ በመስጠት ምስክሮችን ቦታ ለማዘዋወር እና የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ አዲስ የሚመጡ ምስክሮችን ለመጠበቅ እና ሌሎች የተደራጁ ወንጀሎች ወይም ሌላ ከፍተኛ የወንጀል አደጋዎችን ለመከላከል የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ለማፊያ የበታች አለቆች፣ ለወሮበሎች፣ የወንጀለኛ ቡድን አማካሪዎች እና ለወታደሮች ተመጣጣኝ እና በትዕግስት የሚካሄድ የፍትህ ሂደት ዕድልን በመስጠት አምመመን እንዲቀላቀሉ በማድረግ የICC ዋና አቃቤ ህግ በሰው ልጅ ላይ በተፈጸመ ወንጀል ከአፍሪካ ኃያል ባለስልጣኖች አስተማማኝ የምስክርነት ቃል የሚሰጡትን ሙሉ የምስክርነት ጥበቃ በመስጠት በሌላ አገር ከነቤተሰቦቻቸው ተዛውረው እንዲሰሩ ለማድረግ ዋና አቃቤ ህጓ ሙሉ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው፡፡ ያለICC የምስክሮች ደህንነት መከላከያ መርሀ ግብር ታማኝነት ያላቸው የምስክሮች ደህንነትን ትብብር የማግኘቱ ዕድል በጣም ውሱን ነው፡፡ አምመመ በመጀመሪያ መተግበር በጀመረበት ጊዜ ትላልቆቹን ወንጀለኞች ለመያዝ ትናንሾቹን ወንጀለኞች በመንከባከብ የሞራል ጥንክሪያቸውን አሳይተዋል፡፡ “መዳረሻው መንገዱን ያሳያል” የሚለውን የኮንግሮሱን ፖሊሲ ተችተውታል፡፡ ማፊያዎች ከቢዝነስ ባይወጡም ቅሉ ህጎችን ማጭበርበር እና አምመመ መርሀ ግብር በአሜሪካ ውስጥ የተደራጁ ወንጀሎች መሻሻል እንዲያሳዩ እና እንዲዳከሙ እና አደገኛ እንዳይሆኑ ተደርጓል፡፡
ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አለም አቀፍ የጠበቃዎች ማህበር ዘገባ ከዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የምስክርነት ደህንነት መከላከል እና አገልግሎቶች በICC በጀት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ነው፡፡ ይህ ታላቅ ማስተዋልን ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ግን ነገሮች ሁሉ በሂደት መታየት አለባቸው፡፡ የላይቤሪያ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቻርለስ ቴለር ረዥም የፍርድ ሂደት ሩብ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈጅቷል፡፡ ቴለር ለህግ ደጋፍ አግልግሎት በወር 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ይቀበላሉ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከፍርድ ቤቱ ጋር ያለው ርቀት እና በሁለቱም ወገን በኩል ያለው ባለአምስት ኮከብ የህግ ውክልና ሂደቱን በጣም ውድ አደረገው ማለትም በግምት በዓመት ከ35-40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያስወጣ ሆኗል፡፡ ለማጠቃለል ያህል  የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ታክስ ከፋዮች ገንዘብ 250 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ምናልባትም ከዚያ በላይ ይሆን ነበር ክሱ ወደ አቤቱታ የሚቀየር ከሆነ፡፡ ፍትህ ከምንም በላይ ታላቅ ዋጋ ያላት ሲሆን ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለህግ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ላም መሆን የለበትም፡፡ ወደ ሶስት ደርዘን የሚሞሉ ክሶች በICC ቅድመ ፍትህ ደረጃ ነበሩ፡፡ የቴለር የክስ ወጭን ፍራክሽንን በማየት የሁሉንም ተጠርጣሪ የክስ ሂደቶች ለማከናወን በጠቅላላ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ለህግ አገልግሎት የሚከፈል ገንዘብ እና ወጭ በተመሳሳይ መልኩ ለተቀነባበረ የምስክርነት ደህንነት መከላከያ መርሀ ግብር የማይውልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለስራው አስፈላጊ የሆነውን የገንዘብ መዋጭ ከሚያዋጡት