Tuesday, November 4, 2014

የተረገዘው እንዲወለድ



የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል አይፈልግም የሚለው ጥያቄ አከራካሪ አይመስለኝም። ፌስ ቡክ ተጠቃሚውን ብቻ አይቶ የህዝቡን ፍላጎት መረዳት ይቻላል። ተመራማሪዎች በአንድ አገር ያለውን የህዝብ ስሜት ለማወቅ እስከ 2 ሺ የሚደርሱ ሰዎችን አነጋግረው ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ። እኔም ካሉኝ 5 ሺ የፌስቡክ ጓደኞች መካከል ፣ ፖለቲካን ከሚከታሉት ውስጥ ማለቴ ነው፣ ከ90 በመቶ በላይ ለውጥ ፈላጊዎች ናቸው። ሁሉም ፌስቡከር ተመሳሳይ ናሙና ወስዶ ጥናት ሊያካሂድ ይችላል። እጅግ የሚበዛው ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ለውጡ በምን መንገድ ይሁን- በአብዮት ወይስ በዘገምተኛ ለውጥ፣ በትጥቅ ትግል ወይስ በሰላማዊ ትግል- ሰላማዊ ትግል ሲባልስ- በህዝባዊ አመጽ ወይስ በየ5 አመቱ በሚደረግ ምርጫ በሚለው ላይ የአሃዝ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ስርዓቱ እንዲለወጥ በመፈለግ በኩል ግን ካላጋነንኩ 5 በመቶ ከሚሆኑት ባለስልጣኖችና ተጠቃሚዎች በስተቀር እጅግ አብዛኛው ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ባለፉት 4 ዓመታት ካነጋገርኳቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተነስቼ ከማንም በላይ በቅድሚያ ለውጥ ፈላጊው በመካከለኛ ደረጃ ያለውና ተራው ወታደር መሆኑን መመስከር እችላለሁ። ስሜቱን የሚገልጽበት መድረክ ስላላገኘ እንጅ ወታደሩ ትንሽ ነገር የሚጠብቅ ፣ በቋፍ ላይ ያለ፣ ለለውጥ ዝግጁ የሆነ ሃይል ነው።

አብዛኛው ህዝብ ለውጥ ፈላጊ እስከሆነ ድረስ ለውጥ አይቀርም። ጭቆናም እስካለ ድረስ አመጽ አይቀሬ ነው ። በኢትዮጵያ የሚመጣው የስርዓት ለውጥ ህዝባዊ አመጽና ሃይልን ያማከለ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። የሃይል አማራጩ እየተጠናከረ ሲመጣ፣ የሲቪሉም የለውጥ እንቅስቃሴ እየጎለበተ ይመጣል፣ ወይም በተቃራኒው። ብዙዎች ሁለቱን ሃይሎች ተጻራሪ አድርገው ይመለከቷቸዋል። የሃይል አማራጭ መኖር ህዝባዊ አመጽን ወይም ሰላማዊ ትግልን ያዳክማል ብለው ይሰጋሉ። ለእኔ ደግሞ ህዝባዊ አመጽና የሃይል አማራጭ ተደጋጋፊ እንጅ ተጻራሪ ሃይሎች አይደሉም። የተቃዋሚዎች የሃይል ትግል ሲጠናከር፣ የገዢው ሃይል እየተዳከመ ይሄዳል። የገዢው ሃይል ሲዳከም ደግሞ ህዝባዊ አመጸኞች የልብ ልብ ይሰማቸውና ህዝባዊ አመጻቸውን ይቀጥላሉ። ሃይል ያላቸው ወገኖች ህዝባዊ አመጽ ለሚያካሂዱት ሽፋን ከመስጠት አልፎ፣ ድምር ሃይል ስለሚፈጥሩ የገዢውን ፓርቲ ሃይል ለመቋቋም በሂደትም ለማሸነፍ ያስችላቸዋል። የተደራጀ የሃይል አማራጭ መኖሩ በህዝባዊ አመጽ ለሚነሳ የስልጣን ክፍተት ( power-vacuum) መሙያ ይሆናል፤ የገዢው ፓርቲ ተማኝ ወታደሮች የስልጣን ክፍተቱን ተጠቅመው በአመጸኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቢነሱ ወይም ለዘረፋ ቢነሱ ወይም ቢሸፍቱ ወዘተ አዲሶቹ ሃይሎች ማስታገሻ ኪኒን ይሰጧቸዋል። ህዝቡ የስልጣን ክፍተት እንደማይኖር ዋስትና ካገኘ ደግሞ ህዝባዊ አመጹን በሙሉ ልብ ለማካሄድ ያስችለዋል። የስልጣን ክፍተት ይፈጠራል ብሎ የሚሰጋ ሃይል ስለማይኖር ለውጥ ፈላጊው በአንድ ልብ ሊነሳ ይችላል።

