Tuesday, September 30, 2014

አስደንጋጭና አሳፋሪ ምስጢር ሲገለጥ፡ Shocking!

አስደንጋጭና አሳፋሪ ምስጢር ሲገለጥ፡ Shocking!

Sept 21, 2014
በሴቭ አድና
ትላንት ሀይማኖተኛ፣ ፈሪሀ እግዚአብሄር የያዘና ጨዋ የነበረ ህዝብ እንዴት እንዲህ በሙስና፣ የንዋይ ፍቅርና በውሸት እንዲህ ረከሰ?
ባንድ ነገር መስማማት እንችላለን፡፡ የዛሬ አያድርገውና ህዝባችን ሙስናን፣ ስርቆትን፣ ውሸትን፣ ጭቆናን የሚፀየፍ፤ ተካፍሎ መብላትን እንጂ መስገብገብን የማይሆንለት፤ ክብሩን የጠበቀ፣ የሌላ መብትም የማይነካ ኩሩና በራስ መተማመን የተጎናፀና ከፍ ያለ የሞራል እሴቶች የነበሩት ነበር፣ ከአንድ ሁለት ዐስርት ዐመታት በፊት፡፡
አንዳንዶች ጥቂት አባባሎችን (ለምሳሌ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን የአማርኛ ምሳሌ) እያነሱ “ባህላችን ሙስና ያበረታታል” ለማለት ዳርዳር ቢሉም ማለት ይህ ከእውነታ የራቀ ነው፡፡
1. አንደኛ እንዲህ ዐይነቶቹ የስልጣን መባለግን የሚያበረታቱ አባባሎችና አስተሳሰቦች ኢምንቶች ናቸው፤ ከእነዚህ በአስርና ሀያ እጠፍ የበዙ ይህ ዐይነቱ የስነ-ምግባር ዝቅጠት የሚኮንኑ በመቶና በሺህ የሚቆጠሩ ጠንካራ ምሳሌዎች አሉን፤
ደግሞም እንዲህ ዐይነት አባባሎች በአንድና ሁለት ቋንቋዎች ላይ እንጂ ሀገሪቱን አይወክሉም፡፡ ለምሳሌ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በበርካታ ሌሎች የሀገራችን ቋንቋዎች እምብዛም አይገኙም ወይም ጨርሰው የሉም፡፡ ይሀንን የሚያወግዝ ግን በገፍ አለ፡፡ ይሁን እንጂ ያሁኑ የስነምግባር ዝቅጠት በተለይም ሙስና ግን በሀገሪቱ ከጫፍ እስከጫፍ፣ በሁሉም ህዝቦች አለ፡፡
አዎ ትላንት ህዝባችን ሀይማኖተኛ፣ ፈሪሀ እግዚአብሄር/አላህ የበዛው፣ ለሐቅና ለርትዕ የሚቆም፣ ውሸትና ስርቆት የሚፀየፍ ነበር፤ አሁን ያ በብርሀን ፍጥነት እየጠፋ ነው- በዋናነት በአንድ ሰው/ቡድን ጊዜያዊ ፓለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ታስቦበት የተጠነሰሰ ሴራ ምክንያት!
ነገሩ እንዲህ ነው፤
ከ1993 ዐ.ም የህ.ወ.ሐ.ት ክፍፍል በኃላ በተፈጠረው መንገዳገድ ምክንያት ይሀንን አደጋ በዘለቄታ ለማስቀረት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በመሪውና የአሸናፊው ጎራ መሪ መሐንዲስነት አንድ እቅድ አወጣ፤
“ሰዉን ሁሉ ማኖ በማስነካት፣ እንዲሰርቅና በሌላ ወንጀል ኢንዲነከር በማድረግ አካሉም መንፈሱም መቆጣጠር”
ቀላል ስሌት ነበር፤ የመጀመርያዋን ሂድ የምትል ጥይት እንዴ ከተተኮሰች ቀሪው በራሱ መንገድ ይቀጥላል ነው፡፡ እናም ሰውየው ለቧለሟሎቻቸው ለራሳችሁ አትስነፉ፣ ነገ እንድ ነገር ብትሆኑ ሆር ብሎ የሚያያችሁ የለም፤ ከእነ ገብሩ አስራት መማር አለባችሁ የሚል ውስጠ ወይራ ያዘለ መልእክት እንዳስተላለፉላቸው ይነገራል፡፡ በፓርላማው ጭምር ሙስና ከተያዙ ወንጀል ነው ፤ ካልተያዙ ስራ ነው ማለታቸውስ እንዴት ይረሳል? “እንኳን እናቴ ሙታ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል” እንዲሉ ሊበላ አሰፍስፎ ለሚጠብቅ ባለስልጣን ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ አይከብደውም፡፡
ስሌቱ ሁለት ጥቅሞች እንዲሚያስገኝ ታምኖበታል፡፡
1. አንድ ሰው በዚሁ ሁኔታ እጁ ከቆሸሸና በሙስና ከተጨማለቀ ይህንን ወንጀል እንደማስያዣና ማስፈራሪያ በመጠቀም የወደፊት ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙሙት ፈረስ ታማኝ ታዛዥ ማድረግ፤
