January 1, 2015
ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ(ህወሃት)የተመሠረተበትን አርባኛ ዓመት ለማክበር ሽር ጉድ እየተባለ ባለበትና በመጠኑ ከፍተኛ የሆነ የሀገሪቱ የገንዘብ ወጭ ተደርጎ አስረሽ ምችው የሚደለቅበት ሰአት ላይ ያለን ሲሆን የዘድሮው በዓል አከባበር ደግሞ የተለየ ሆኗል አስቀድመው ነው የጀመሩት ያም ሆነ ይህ በዓሉ ለምን ይከበራል? የሚያከብረውስ ማን ነው? ብለን ስንጠይቅ ድርጅቱ በጫካ አሥራ ሰባት ዓመት በትረ ሥልጣኑን ከጨበጠ በኋላ በከተሞች ለሃያ ሦሥት ዓመታት ያህል የምሥረታ በዓሉን በከፍተ የገንዘብ ወጭ እያከበረ ዘልቋል።በዓሉ የሚከበርበት ምክንያት፦ ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳበት ዓላማ ግቡን እየመታ በመምጣቱ፤ከዚህ ግቡ የማይባሉ ሰዎችን ለሀገር ሥልጣን በማብቃቱ፤ጥቂቶቹን ሚሊየነር በማድረጉ፤የድርጅቱን ዓላማ የሚቃወሙትን እያወደመና እየበላ በመምጣቱ፤ ከሀገር እንዲሰደዱ በማድረጉ እንዲሁም አሰቃቂና ጭካኔ በተሞላበት ድብደባና እንግልት በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ፤ጋዜጠኞች፤ጦማርያን፤የሃይማኖት መሪዎች፤ተማሪዎች፤አስተማሪዎች፤ነጋዴዎች፤አርሶ አደሮች ወህኒ ቤት ወርደው እንደ ብረት እየተቀጠቀጡ የሚገኙበት፤የሀገር ሀብት ተንጠፍጥፎ ካዝናው ባዶ እስኪሆን ድረስ ተጠርጎ ወደ ውጭ አገር ተልኮ በጥቂት ባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸው የግል ባንክ አካውንት በመቀመጡ፤ከአጎራባች አገሮች ጋር የሚዋሰነው የኢትዮጵያ ለም መሬት በገፀ-በረከትነት የኢትዮጵያ ጠላት ለሆኑ አገሮች በመሰጠቱ፤በኢንቭስት-መንት ስም ነዋሪው ኢትዮጵያዊ ዜጋ እየተፈናቀለ መሬት ለውጭ ባለሀብት ያለምንም ክፍያ በመሰጠቱ፤የንግዱም ሆነ የግብርናው ዘርፍ ሕዝብ የማይሳተፍበትና በባለሥልጣናት እጅ የገባበት፤አገሪቱ ወደብ አልባ የሆነችበት፤አንድነት የጠፋበትና ለዘመናት አብረው በሰላምና በፍቅር በአንድነት የኖሩ ነገደ ኢትዮጵያውያን በጥርጣሬና በጥላቻ የሚተያዩበት ሁኔታ በመፈጠሩ፤ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ የተረገጠበት ላይ በመድረሱ ህወሃትና ጋሻ ጃጌዎችን የሚያስደስት ተግባር ከዚህ በላይ ስለማይኖር በዓሉ ይከበራል።