ሁለቱ ሃይሎች ተደጋግፈው ይቀጥሉ ዘንድ አንድ ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ አለበት ። ህዝባዊ አመጸኞችም ሆኑ የሃይል አማራጭ አቀንቃኞች፣ የሲቪል አስተዳደርና ዲሞክራሲ ለመመስረት የወሰኑና ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ ለመከተል ፈቃደኞች ያልሆኑ መሆን አለባቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከተስማሙ ( በሃሳብ ማለቴ ነው) ትግሉ ፈር ይዞ ይቀጥላል። ህዝባዊ አመጸኞች በህዝብ ድምጽ ለሚመጣ ስልጣን ሲታገሉ ፣ ነፍጥ ያነገቱት በተቃራኒው በመሳሪያ ለሚመጣ ስልጣን የሚታገሉ ከሆነ ፣ አንዱ የሌላው ተቀናቃኝ እንጅ ደጋፊ ወዳጅ ሊሆን አይችልም፤ ድምር ሃይል ስለማይፈጥሩም አያሸንፉም፣ ቢያሸንፉም እንኳ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማካሄድ አይችሉም። ስለዚህም ነው፣ ዲሞክራሲን ለመገንባት ቁርባን የወሰደ ታጣቂ ሃይል ግድ የሚለው። ይህ ሃይል ከዲሞክራሲ ውጭ ሌላ አይዲዮሎጂ ወይም ሌላ የሚታገልለት አላማ ሊኖረው አይገባም። እንዲህ አይነት ግልጽ አላማ ይዞ የተነሳ ታጣቂ ሃይል ካለ ፣ ለህዝባዊ አመጽ ትግሉ ደጋፊ ሃይል እንጅ ተጻራሪ ሃይል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም።
ታጣቂ ሃይሎች ከነፍጥ ባሻገር የዲሞክራሲን ዝናር መታጠቅ ግድ እንደሚላቸው ሁሉ ፣ ህዝባዊ አመጸኞችም ሊታጠቋቸው የሚገቡ ዝናሮች አሉ። ሁሉም ህዝባዊ አመጸኞች የትግሉ ዋና አላማ ስልጣን ከህዝብ ፍላጎት የሚነጭ መሆኑን አምነው መቀበል፣ ከዚህ ውጭ የሚመጣ ነገር ሁሉ ተቀባይነት የማይኖረው መሆኑን አምነው መቀበል ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱም መስራት አለባቸው። ስምምነቱንም አመጹን ከመጀመራቸው በፊት ማካሄድ አለባቸው። ህዝቡም ይህን ማድረጋቸውን ማረጋጋጥ አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ ከተስማሙ ገዢዎች ሊከፋፍሉዋቸው፣ በስልጣን ወይም በገንዘብ ደልለው ከዋና መስመራቸው ሊያስወጡዋቸው አይችሉም። የተረገዘው ለውጥም ቀኑን ጠብቆ ይወለዳል።

kFasil Yenealem

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.