Ethiopia Zare (ማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. March 17, 2015)፡- በውጪ አገር ለሠላሳ ዓመታት የቆዩትና ለሰባት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት የሰሩት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከስራ መባረራቸውን ገለጹ። ዶ/ር ዳኛቸው፣ ኢትዮጵያዊ ማለት መብቱ የሚረገጥ ማለት በመሆኑ፣ አሁን ገና ኢትዮጵያዊ ሆንኩ በማለት በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር ዳኛቸው ከዩኒቨርስቲው ከስራ የተባረሩበትን ምክንያት ሲገልጹ፤ የዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግና የቅጥር ውሌ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው አንድ መምህር ለስድስት ዓመት በተከታታይ ከአስተማረ፣ ለአገለገለበት ዘመን የአንድ ዓመት የጥናትና ምርምር ዕረፍት (sabbatical leave) እንደሚሰጠው ተደንግጓል። ሆኖም በዚህ መነሻ በማድረግና የጡረታ ዕድሚዬ መድረሱን በማመካኘት እንድሰናበት አድርገውኛል ብለዋል።
ከዛ በፊት ለሦስት ወራት ደሞዝ ተከልክለው እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ዳኛቸው፤ በተለምዶ ስድሳ ዓመት የሞላቸው መምህራን የውል ማራዘሚያ ጊዜ ይጠይቃሉ። እኔ የማውቃቸውና በተደጋጋሚ የተጨመረላቸው መምህራንም አሉ። በጣም አስገራሚና በግቢው አነጋጋሪ የኾነው ግን የእኔና የዶ/ር መረራ ጉዲና የውል ማራዘሚያ ጊዜ መከልከሉ ነው በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል።
ለዚህ ሁሉ መነሻ የሆነውና ከባለሥልጣናቱ ጋር አለመግባባት የተፈጠረበት ምክንያት፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ልዩነት እንደሆነ አልደበቁም። ከዩኒቨርሲቲው በመባረራቸው ብዙ ቢያዝኑም፤ ለሰባት ዓመታት ያህል ለማስተማር በመቻሌ ሙሉ የሆነ እውቀት ያገኙ ተተኪዎች ለማፍራት ስለበቃሁ አንጻራዊ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።
በሌላ በኩል ግን ከሌሎች ጥቃት ከደረሰባቸው ወጣቶች ዓይን ሲታይ የኔ መባረር ብዙም የሚያሳዝን አይደለም፤ እንደውም ለሰላሳ ዓመታት የት ነበርክ ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይወቅሰኝ ይሄንን ዕድል ሰጥቶ ስላሰራኝ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። አሁንም ቢሆን የስራ ፍላጎት ቢኖረኝም በእንዲህ ዓይነት አገር የኔ ፍላጎት ብቻ ለስራ ብቁ ስለማያደርግ የወደፊቱን መናገር ያዳግታል፤ ሆኖም ሀገሬን ለማገልገል ምንግዜም ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
ዶ/ር ዳኛቸው በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ቢኾኑም፤ በሕግ ፋክልቲ፣ በሴንተር ፎር ሂዩማን ራይትስ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ በአምስት ኪሎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋክልቲ፣ በቴአትሪካል አርትስ እና በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤትም እንዳስተማሩ ታውቋል።
ዶክተሩ በዩኒቨርሲቲው የቆዩበትን ጊዜ እና ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበትን ተቋማዊ ኹኔታ በተመለከተ አንድ መጽሐፍ ለህዝብ እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል።
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.