ይህን የህወሃት በዓል የሚያከብረው ማን ነው?የህወሃት አባላት፤አመራርና ጋሻ-ጃግሬዎች ምስኪኑን ሕዝብ በቀጭን ትዕዛዝ በኃይል ተገዶ እንዲወጣ በማድረግ ሲሆን እምብኝ አልወጣም በዓሉ የኔ በዓል አይደለም ያለውን ደግሞ በታጠቀ ኃይል በመሣሪያ ጀርባውን፤ግንባሩን በጠመንጃ አፈሙዝ እየተገጨ እንዲወጣ በማስገደድ ነው በዓሉን የሚያከብሩት።ከህወሃት አምባገነናዊ ባህርይ መልካም ነገር የማይታሰብ ቢሆንም ህወሃት ለተነሳበት እኩይ ዓላማ ፀንቶ የቆመ በመሆኑ በዓሉን አታክብር ማለት የዋህ የሚያስብል ይሆናል።ነገር ግን ይህን ጠባብና ዘረኛ ሥርዓት ማስወገድ አለብኝ የሚሉ ኃይሎች በዓላማቸው ፀንተው አንድነት ፈጥረው ትግል አለማካሄዳቸው ህወሃትን ለዚህ ያበቃው መሆኑን ግልጽ አድርጌ ማለፍ እወዳለሁ።ሕዝቡ በቃኝ ካለ ሰንብቷል፤ አመጽ ያረገዘ ሕዝብ ከየአቅጣጫው እየሰነዘረ ያለው ርምጃ የተቃዋሚ ኃይሎችን የሕዝቡ ትግልና አመጽ ጭራ አድርጓቸው እየታየ ነው።ስለዚህ የተቃዋሚ ኃይሎች (ድርጅቶች)ሕዝብ እየሄደበት ባለው ፍጥነት በመሄድ የማደራጀት ተግባር መቅደም አለበት ብየ አምናለሁ ወይም ይጠበቅባቸዋል።ይህ የሚያግባባን ከሆነ መነሻ ወደ አደረኩት ርእሴ ተመልሸ ከበረከት ስምኦን (መብርሃቱ ገ/እግዚአብሔር) የደደቢት ድስኩር በጽሁፍም ሆነ በቪዲዮ ክሊፕ ከተመለከትኩት ትዝብት በትንሹ ጨልፌ ላካፍላችሁ ወደድኩ።
1ኛ/ በረከት ወይም መብርሃቱ ያ! ትውልድ ከሚባሉት አንዱ ሲሆን ኢህአፓ ከተመሠረተ በኋላ ትግሉን የተቀላቀለ የወቅቱ ወጣት ታጋይ ነበር በረከት ወንድምና እህቶቹ በመላኩ ተፈራ የተገደሉ ሲሆን አንዱ ወንድሙ ካሣሁን ደግሞ በህወሃትና ኢህአፓ በተደረገ ጦርነት በህወሃት ተገድሏል። በዚህ ምክንያት በረከት በደርግና በህወሃት የመረረ ጥላቻ በልቡ ውስጥ አስቀምጦ በኢህአፓ ታጋይነቱ ቀጥሏል።በኋላ ላይ ግን የበለሳው ወይም ሪጅን 3 እየተባለ የሚታወቀው ክንፍ ከኢህአፓ አፈንግጦ(አንጃ ፈጥሮ) ወደ ትግራይ ሲያመራ (ሲንቀሳቀስ) 120 የሚጠጋ የሰው ኃይል ውስጥ በረከት አንዱ ነበር።ያሁሉ ሰው በየምክንያቱ እየሾለከ ሲጠፋ ከቀሩት 37 ሰዎች መሀል በረከት አልተለየም ነበር።
2ኛ/በረከት ወደ ትግራይ ሲሄድ ከህወሃት ጋር በመተባበር ደርግን ጥሎ ሥልጣን ለመያዝና የዛሬው ፈላጭ ቆራጫችን ሊሆን እንደሚችል አስቦት ነበር ወይ?ሲባል ሊሆን እንደማይችል ብዙ ማስያዎች ነበሩ። ህወሃት ከበለሳ የሄደውን ቡድን ኢህዲን ብሎ ስም ለጥፎ የራሱ መሣርያ ሲያደርገውና ወደ ወሎ ከአንድ የህወሃት ብርጌድ ትንታግ ሠራዊት ጋር ሲመለሱና በ1973 ዓ/ም ህዳር ወር ላይ መስራች ጉባኤ ተካሂዶ የማዕከላዊ ኮሚቴ ተመርጦ እንቅስቃሴ ሲጀመር በረከት ከህወሃት መዳፍ ሥር ገብቻለሁ ብሎ አላመነም ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የኢህዲን ሊቀመንበር