Sunday, August 24, 2014

መነሻ ገጽ - ዜና - በቅርስነት የተመዘገበ ሕንፃ በልማት ምክንያት እንዲፈርስ መታዘዙ ተቃውሞ አስነሳ

በቅርስነት የተመዘገበ ሕንፃ በልማት ምክንያት እንዲፈርስ መታዘዙ ተቃውሞ አስነሳ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘውንና በቅርስነት የተመዘገበውን ታዋቂው ሎምባርዲያ ሬስቶራንት ያለበትን ሕንፃ ጨምሮ፣ በ10.6 ሔክታር ላይ የሚገኙ ግንባታዎችን ለማፍረስ ለተነሺዎች የመጨረሻ
ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያው ባለፈው ዓርብ አብቅቷል፡፡ በተለይ የሕንፃው ባለቤት የሆነው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲና የሕንፃው ተከራዮች የአስተዳደሩን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡ 
ተቃውሞ አቅራቢዎቹ ሕንፃው በቅርስነት የተመዘገበ ሆኖ ሳለ እንዲፈርስ መወሰኑ አግባብ አይደለም እያሉ ነው፡፡ 
ሕንፃው በ1921 ዓ.ም. የተገነባ ሲሆን፣ ሕንፃውን የገነቡት የመናዊው ታዋቂ ነጋዴ ሼክ አህመድ ሳላህ አልዛህሪ ናቸው፡፡ ሕንፃው ከ85 ዓመታት በላይ ከማስቆጠሩም በተጨማሪ የሥነ ሕንፃ ቦርድ በቅርስነት አስመዝግቦታል፡፡ 
የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት በጻፈው ደብዳቤ፣ በተመሳሳይ በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የሼክ አህመድ ሳላህ ቤት በአዲሱ ማስተር ፕላን ላይ በቅርስነት እንዲመዘገብ መደረጉን አስታውቋል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪም የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሕንፃው በቅርስነት ስለመያዙ፣ እንዲሁም የሚመለከተው አካል ለቅርሱ ጥበቃ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ 
ነገር ግን የልደታ ክፍለ ከተማ፣ የከተማ ማደስና መሬት ባንክ ጽሕፈት ቤት ለዚህ ማሳሰቢያ ትኩረት እንዳልሰጠ ታውቋል፡፡ 
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ለምለም ገብረ ሚካኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕንፃው ቅርስ መባሉ አያሳምንም፡፡ ይልቁኑም በአካባቢው በሚካሄደው መልሶ ማልማት ከ40 እና ከ50 ፎቅ በላይ ከፍታ ያላቸው ሕንፃዎች ስለሚገነቡ መፍረሱ አግባብ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ግንባታዎች በማዕከላዊው የከተማው ክፍል ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች እንዲገነቡ በተያዘው ዕቅድ መሠረት የሚካሄዱ ናቸው፤›› ሲሉም አቶ ለምለም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚያካሂደው መልሶ ማልማት ከብዙ ቅርሶች መፍረስ በኋላ፣ ልማቱ ቅርሶችን ታሳቢ ባደረገ መንገድ እንዲከናወን በቅርቡ መመርያ ማስተላለፉ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን አሁንም የሚካሄዱ ልማቶች መንግሥት በቅርስነት ላስመዘገባቸው ግንባታዎች ትኩረት ገና አልሰጠም ሲሉ በርካታ ባለሙያዎች ይተቻሉ፡፡
የሕንፃው ባለቤት የነበሩት ሼክ አህመድ ሳላ አልዛህሪ በደቡብ የመን ረዳአ በተባለ ቦታ በ1873 ዓ.ም. ነው የተወለዱት፡፡ የአዲስ አበባ ፕሬስ በ1998 ዓ.ም. ባሳታመው የፊታውራሪ ተክለ ሃይማኖት ተክለ ማርያም ግለ ታሪክ፣ እንዲሁም ‹‹ከእንጦጦ ሐሙስ ገበያ እስከ መርካቶ›› በተሰኘ መጽሐፍ ላይ የሼክ አህመድ የሕይወት ታሪክ ተጽፏል፡፡ 
በመጽሐፉ እንደተገለጸው ሼክ አህመድ ታዋቂ ነጋዴ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ለኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች የጉምሩክ አስተላላፊነት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ያስተዳድሩ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ ለኢትዮጵያውያን አርበኞች ደጀን ነበሩ፡፡ 
ሕንፃው ሁለት ፎቅ ከፍታ ሲኖረው፣ ቀደም ሲል በሆስቴልነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለመኖርያነት፣ ለንግድና ለቢሮ አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ 
 Link:-http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.