የጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ የልደት በአል አገር ቤት በድምቀት ተከበረ
(ርእዮት ለልደት ቀኗ ከእስር ቤት የላከችውን ደብዳቤ ይዘናል)
(ኢ.ኤም.ኤፍ) በውጭው አለም የታዋቂ ታጋዮችን የልደት በአል በማክበር አላማቸውን ህያው ማድረግ የተለመደ ነው። ኔልሰን ማንዴላ በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት የልደት በአላቸውን በማክበር፤ አላማቸው ሁሌም በተከታዮቻቸው ህሊና ውስጥ እንዲቆይ ሲደረግ ነበር። ከሞቱም በኋላ ቢሆን ይኸው የልደት ማክበር ስርአት እንደቀጠለ ነው። በአሜሪካ ደግሞ መስሪያ ቤቶች እና ት/ቤት ጭምር ተዘግተው የጥቁሩ ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በየአመቱ በድምቀት ሲከበር እናያለን። በዚህም የልደት በአል አጋጣሚ… ማርቲን ሉተር ኪንግ የቆመለት የሰላማዊ ትግል አላማ ይዘከራል። ይህ አይነቱ መልካም ባህል ወደ ኢትዮጵያ ተሸጋግሮ የጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ የልደት በአል በየአመቱ በመከበር ላይ ነው።
በዚህ አመት የርዕዮት አለሙ የልደት ቀን ከመድረሱ በፊት በውጭ አገር በሚገኙ ደጋፊዎች ጭምር ነው መከበር የጀመረው። በአትላንታ የሚገኘው ማህደረ አንድነት የተባለው፤ አንጋፋ የሬድዮ ጣቢያ የርዕዮት አለሙን የልደት በአል ባለፈው የእሁድ ፕሮግራሙ ሰፊ የአየር ሽፋን ሰጥቶ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እንድትታወስ አድርጓል።
እሮብ ‘ለት የር ዕዮት አለሙ ልደት ሲከበር፤ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ተገኝተው ነበር። የመድረክ፣ የአንድነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች ተገኝተዋል። እንደፕሮፌሰር መስፍን እና ዶ/ር ያዕቆብ አይነት ታዋቂ ሰዎች በልደት በአሏ ላይ ሲገኙ ልዩነታቸውን ወደጎን አድርገው ነበር። የልደት በአሏ ከተከበረ በኋላ ፍቅረኛዋ ጋዜጠኛ ስለሺ ሃጎስ እንደገለጸው ከሆነ፤ “ሁሉም ሰው ተገኝቶ ነበር።” በማለት ስሜቱን እንዲህ በማለት ነበር የገለጸው።
ልደቷን ሰብሰብ ብለን አክብረናል፡፡ የቀረ ሰው የለም፡፡ ቤተሰቦቿ፣ ጓደኞቿ፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች… ማንም አልቀረም፡፡ “ደስ ይል ነበር” የማልለው ርዕዮት ስላልነበረች ብቻ ነው፡፡ የልደት በዓሉ ሲከበር ርዕዮት በዚህ ሰዐት ምን እያሰበች ይሆን? በሚል ጥያቄ ስናጥ ነበር፡፡ አሁንም መልስ ባላኘሁላቸው በርካታ ጥያቄዎች እየተናጥኩ ነው፡፡ ለርዕዮት መስዋዕትነት እውቅና ለመስጠት የሚፈቅዱ ሰዎች ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ ታዲያ ርዕዮት ይሄ ሁሉ ሰው እያላት ለምን ትሰቃያለች? ለምን እኛ እያለን የርዕዮትና የመሰሎቿ የመከራ ቀን ይረዝማል? እኛስ ተራበተራ እየተለቀምን መከራችንን የምናየው ለምንድነው? ለምን አንድ አልሆንም? ለምን? ለምን? ለምን? ለምን?… ጥያቄ ብቻ፤ መልስ የለም፡፡
በዚህ የልደት አከባበር ወቅት ርዕዮት አለሙ ከቃሊቲ እስር ቤት በጽሁፍ ያስተላለፈችው መልእክት በንባብ ተሰምቷል። ይህንኑ ጽሁፍ ከዚህ በመቀጠል አቅርበነዋል።
ጥር 13/2007 ዓ.ም
==============================
በቅድሚያ የልደት በዓሌን ለማክበር እዚህ የተሰባሰባችሁትንና እዚህ ባትገኙም አላማዬን በመደገፍ ፍቅርና ከብር የሰጣችሁኝን ወገኖች ሁሉ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
በመቀጠል እኛም ራሳችን ሆንን ሌሎች ኢትዮጵያዉያን እንደሰዉ መኖር የሚችሉባትን ሀገር ለመፍጠር በየሙያ ዘርፎቻችሁ፣ በፓርቲ ተደራጅታችሁም ሆነ በሌላ በማንኛዉም መንገድ እየታገላችሁ ላላችሁ በሀገር ዉስጥና በዉጭ የምትኖሩ የማከብራችሁ ወገኖች በሙሉ ሶስት ዋና ነጥቦችን የያዘ አጭር መልዕክት ላስተላልፍላችሁ ፈልጋለሁ፡፡