ጀርመን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና ስፔን ጋር የምስክርነት ደህንነት መከላከያ መርሀ ግብርን እንዲሁም ጥገኝነት የማግኘት ዕድል የቦታ ዝውውር ድጋፍ እንዲያደርጉ አብሮ መስራት ይኖርበታል፡፡ ለምስክሮች እና ለቤተሰቦቻቸው አዲስ መታወቂያ እና ድጋፍ መሰጠት አለባቸው፣ ከዚህም ጋር የስራ የስራ ድጋፍ፣ የቤት እና የጤና ድጋፍ መደረግ አለበት፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአፍረካ ወሮበላ መሪዎች ወደ ዓለም አቀፍ የፍርድ ቤቶች ጠበቃ ማህበር ለማምጣት ምናልባትም ጠንካራ የምስክሮች ደህንነት መከላከል መርሀ ግበር ዋና ግብዓት ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ICC እንደ ተቋም ትንሽ የፍትህ ሂደት እና የተጠያቂነት የፍርሀት ደወል ድምጽ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ቢያሰማ አቅማቸው እና በሰው ልጆች ላይ ወንጀል ለመፈጸም ያለው ፍላጎት በእጅጉ ሊወገድ ይገባል፡፡
በአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ተመሳሳዮች በሰው ልጆች ላይ የሚፈጽሟቸውን ወንጀሎች ተገቢውን ዋጋ ከፍለው እውነት የምትወጣበትን መንገድ ለመቀየስ በአፍሪካ ጥቂት ምስክሮች ለዚሁ ተግባር ጀግኖች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለሰለባ የሚዳርጉ እስከሆኑ ድረስ ወደፊት የሚመጡበት ምክንያት የለም፡፡ ቢሆንም ጠንካራ የICC ምስክሮች መከላከል መርሀ ግብር ካለ የጥቃት ሰለባዎች እና ጥቂት ጥቃት ፈጻሚዎች ወደፊት በመምጣት ብዙሀንን በመግደል የሚፈጁት እና ማሰቃየቶች የሚፈጸሙት በአፍሪካ በህዝብ ቢሮ ከፍተኛ የስልጣን ቦታን የሚይዝ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያሉ የአፍሪካ መሪዎች ብዙ በሰው ልጆች ላይ ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ባለስልጣኖች በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ የሚቀልዱ ቢሆንም እነርሱን ደፍሮ የሚመሰክርባቸው አይኖርም በሚል አጉል እምነት በአገራቸው እንደሚኖሩ ይጠብቃሉ፡፡ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከኬንያታ የፍርድ ሂደት ጉዳይ ጠቃሚ ትምህርት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ፍትህ ዋጋው በግምት ሊለካ አይችልም ሆኖም ግን ፍትህን ለጥቃት ሰለባዎች እና ወንጀሎች ለሚፈጸሙባቸው ሰዎች በተቀነባበረ የምስክርነት መከላከያ መርሀ ግብር መቅረብ ያለበት አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ተለዋጭ አሰራር ደግሞ የማስመሰያ የፍርድ ቤት ክፍል ውስጥ በማድረግ ፍትህ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መድረክ ማቅረብ እና የፍርድ ቤቱን የኢፍትሀዊነት ትረካ “ድምጽ እና ጩኸት የበዛበት ምንም ነገር የማይፈይድ ነገር ነው፡፡”
የአፍሪካ ወሮበላ ዘራፊ መሪዎች የኬንያታን እና መሰሎቻቸውን ጥልቅ ትንፋሽ ከፍ እና ዝቅ በማድረግ እረፍት ማድረግ እንደሚፈልግ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለእነርሱ ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች የሞኞች ፍርድ ቤት ነው በሚል በጸጥታ ይስቃሉ፡፡ ለዚህም ነው ICCን ከዓለም አቀፍ ወንጀሎች እና ሸፍጠኞች ለማዳን በአፍሪካ ከፍተኛ ቢሮዎች ላይ መሰለፍ ያለብን፡፡


በሰው ልጆች ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች የተደራጁ ወንጀሎች ናቸው!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
መጋቢት 30 ቀን 2006 .

Link:-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11720/

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.