ጌታቸው ጀቤሳ(ያሬድ ጥበቡ)እና በመለስ ዜናዊ መሀከል የጌታና የሎሌ አይነት ባርይ ማስተናገድ ያልፈለገው ጌታቸው በአቋሙ ሲገፋ**ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም** እንዲሉ ጌታቸውን ገፋፍተው በማስወገድ ታምራት ላይኔን(አሰፋ ማሞን)በሊቀመንበርነት በማስመረጥ ህወሃት እንዳሻው የሚያሽከረክረው ኢህዲን ጌታቸውን የውጭ የዲፕሎማሲ ሥራ ወኪል በማድረግ ወደ ውጭ ላከ።ጌታቸው በአጭር ጊዜ ብዙ የመታገያ ጎራው እንደ ጉም ሊጨበጣቸው ያልቻሉትን ለማፍራት ቻለ።ነገር ግን እነዚህ ከኢህዲን ጋር በመሆን ለመታገል የተነሱና ኢህዲንን ሳይገናኙ ቀሩ ዋናው ምክንያት ሾፋሪው ህወሃት ስለነበር እንዚያ ሰዎች ኢህዲንን ሲቀላቀሉ ህወሃት የሚገጥመውን ስለሚያውቅ ኢህዲን ወደ ውጭ ለመውጣትም ሆነ ወደ ውስጥ ለመግባት መስመሩን የዘረጋው ህወሃት ስለነበር ህወሃት የጌታቸውን መልእክት እየጠለፈ በማስቀመጥ የግንኙነቱን በር ዘጋው።በዚህ ምክንያት በህወሃትና ኢህዲን እንዲሁም በኢህዲን በራሱ በተለያየ ቦታ የመከፋፈል ችግር ነገሰ አንዱ ጎራ የጌታቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የታምራት ሆነ።ሦስተኛው ወገን መሃል ሰፋሪና ደርግን ናፋቂም ነበረበት እንደ አዲሱ ለገሰ የመሰሉ ደግሞ ወደ ኢህአፓ ያቀኑም ነበሩ። በዚህ ጊዜ ነበር በረከት ከጌታቸው ወገን በመሆን ህወሃትን ሲያወግዝ የነበረው**ስንት ጊዜ ነው የህወሃት ሸሚዝ ሆነን የምኖረው በማለት የራሱ መሪ ቃል ፈጥሮ ህወሃትን በስፋት ይቃወም ነበር ነገር ግን ያ የበረከት ሃሳብ ተቀለበሰና በረከትን ዛሬ ላይ ሆነን እንመልከተው።**
3ኛ/ በረከት መቼ ነው ቅራኔውን አስወግዶ ከህወሃት ጋር መታገል የጀመረው?አዲሱ ለገሰ፤ተፈራ ዋልዋ፤ታምራት ላይኔ ትግራይ ሄደው በህወሃት የካድሬ ማሰልጠኛ ማእከል ገብተው የካድሬነት ክህነቱን ተጠምቀው ከወጡ በኋላ ኢህዲን የህወሃትን ፍላጎት ከማስፈጸም ወጭ እንደ አንድ ህብረ-ብሄራዊ ድርጅት መቆም አልቻለም።ውሎ አድሮ ደግሞ ኢህአዲግ በሚል የጋራ ግንባር ሥር ገብቶ ወደቀ መጥፎ ቀን የኢህዲን ታጋይ ባመናቸው መሮዎቹ ሊወጣ ከማይችልበት እሥር ቤት ገብቶ የህወሃት ጥቅም አስጠባቂ ሆነ።እነዚህ ከላይ ስማቸውን የጠቀስኳቸው ግለሰቦች የታገሉት የአማራው ነገድ ሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ ሲሆን አማራ ስለአልሆኑ ኃላፊነት በጎደለው መንፈስ የአማራውን ነገድ ሕዝብና አብሯቸው ይታገል የነበረውን ትውልደ አማራ እየበሉና እያስበሉ የመጡ የእናት ጡት ነካሾች ናቸው።ይህ አይነት የግድያ ተግባር በደርግ ጊዜ የተጀመረ ብቻ ሳይሆን ደርግ ከወደቀ በኋላም ተጠናክሮ ቀጥሏል።የመጀመርያው ዘመቻ አማራውን ማስወገድ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በኦሮሞው ላይ ይሆናል።የዚህን ጅማሮ እየተመለከትነው ነው።
