Friday, March 27, 2015

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከጥፋት የሚታደገው ብቸኛው መንገድ!!!

Amsalu
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሰሞኑን የተለያዩ ምሁራን በአማራ ስም የመደራጀትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ጽፈዋል፡፡ አስቀድሞም ከፊሎቹ “ራሳችንን ማንነታችንን መሠረት አድርጎ እየተፈጸመብን ካለው ጥቃት ለመከላከል እንችል ዘንድ በራሳችን ብሔረሰብ በአማራ ስም የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም የግድ አስፈላጊ ነው” በማለት በአማራ ስም የፖለቲካ ድርጅት የማቋቋምን ጉዳይ አስፈላጊነት ያንጸባረቁ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ያልበሰሉትም ከዚህም አልፈው በተቀደደላቸው በር በመግባት የመገንጠልን ሐሳብ ያነሡም አሉ፡፡ እነኝህ ሁሉ አስተሳሰቦች ለኔ የሚያሳዩኝ ነገር ምንድን ነው? የወያኔና የሌሎች የጥፋት ኃይሎች የጎሳ ፖለቲካ ምን ያህል እንደሠራላቸው ስር እየሰደደ እንደሆነና ሳናውቀው የዚህ የጥፋትና ፀረ ኢትዮጵያ መርዘኛ የጥፋት ስብከት ሰለባ መሆናችንን ነው፡፡ እኔን የቸገረኝ ነገር ቢኖር እንዲህ ዓይነት አቋም ከያዝን በኋላ እኛን ከወያኔ የሚለየን ምን እንደሆነና የጎሳ ፖለቲካ ከሚያመጣው አላስፈላጊ ችግሮች አንጻር ከጎሳ ተኮር አደረጃጀት ርቀን በኢትዮጵያ ጥላ ስር ወይም ብሔራዊ አደረጃጀትን በመጠቀም ያሉብንን ችግሮች እንዳንዋጋ ምን እንደሚከለክለን ነው፡፡ የቸገረን ቆርጦ የሚታገል ታጋይ መጥፋት እንጅ የድርጅት ስም አይደለምና፡፡ አይበለውና አማራ እንደ ሕዝብ አማራነቱን ለማየት የኢትዮጵያን መነጽር አውልቆ የጎሳ መነጽር ያጠለቀ ለት ይህች ሀገር ያልቅላታል፡፡ የወያኔ ዓላማና ትግልስ ምን ሆነና? የአማራ ማኅበረሰብ በአማራ ስም ተደራጅቶ መታገል የማይፈልግበትና ይሄንን የሚጠላበት ከማንነቱ ጋር የተሳሰረ ምክንያትና አስቀድሞ የደረሰበት ላቅ ያለ የበሰለ አስተሳሰብ አለውና ይሄንን ቅርሱን የእናት አባት አደራውን እንድታከብሩለት እያሳሰብኩ ከብሔረሰብና ከእሱ ጋር ተያይዘው ስላሉብን ችግሮችና መፍትሔያቸው ላይ በማተኮር አምና የጻፍኩትን ይሄንን ጽሑፍ አሁን ከተቀሰቀሰው መነጋገሪያ አንጻር ወቅታዊ ሆኖ ስላገኘሁት እንድታነቡ እጋብዛቹሀለሁ፡-
ዛሬ እውነት እውነቱን እንቅጭ እንቅጩን እንነጋገራለን፡፡ እንዴ! ይሄ ሰው ከዚህ ቀደም ሲያወራልን የኖረው ቅጥፈት ነበር እንዴ? እንዳትሉ፤ አለ አይደል ይሄ መፏከቱን መሸራደዱን መበሻሸቁን ትተን እንደ ባለ አእምሮና ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ በንጹሕ በቅዱስ ልቡና ልዕልና ያለውን ሐሳብ አንሥተን እንወያያለን ለማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ዐይነ ሕሊናችንን ያብራልን እዝነ ልቡናችንን ይክፈትልን አሜን!!
ሀገራችን ኢትዮጵያ የዘውግ ፖለቲካ (እምነተ-አስተዳደር) ወይም ብሔር ተኮር የሆነ ከፋፋይና አጥፊ የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ በግዳጅ እንድትዘፈቅ ከተደረገች 24ኛ ዓመታችንን ይዘናል፡፡ በዚህ ዘመን ውስጥ አንድነት የነበረው ሕዝብ በግድ ካልተነጣጠልክ፣ በጎሪጥ ካልተያየህ፣ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ሁሉ ለእኛ ለእኛ ሳይሆን ለእኔ ለእኔ (ለብሔረሰቡ ብቻ) ካላልክ ተብሎ እየተወተወተ ወዶ ሳይሆን በግድ ይሄንን እኩይ አስተሳሰብን እንዲጨብጥ ተገደደ ተደረገም፡፡