አቶ አበበ አንድ ሁለት መቶ ሚልዮን ሰረቀ እንበል፡፡ ብዙ ድርጅቶችም ከፍቷል፡፡ ብዙ የሙስና ኔትዎርክ ዘርግቷል፡፡ ይሀንን አቶ መለስ በደምብ ያውቃሉ፡፡ ዝርዝር መረጃ አላቸው፡፡ ምናልባትም አቶ አበበን በተመለከተ በ10፣ 15 ገፅ የተጠቃለለ መረጃ አላቸው፡፡ ይህ ሰው እየሰረቀ ታዛዥነቱ አጥብቆ ከቀጠለ ይሀንን አያነሱለትም፡፡ ይህ ውድ ልጅ ነው፡፡ አቶ አበበ አንድ ቀን የጥጋብ ወይም ትእቢት ምልክት፣ የሐሳብ ተቃርኖ…ወ.ዘ.ተ ያሳየ ቀን ወደ ቤተምንግስት ይጠራል፡፡
“አቶ አበበ፤ ሰላም፡ ግባ፤ ቁጭ በል፤ አቶ አበበ፤ መቸም አንተ ጠንካራና ታማኝ ሰራተኛችን ሁነህ ዘልቀሀል፡፡ እንደዛም ሁኖ ግን እጅህ በብዙ ሙስናና ደም እንደተጨማለቀ እናውቃለን፤ መቸም የኛ ሰው ስለሆንክና ጠንካራና ታማኝ ሰራተኛ ስለሆንክ ነው ዝም የምንልህ እንጂ ሳናውቀው ቀርተን አይደለም፤ ደግሞም ከዛሬ ነገ ትለወጣለህ የሚል እምነታችን የፀና ነበር”:: ከዚያ ደብተሯ ትወጣለች፡፡ “ይኸው፤ በዚህ ቀን እንዲህ አድርገሀል፤ እዚህ ቦታ ባለ 9 ፎቅ ህንፃ ገንብተሀል፣ እንትን ሪልስቴትም 60 % ሸር ያንተ እንደሆነ እናውቃለን፤ በእህትህ ስምም 70 ሚልዮን የሚገመት ድርጅት ከፍተሐል….” ደብተሯ ትታጠፋለች፡፡ አበበ ሽብር በሽብር፣ ላብ በላብ ይሆናል፡፡ መሬቷ አፏ ከፍታ ብትውጠው በወደደ፡፡ “ካሁን ካሁን ከጀርባየ መጥተው አፈፍ አድርገው ወሰዱኝ” እያለ ሲያስብ “አይዞህ፤ አትፍራ፡፡ እኛ ይሀንን ሁሉ ከመጀመርያው ጀምረን እናውቅ ነበር፡፡ አሁን ወደ ቤትህ ሂድ፤ አትጨነቅ፤ ምንም አትሆንም፡፡ ብቻ ስራህን በርትተህ ስራ፣ ለስርዐቱ ያለህን ታማኝነትህና አገልጋየነት ግን እንዳታጎድል፤ ያኔ ከፍ ያለ ችግር ይከተልብሀል፡፡”
ይህ ሰው ከዚህ በኃላ ባርያ ከመሆን ውጪ ምን አማራጭ አለው? በእርግጥ እንደነ ጁነዲንና ኤርምያስ ያለም የያዘውን ይዞ፣ የበላውን በልቶ አጋጣሚውን ሲያገኝ ሽል የሚልና ወጥቶ ብፁዕ ወቅዱስ እንደነበረ የሚሰብክም አለ፡፡
2. በዚሁ ሁኔታ ከማህበረሰቡና ከህዝቡ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባ ሰው ወደፊት እንጂ ወደ ኃላ ዞር ብሎ ማየት አይችልም፡፡ ጀርባ የቆሸሸ ነዋ፡፡ ይህ ሰው ከመንግስት ጋር ቢጣላ እንኳ መንግስት ላይ ችግር የመፍጠርና ሆነ ሌላ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችል አይሆንም፡፡ እናም እየሰረቀ ህሊናውን ሸጦ ከመኖር ሌላ አማራጭ የለውም፡፡
በነዚህ የጥቅም ስሌቶች የተመራው ባለስልጣን ሁሉ ሙሰኛና የተገዛ የማድረግ ዘመቻ እርሳቸውም ካሰቡት በላይ በፍጥነት መንሰራፋቱ ይነገራል፡፡ እላይ አንድ ሁለት ብሎ የተጀመረ ሙስና ዛሬ በየቤታችን በየጓዳችን የምታንኳኳ የየዕለት ክስተታችን ናት፡፡
በአንድ ሁለት ሰው ስሌት አንድ ሀገር፣ 90 ሚልዮን ህዝብ ሙሰኛ ይሆናል ብሎ መጠበቅም ቢከብድ የሆነው ግን ይህ ነው፡፡ ይሀንን በተወሰነ የሚያበረታታ አለማዊ ሁኔታና ግፊትም እንደነበረ ግን የሚካድ አይሆንም- ሚናው ትንሽም ቢሆን፡፡
ዞሮ ዞሮ ስርዓቱን ለማጠናከርና ሰዎች ሆዳቸውንና ህሊናቸውን ለመቆጣጠር ታስቦበት የተስፋፋው ሙስና እራሱን ስርዐቱንም ማንኮሻኮሽና የስርዐቱን ህልውና የሚፈታተንበት ደረጃ ደርሷል፡፡አሁን ሙሰኞቹም ፍፁም ፈርጥመው ለሁሉም አደጋ ሆነዋል፡፡እንግዲህ በቆፈሩት ጉድጓድ….እንደሚባለው ነው፡፡
“ትልቅ ነበርን፣ ትልቅም እንሆናለን!” ይህ እንዲሆን ግን ችግሮቻችንን እንወቅ፣ መነሻቸውን እንመርምር፣ ጥልቀታቸውን እንረዳ፤ ከዚያም ወደ መፍትሔው እንሂድ፡፡ አበቃሁ፡፡
Link:-http://abbaymedia.com/amharic/2014/09/21/አስደንጋጭና-አሳፋሪ-ምስጢር-ሲገለጥ፡-shocking/

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.