4ኛ/ ህወሃት አንድ የሚመፃደቅበት አንድ ትራጀዲ አለ እሱም የብሄር ብሄረስቦችን መብት አረጋግጫለሁ የብሄር ብሄረሰቦች ምክር ቤት አቋቁሜ ያለሁ የሚለው ፈሊጥ ነው።እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብና ጐሣ ወይም ነገድ ሕዝብ በሰላም ውሎ እንዳያድር የዲሞክራሲና የፍትህ፤የእድገት፤የእምነት ጥያቄዎችን እንዳያነሳ እርስ በርስ እያናከሳቸው ይገኛል።በአጭሩ ለማሳየትም ሁለት ምሳሌዎችን ልጥቀስ በኢትዮጵያ ሶማሌና አፋር ክልል ግጭት ተፈጠረ የግጭቱ ፈጣሪ ራሱ ህወሃት ሲሆን የተሰጠው መፍትሄ ደግሞ በጣሙን የሚገርምና በሁለቱ ሕዝቦች መሀከል ያለውን ግንኙነት ለማሻከርና ተባብሶ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው። ሶሞኑን በአማራና በትግራይ አጎራባች ክልሎች የተፈጥረው ግጭት ሆነ ተብሎ በህወሃት የተፈበረከ ሲሆን ከሁለቱም ወገኖች ደም እንዲፈስ ንብረት እንዲወድም እስከወዲያኛው የማያገናኝ ተግባር እየተፈፀመ ይገኛል።ድርጊቱን የሚያስፈጽሙት እንደ እባብ ገላ ማንነታቸውን አውልቀው የጣሉ የለየላቸው ሆዳም የህወሃት ጀሌዎች አማራዎችና የወረራው ፊታውራሪ ህወሃት መሆናቸው ቢታወቅም ሰፊው የትግራይና የአማራ ነገድ ሕዝብ እንደ ድሮው እንደ ጥንቱ በአገራችን ባህል መሠረት የተጫረውን እሳት ሊያበርዱት ይገባል።በተለይ የትግራይ ሕዝብ ህወሃት ለአርባ ዓመታት ያህል መጠቀሚያ አድርጐ የተጠቀመበት ሲሆ ዛሬም ባድማው ባዶ እንዲሆን ከኤርትራ ሕዝብና ከአማራ ሕዝብ ጋር በማጋጨት ሰላምህን እያደፈረሱ ስለሆነ በቃችሁ በላቸው።
በመጨረሻም አቶ በረከት እሱን መች ጠየቅንህ በሚል የጀመርኩት ባእዴንም ወያኔዎች (ወየንቲ) ነን ብሎ የተናገረውን ሰምቼ ነው።ህወሃትን ከሚገባው በላይ ሲያወድስ ባእዴን እንዴት ይንከባከቡት እንደነበር ሲደርት ባእዴን የመጣ አሁን በዚያ ወቅት የነበረው ኢህዲን ይህንም መለየት ከማይችልበት የደረሰ ይመስለኛል ታናንት **ህወሃት የታገለው የአክሱማዊ ዳይናስቲን ለመመለስ አይደለም ** ያለው ጀግና ዛሬ ድመት እጅ እንደገባች አይጥ በጣም አንሶና አድርባይነቱን ሊሸፍን በማይችል መልኩ ሲዘላብድ ደደቢት ላይ ሆኖ የተወራ ወሬ ወይም ድስኩር አይሰማም ብሎ አስቦ ወይንስ አንዳች ነገር ወርዶበት?ህወሃት በዓሉን የሚያከብረው በየካቲት ነው ዘንድሮ አስቀድሞ ወደ ደደቢት ሄዶ ያን ያህል ውሽከታ ሲደረግ ግርምት ጥሎብኝ ነበር።