ጊዜዉ የምንታገለው ስርአት ከመቼዉም በበለጠ ሁኔታ አምባገነንነቱ የበረታበት ወቅት እንደመሆኑ ከባድ የስራና የመስዕዋትነት ዘመን ከፊታችን እንደሚጠብቀን ግልፅ ነው፡፡ ተግባራዊነቱ ላይ ድክመት ቢኖርብንም ስራችንን ለማቅለልም ሆነ መስዕዋትነቱን ቀንሶ ባልረዘመ ጊዜ ዉስጥ ለድል ለመብቃት አንድነት ቁልፍ መሆኑን እኔን እናንተም አናጣዉም፡፡ የአንድነትን ተገቢነትና ጠቃሚነት እስካመንበት ጊዜ ድረስ ቆም ብለን ድክመቶቻችንን በመገምገም እና በተቻለ መጠን አላስፈላጊ ልዩነቶችን በማጥበብ ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛዉንም አይነት ህብረት ልንፈጥር ይገባል እስኪ አስቡበት፡፡
በተለያዩ እስር ቤቶች ዉስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ የሃይማኖታቸዉን ነፃነት ለማስከበር የቆረጡ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች፣ የሀገርና የወገን ጉዳይ ያገባናል ያሉ በተለያዩ የትምህርትና የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተዉ የነበሩ ግለሰቦች፣ እነዚህና የመሳሰሉትን እስረኞች ስታስቡ ምን ይሰማችኋል? ሁሉም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ለሀገራችን ብሩህ ቀን ለማምጣት ወይም እንደሰዉ መብታቸው ተከብሮ ለመኖር ሲ,ታትሩ የነበሩ ግን በተለያየ ስም ተጠርተው ወደ እስር ቤት የተወረወሩ የኢትዮጵያችን ምርጥ ልጆች መሆናቸዉ እነደሚሰማችሁ አልጠራጠርም፡፡ እኔም የሚሰማኝ እንዲሁ ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ በተሰማኝ ቁጥር እቆጫለሁ፡፡
የሁላችንም አላማ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ቢሆንም ተነሳሽነቱን ወስደን ወደ አንድነት ለመምጣት ባለመሞከራችን ወይም በሙከራችን ባለመግፋታችን ምክንያት መከራችንንም ሆነ የድሉን ቀን እንዳራዘምን መረዳቴ የቁጭቴ ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም እድሉ በእጃችሁ ያለ እናንተ ከእንዲህ አይነቱ ቁጭት ትድኑ ዘንድ ይህን አምባገነን ስርዐት ከልባቸዉ የሚቃወሙትን ሁሉ በሆነ መንገድ ወደ አንድነት ለማምጣት የሚቻላችሁን ሁሉ እንድታደርጉ አበረታታችኋለሁ፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር እንኳን ቢያንስ ቢያንስ አንዳችሁ ስለሌላችሁ አሉታዊ አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ ግን ይኖርባችኋል፡፡
ስለ አንድነት ይህችን ያህል ካልኩ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተገቢ የሆነ የትግል ስልትና አይነት ስለመጠቀም ጥቂት ለመተንፈስ ወደድኩ፡፡ ኔልሰን ማንዴላ Long walk to freedom በተሰኘ ግለ ታሪካቸዉ ላይ እንዳሰፈሩት የትግሉን ስልት የሚወስነዉ ጨቋኙ ነው፡፡ እኔም በዚህ አምናለሁ፡፡ አንድ ሰዉ ለሰደበዉ ሰውና ለተኮሰበት አንድ አይነት የአፀፋ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ጤነኛነቱ ያጠራጥራል፡፡ አንድ ጤነኛ ሰዉ ለሁለቱም የሚሰጠው የአፀፋ ምላሽ የተለያየና ለድርጊታቸዉ የሚመጥን እንደሚሆን ይገመታል፡፡ በሌላ አነጋገር የተበዳዩን ሰዉዬ ምላሽ የወሰነው በዳዩ ነው ማለት ነው፡፡ እኛስ ምን እያደርግን ነው ያለው? መረጥነው የትግል ስልት የምንታገለውን አካል ለማሸነፍ የሚያዋጣ ነዉን? የሚያዋጣ ከሆነስ በሚገባ ተጠቅመንበታል? እነዚህንና የመሳሰሉት ጥያቄዎች መጠያየቅና በቂ ምላሽ ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አሁን እየተሸከረከርንበት ካለሁ ክብም መዉጣት አለብን “የቱ ክብ?” ካላችሁኝ መልሴ እነሆ!
