(ኢ.ኤም.ኤፍ) በቅርቡ የህወሃት 40ኛ አመት ሲከበር፤ በርካታ የኪነ ጥበብ ሰዎች የተደረገላቸውን ግብዣ ተቀብለው ወደ ትግራይ ማምራታቸው ይታወሳል። ሁሉም አርቲስት ግን… ፖለቲካዊ ይዘት ያለውን ጉዞ አልተቀበለም። ሁሉም የየራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል። ህዝቡ ወደ ደደቢት የሄዱትን ያወገዘውን ያህል ጥሪውን ሳይቀበሉ የቀሩትንም ማመስገን ይገባው ነበር። ወደ ደደቢት ካልሄዱት መካከል፤ እነአብርሃም ወልዴ፣ እነጆሲ፣ ላፎንቴን፣ ደረጄ ኃይሌ፣ ሰይፉ ፋንታሁን እና ሌሎችም ሊመሰገኑ ይገባል። ሁሉም በየራሳቸው መንገድ የራሳቸው ምክንያት ቢኖራቸውም፤ ለመጀመሪያ ግዜ ምክንያቱን በአደባባይ ለመግለጽ የበቃው ገጣሚ ታገል ሰይፉ ግን፤ “ጥሪ ቢደረግልኝም ስላላመንኩበት ቀርቻለሁ።” ብሏል።
የዚህ ሁሉ መነሻ፤ የኢዮፒካ ሊንክ ሬድዮ ጋዜጠኞች ያቀረቡት ቀለል ያለ የሚመስል ጥያቄ ነበር። እንዲህ ብለው ጠየቁት። “ሰዎች ስላንተ እንዲያውቁ የምትፈልገው ነገር ምንድነው?” አሉት። ገጣሚ ታገልም ሲመልስ፤“ከተፈቀደልኝ ሰዎች እንዲያውቁት የምፈልገው…” ብሎ ጀመረ።
“ሰዎች የማይረዱት ነገር አለ። ለምሳሌ ባለፈው የመቀሌ ጉዞ ላይ እኔ አልሄድኩም። አርቲስቶች ሲሄዱ ጥሪ ተደርጎልኛል። ነገር ግን የደደቢቱን ጉዞ ስላላመንኩበት ቀርቻለሁ። ስለማልፈልገው ማለት ነው። …ለነሱም የምለው ነው። በተለይ ባለፉት 15 አመታት ብዙ ነገር አልተሰራም። ለስነ ጽሁፍ የሚመች ግዜ አይደለም። ስነጽሁፍን ትኩረት አልሰጡትም። እያየን ነው። ግድቡ ሲገነባ ደስ ይላል። ቤት ሲሰራ ደስ ይላል። ነገር ግን የሞራል ሃብታችን እየወደቀ ነው። በደርግ ግዜ ለስነ ጽሁፍ ትኩረት ተሰጥቶት አድጓል። ብዙ ትላልቅ ደራሲዎቻችን በሳንሱር ዘመን ነው የወጡት። እንደነጸጋዬ ገብረመኅን፣ እነ በአሉ ግርማ… አሁን ግን እንደነዚያ አይነት ትላልቅ ሰዎች አልወጡም። ምክንያቱም ለስነ ጽሁፍ ትኩረት አልተሰጠም። ይህ መንግስትን ዋጋ ያስከፍለዋል።
“እንዲያውም ጠቅላይ ሚንስትሩ የሞቱ ግዜ ለሳቸው የተሰማኝን ሃዘን የሚገልጽ ግጥም አቅርቤ ነበር። እና ከዝግጅቴ በኋላ አንድ ጋዜጠኛ ‘ጠቅላይ ሚንስትሩ ለኪነ ጥበቡ ማደግ ምን አድርገዋል?’ ሲለኝ ‘ምንም’ ነበር ያልኩት። እርግጥ ይህ ያልኩትን ቆርጠው አውጥተውታል። …እናም ወደ ትግራይ ለጉብኝት ሲሄዱ ስላላመንኩበት እኔ አልሄኩም።
“በሁለተኛ ደረጃ የግል አቋም አለኝ። ለምሳሌ ‘በደርግ እና ኢህአዴግ’ መካከል የተካሄደው ጦርነት የሁለት ወንድማማቾች ጸብ ነው። እዛ ጸብ ውስጥ አንዱን በሌላው ላይ ጀግና ማለት እምነቴ አይደለም። ለኔ የመንግስት ጀግንነት የሚጀምረው ጦርነቱን ጨርሶ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ባሳያቸው ለውጦች ነው የምለካው። እንጂ እዛ ጋር ገዳይም ወንድሜ ነው፤ ሟችም ወንድሜ ነው። አንዱን በአንዱ ላይ ጀግና ለማለት እዚያ አልሄድም። አስፈላጊም አልነበረም። አሁን እኔ እንደዚህ አይነት አቋም አለኝ። ሆኖም አንዳንድ ድረ ገጾች ላይ ስታይ፤ (ለአባይ ግድብ ያቀረበውን ግጥም አይተው፤ ሰዎች ‘‘ባንዳ ባንዳ’ ብለው የሰደቡትን በማስታወስ ይመስላል… የንዴት ትንፋሽ አስማ) የአባይ ጉዳይ ሲሆን በዚህ ሁሉ ልዩነት መሃል አገሪቱን ዲያብሎስም ቢመራት የአባይን መገደብ እደግፈዋለሁ። ብዙ ሰዎች ይህንን በደንብ አይረዱትም። ….ወደኋላ ሄደህ ብትመለከት ወንድሙን ገድሎ ስለመጣው ኢህአዴግ ጀግንነት ጽፌ አላውቅም።
“…ከመንግስት ጋር ብዙ ደስ የማይሉኝ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። አባይ ሲባል ግን… ይህ የአገር ጉዳይ ነው። …ማንም የፈለገውን ትርጉም ቢሰጠው ይህ ለዘመናት አያት ቅድማያቶቻችን እንዲሆን ሲመኙት የነበረው ነገር ነው። ስለዚህ አባይን በተመለከተ ሰዎች በዚህ በኩል ቢረዱኝ ደስ ይለኛል፤ ለማለት ነው።” ብሏል።
ገጣሚ ታገል ሰይፉ በዚህ ቃለ ምልልሱ ላይ አሁን ባለው የኢህአዴግ አስተዳደር ዘመን የትውልድ ዝቅጠት መድረሱን ሳይጠቅስ አላለፈም። ትልቁ የሞራል እሴት እየተሸረሸረ፤ ወጣቱ የራሱን ተራ ጥቅም የሚያስቀድም ጥቅመኛ እና ግለኛ መሆኑን በሰፊው ዘርዝሯል። በቃለ ምልልሱ መጨረሻ ላይ የኢትዮፒካ ሊንክ ጋዜጠኞች ጭምር ገጣሚ ታገልን፤ “ጀግና” የሚል ቅጽል ሰጥተውት ቃለ ምልልሳቸውን አብቅተዋል።
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.