በረከት፦ላንተ የሚቀርብህ ሻእብያ እንጅ ህወሃት አይደለም ብአዴን ልትሆንም አትችልም ምክንያቱም አንተ የሞቱት እማ ብሬና የአባ ገብረእግዚአብሔር ልጅ ነህ እነሱ ደግሞ ጥርት ያሉ ጨዋ ኤርትራዊ ናቸው ታዲያ አንተ ብሔረ አማራ ሆነህ እንዴት ነው አማራውን የምትወክለው?ይህን ነው መመለስ የሚገባህና የምንጠይቅህ ስለህወሃት ጀግንነት ስለደርግ ጨቋኝነት አንተ አትነግረንም ይልቁንስ አንተን ጨምሮ ከጌቶችህ ጋር የምታራምዱት ሥርዓት ምን እንደሚመስል ለማሰብ ሞክር ።ወጣት ሴቶችና ወንዶች በዘመናዊ ባርነት ሥር እንዲወድቁ የሚያደርግ ህጋዊ የደላላ ጽ/ቤት ከፍቶ ስደትን የሚጠራ መንግሥት ፤በተለያየ ሱስ ተለክፈው መደበኛ ተግባራቸውን እንዳይፈጽሙ የሚያደርግ መንግሥት፤ በዓረብ አገር ያሁሉ ግፍ ሲፈጸም፤ወደ ዓረብ አገር ለመሄድ በሽዎች የሚቆጠሩ ባህር ላይ ሰምጠው የአሳ ቀለብ ሲሆኑ ከየአቅጣጫው በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት ሲደርስ ያንተ መንግሥት አንድም የደረሰ ጉዳት የለም፤የሞተ፤የታሰረ የለም ብሎ ሞግቶናል የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን ጋዜጠኞችን፤ጦማርያንን፤ተማሪዎች አስተማሪዎችን ነጋዴውን፤አርሶ አደሩን የሃይማኖት መሪዎችን ማሰር መግደል አስሮ ማሰቃየት የሚል መርህ የሚያራምድና የዘረጋ ጭፍን አስተሳሰብ ከሚያስቡትና በቀልተኝነትን ከሚገፉት አንዱ አንተ ነህ ምናልባት ባንተ አመለካከት እንደ ኤርትራዊነትህ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ሆነ ጉዳት ላይሰማህ ይችል ይሆናል ደግሞም ትክክል ነው። እኛ ግን እንጠይቅሃለን ማተብህን ከፈታህ ወዲህ በአስፈጃቸው አማራዎች ሁሉ እንጠይቅሃለን፤የመንግሥት ሥልጣንን መከታ በማድረግ በአባቶቻችን ደምና አጥንት ተከብሮ የኖረውን ዳር ድንበራችን በማስደፈርህ እንጠይቅሃለን፤አንዱን ጐሣ ከሌላኛው ጐሣ ጋር በማጋጨት ደም በማፋሰስህ እንጠይቅሃለን፤ ምስኪን አብሮ አደጐችህን የትግል ጓዶችህን ጊዜ ጠብቀህ ስለበላሃቸው እንጠይቅሃለን። ብአዴን እንዲፈርስ አንተም ከአማራ ሕዝብ ትካሻ እንድትወርድ ሌሎችንም እንዲወርዱ እንጠይቃችኋለን ፤የአማራ ዘር እንዲመክን በማድረግህ እንጠይቅሃለን።ለዛሬው ይህ ይበቃሃል ደጋግመህ አንብበው አያ በረከት።
ነብሮ ነኝ ከሰ/አሜሪካ
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.