ምርጫ በደረሰ ቁጥር ገዢዉ ፓርቲ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባሎች እንዲሁም የግሉን ፕሬስ ጋዜጠኞች ያስራል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በቂ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ የሚችለዉን ሁሉ ይፈፅማል፡፡ የግል የህትመት ዉጤቶችን ይዘጋል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ምርጫዉ ይደረጋል፡፡ ገዢዉ ፓርቲ ድምጽ ያጭበረብራል፡፡ ምርጫዉ ተጭበርብሯል የሚሉ ወገኖች ካሉ ከመታሰር አንስቶ እስከመገደል ድረስ እርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “አሸንፋችኋል” የተባሉትን መቀመጫ በጸጋ ተቀብለዉ እስከሚቀጥለው አምስት አመት ድረስ ያደፍጣሉ፡፡
ታዋቂዉ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን “አንድ ነገር በተመሳሳይ መልኩ እያደረጉ የተለየ ዉጤት መጠበቅ ሞኝነት ነው” አለ ተብሎ የለ? እስካሁን የተሞኘነዉ ከበቂ በላይ በመሆኑ አካሄዳችንን ቆም ብለን ማየትና የትግል ስልቶቻችንን መፈተሸ ይኖርብናል፡፡ እንዲህ ማድረግ ካልተቻለ ግን ህዝቡ አካሄዳችን የትም እንደማይደርስ ይሰማዉና በትግሉ ዉጤታማነት ተስፋ ይቆርጣል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ተስፋ መቁረጡ ወደ ግሉ ፕሬስ አባላት፣ ወደ ተቃዋሚ ፓርቲ አባሎችና አመራሮች ጭምር እየተጋባ አንገት ደፍቶ መገዛት ይከተላል፡፡ ያቀን ከመምጣቱ በፊት የህዝቡን ተጠቃሚነትና ደህንነት ማዕከል ያደረጉ ነገር ግን አዋጪ ሊሆኑ የሚችሉ የመታገያ መንገዶችን በሙሉ መፈተሸና እንዳስፈላጊነቱ መጠቀም አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ ይሰማኛል ፡፡
በሶስተኛነት ልጠቅሰዉ የምፈልገዉ ጉዳይ ፅናት ነው፡፡ ፅናት የያዝነዉን አላማ ከዳር ለማድረስም ሆነ ለራሳችን የስነልቦና ደህንነት የሚጠቅመን ድንቅ ሀብት በመሆኑ አጥብቀን ልንይዘዉ ይገባናል፡፡ ላመንበት ነገር መቆም፣ ለሱው መኖርና ለሱው መሞት! ወደ ድል መድረሻ መንገዱ ሲረዝምባቸዉ ወይም አላዋጣ ሲላቸዉ አላማቸዉን የሚተዉ ወይም የሚቀይሩ ሰዎች አልገጠሟችሁም? ከእነሱ ስህተት ተምራችሁ አካሄዳችሁ ወደተስፋ መዉረጥ ሳይወስዳችሁ በፊት አስተካክሉት፡፡ አላማችሁን ግን በፅናት አጥብቃችሁ ያዙት፡፡ ከመጀመሪያው በያዝነዉ አላማ ምክንያት የሚደርስብንን ሁሉ ለመቀበል አስቦ መንቀሳቀስ እንጂ መከራ ሲመጣ “ጎመን በጤና” ብሎ ማፈግፈግም ተገቢ አይደለም፡፡ በመሆኑም የጀመርነውን ጉዞ በስኬት ለማጠናቀቅ ከፈለግን ፅናት ሊለየን እንደማይገባ እያስታወስኩ እሰናበታችኋለሁ፡፡ እወዳችኋለሁ፡፡
ርዕዮት አለሙ
ከቃሊቲ እስርቤት
ጥር 13/2007ዓ.ም
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.