በአብዛኛው በወጣት ወንዶችና ሴቶች የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነበት የዘጠኝ ፓርቲዎች ኅበረት፣ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” የተሰኘ የአንድ ወር መርሀ ግብር አውጥቶ፤ ችግሮችን ተጋፍጦ አብዛኛውን ተግባራዊ አድርጓል። የመርሀ ግብሩ አቢይ አካል የነበረውና በህዳር 27 እና 28 ሊከናወን ታድቆ የነበረው የ24 ሰዓት የአደባባይ ተቃውሞ ግን በአገዛዙ የኃይል እርምጃ ምክንያት በታቀደው መንገድ ሊከናውን አልቻለም። የህወሓት ቅልብ የሆኑት ሲቪል የለበሱ ሰላዮችና የፌደራል ፓሊስ በተቃውሞው ተሳታፊዎች ላይ ኢሰብዓዊ የሆነ ጥቃት ፈጽመዋል።
ከጅምሩ፣ የፓርቲዎቹ ኅበረት የተቃውሞ ማሳወቂያ ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማስገባት የገጠመው ችግር የህወሓት አገዛዝ የመንግሥትን መዋቅር ለፓርቲ ሥራ፤ የመንግሥት ተቀጣሪዎችን ደግሞ እንደ ህወሓት አገልጋዮች የሚጠቀምባቸው መሆኑ አንዱ ማሳያ ሆኗል። ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ማሳወቅ የፈለጉት ፓርቲዎች ህወሓት የዘረጋውን አፋኝ ሥርዓት የሚታገሉ በመሆናቸው ብቻ ደብዳቤዓቸውን የሚቀበል እንኳን አጥተው ተጉላልተዋል። ለሰልፉ ቅስቀሳ ማድረግም በራሱ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ወጣቶች ተንገላተዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። ያም ሆኖ ውጣ ውረዶች ታልፈው ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ. ም. ደረሰ።
የኅበረቱ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ጥሪውን የሰማ ሕዝብ ወደ መስቀል አደባባይ ማምራት ሲጀምር ሲቪል የለበሱ የአገዛዙ ታጣቂዎች እና ፌደራል ፓሊሶች ከሰንደቅ ዓላማዎችና መፈክሮች ባለፈ አንዳች ነገር ያልያዙትን እድሜያቸው ከሃያዎች ያልዘለሉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን ደብድበዋል፤ ብዙዎቹም አፍነው በአሰቃቂ ሁኔታ እያንገላቱ ወደ እስር ቤቶች ወስደዋል። ወጣቶች ተወልደው ባደጉበት አገር፤ ስሜታቸውን በነፃነት ለመግለጽ በመድፈራቸው ብቻ በጭካኔ ተረግጠዋል፤ ተፈንክተዋል፤ እጅና እግሮቻቸው ተሰብሯል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህ የህወሓትን ፋሺስታዊ እርምጃ አጥብቆ ይቃወማል። ግንቦት 7፣ ህወሓት ከስልጣን እስካልተወገደ ድረስ እንዲህ ዓይነቱን ፋሺስታዊ ተግባር መፈፀሙን የማይተው እኩይ ኃይል እንደሆነ ያውቃል፤ በዚህም ምክንያት የትግላችን ግብ ህወሓትን ማስወገድና በምትኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት መመሥረት መሆን ይኖርበታል ብሎ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።
ግንቦት 7፣ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. “መብቶቻችንን በህወሓት ዘረኛ አምባገነኖች አናስነጥቅም” በማለት አደባባይ የወጡ ወጣቶችን ጽናት ያደንቃል። ህወሓት የሚለውን ሳይሆን የይስሙላ ህጉ የፈቀደላቸውን ለማድረግ በመድፈራቸው በህወሓት የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚደረገውን ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት አራምደውታል።
እያንዳንዱ የፓለቲካ ድርጅት ከዚህ ኩነት የሚወስዳቸው ተጨማሪ ትምህርቶች ቢኖሩም የሚከተሉትን ነጥቦች ብዙዎችን ያስማማሉ ብለን እናምናለን።
1. ህወሓት በምንም ዓይነት ቢሆን የያዘውን ስልጣን ለሕዝብ ፈቃድ ማስገዛት አይፈልግም፤
2. ህወሓት አገራችን ወደ ትርምስ እየገፋት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤
ከህወሓት አገዛዝ መገላገል የሚቻለው ተገዶ ሲወገድ ብቻ ነው። ህወሓት እንዲወገድ ደግሞ የመጨቆኛ አቅሙ መዳከም ይኖርበታል። ህወሓትን የማስወገጃ አማራጭ መንገዶች ብዙ ሲሆኑ ተቀናጅተው ቢሠሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ ብለን እናምናለን፤ “ሁለገብ ትግል” የምንለው የትግል ስልት ጭብጥ ይህ ነው። “እምቢ ለነፃነቴ” ብሎ የተነሳ ሕዝብ ህወሓትን ምን ያህል እንደሚያስደነግጥ በተደጋጋሚ ታይቷል። ህዳር 27ን መንደርደሪያ አድርገን በመውሰድ ከዚህ በተሻለ ለተደራጀ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና አመጽ ራሳችን እናዘጋጅ።
በዚህ አጋጣሚ ግንቦት 7፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ፓሊስ አባላት ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ማድረግ ይሻል። የመከላከያ ሠራዊት እና ፓሊስ አባላት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በህወሓት ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ የተበደላችሁ መሆኑን እናውቃለን። የህወሓት ሹማምንት ከሆኑ አዛዦቻችሁ መላቀቅና ራሳችሁን ነፃ የማውጣት ኃላፊነት የወደቀው በእናንተው በራሳችሁ ላይ ነው። ሠራዊቱ ራሱን በራሱ ነፃ ማውጣት ይኖርበታል። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ህወሓት መወገዱ የማይቀር በመሆኑ ሠራዊቱ ራሱን ነፃ አውጥቶ ከሕዝብ ጋር ካልወገደ እጣ ፈንታው የተሸነፈ ሠራዊት መሆን ነው። ከዚህ በላይ የሠራዊቱ አባል እየደበደበ ያለው የራሱን ልጅ፣ ወንድሙን ወይም እህቱን እንደሆነ ይወቅ። ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው እያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል በግል ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ሊሰማው ይገባል።
በሁሉም ዓይነት የትግል ዘርፎች የኢትዮጵያ ወጣቶች በስፋት እየተቀላቀሉ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው። ጊዜው የለውጥ ነው። የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተደጋግፈው እንዲሄዱ መደረግ ያለበት ወቅት ላይ ነን። በህዳር 27 ቀን በህወሓት ቅልብ ሰላዮችና የፌደራል ፓሊሶች አማካይነት የደረሰው ጉዳትና የፈሰሰው ደም ለፍትህና ለነፃነት የተከፈለ ዋጋ ነው። ህመማችሁ ህመማችን፤ ትግላችሁ ትግላችን ነው። የተለያዩ መንገዶች ወደ ነፃነት አደባባይ እያመሩ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.