ቅድመ 1983ዓ.ም. በተለይም ከ1966ቱ ዐብዮት ፍንዳታ ወዲህ ምንም እንኳ ብሔረሰቦች እንዳሉ ቢያምንም ሕዝቡ እርስ በእርሱ በሚያደርገው ማኅበራዊ ግንኙነቱና ወሳኝ የሕይዎት ኩነቶቹ የዘር ልዩነትን ማዕከል አድርጎ ሲንቀሳቀስ አይታወቅም ነበር፡፡ ለጓደኝነት (ለባልንጀርነት) ለወዳጅነት፣ ለትዳር አጋርነት፣ ለማኅበርተኝነት ዘሩን ወይም ዘሯን መስፈርት የሚያደርግ ዜጋ መኖሩ እጅግ ያጠራጥራል፡፡ በእርግጥ የነገሥታት የዘር ኃረግ ያላቸው ዜጎች ጋብቻን በተመለከተ የተለየ አመለካከት እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ እሱም ቢሆን ግን  እራሳቸው ነገሥታቱ ከነገሥታት የዘር ኃረግ ብቻ ሳይሆን ከብሔረሰባቸውም ውጭ ለሆኑ ልጆቻቸውን በመስጠት በተደጋጋሚ ይሄንን አስተሳሰብ የጣሱበት ያፈረሱበት በርካታ አጋጣሚ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሕዝቡ ደረጃ ግን ይህ ችግር እንደ ችግር አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በ1983ዓ.ም. ሥልጣን በያዘው ቡድን “በየክልልህ” የሚል መርህ ግን ሁላችንንም ያስተዛዘበ ልጆችን ያፈሩ ትዳሮች ሳይቀር እስኪፈርሱ ድረስ ክስተት ሊባል በሚችል ደረጃ መለያየት መጥቶ አንድነታችንን አፈረሰው፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ይህ የዘር ልዩነት እኩይ አስተሳሰብ ከምንተነፍሰው አየር ጋራ ሳይቀር የተቀላቀለ ገዥ ሐሳብ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ነገሩ ከዚህም አልፎ ዜጎች የዚህ ወይም የዚያ ብሔር አባል በመሆናቸው ብቻ ግድያን ጨምሮ ለተለያየ ዓይነት ጥቃት ሰለባ እስከመሆን ተደርሶ እርስ በእርስ የመጠራጠር የመጠባበቅ የጥላቻ መንፈስ ነገሠ፡፡
እናም ይህ አገዛዝ ይሄንን በብዙ ድካምና ክፍላተ ዘመናት የተገነባውን የሕዝባችንን በተለይ በሀገር ጉዳይ ላይ የነበረንን አንድ ሐሳብ አንድ ልብነት አፈራርሶ ጭራሽም አጠቃላይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማሻከር በማደፍረስ ብዙ ሽህ ዘመናት ወደ ኋላ መልሶ ኢትዮጵያ ከመመሥረቷ በፊት ወደነበረው መፈራቀቅ መለያየት መራራቅ ውስጥ እንድንገባ አደረገ፡፡ ሥርዓቱ በሰነዶች ላይ ሁሉ ሳይቀር ዘርን መጥቀስ ግዴታ አድርጎ ሕግ ሠርቷል፡፡ በዚህም መሠረት እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህ አሠራር ከሁለትና ከዚያ በላይ ብሔረሰብ የተወለደውን ዜጋ ሁሉ ውዥንብር ውስጥ ከቷል፡፡ የግድ አንዱን መርጦ እንዲጠቅስ ይገደዳል፡፡ አንዱን ብቻ እንዲመርጥ ሲያደርጉት ግን ሌሎቹን በደሙ ውስጥ ያሉትን እንደሌሉ እንዲቆጥር በማድረግ እንዲክዳቸው እያደረጉት እንደሆነ የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ይህ አሠራር “ለብሔር ብሔረሰቦች መብትና ህልውና ጠበቃ ነኝ” ለሚለው አገዛዝ ታላቅ ሀፍረት ነው፡፡ ይህ አገዛዝ ይህ ድርጊቱ ፍጹም ኢፍትሐዊ እንደሆነ ጨርሶ አልተረዳም፡፡ ሥርዓቱ ለብሔር ብሔረሰቦች ተቆርቋሪ ነኝ ማለቱ የማስመሰል እንጅ የከልብ የመነጨ አይደለምና ብሔረሰቦች በዜጎች ደም ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንዲያጡ አድርጎ የማስደምሰሱ ተግባር ኢፍትሐዊነት ጨርሶ አልታየውም፡፡
ለዚህ ስሕተታቸው የሚጠቅሱት አንድ ተለምዷዊ አባባል አለ ሰው ዘሩን ሲጠቅስ ዘር የሚቆጠረው የአባት ነውና የአባትን በመጠየቅ ይሞላሉ፡፡ አባቴም እራሱ የእኔ ዓይነት ጉዳይ ሊገጥመው እንደሚችል ግምት ውስጥ አላስገቡም፡፡ ሲጀመር በአባት በኩል የሚቆጠረው የአባት ትውልድ እንጅ ዘር አይደለም ዘር ሊቆጠር ሲፈለግ ግን “በአባቱ ከነገደ እከሌ በእናቱ ከነገደ እከሌ ይወለዳል” ተብሎ መጥቀስ ግድ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ፣ በታሪካዊ፣ በባሕላዊ መዛግብት ያለውና የነበረው አሠራር ይህ ነው፡፡ የዛ ሰው ትውልድ ከሆነ መቁጠር የተፈለገው አባት የአባት አባት እያለ ወደ ላይ ወይም ወደ ታች ይቆጠራል፡፡ ይሄንን አቆጣጠር በተሳሳተ ግንዛቤ የዘር ቆጠራ እንደሆነ አድርገው በመገመት “ዘር የአባት ነው የሚያዘው” ብለው በዚህ መልኩ ሲሠሩ ቆይተዋል እየሠሩም ይገኛሉ፡፡
ሥርዓቱ ይህ አሠራሩ ስሕተት እንደሆነ ተረድቶ ከዚህ በኋላ በሰነዶች ላይ በአንድ ዜጋ ደም ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ ይጠቀሱ ቢባልም እንኳ ያ ወይም ያቺ ዜጋ በአባቴ እንደዚህ በእናቴ እንደዚህ፣ በአባቴ ሴት አያት እንደዚህ በአባቴ ወንድ አያት እንደዚህ፣ በእናቴ ወንድ አያት እንደዚህ በእናቴ ሴት አያት እንደዚህ እየተባለ ወደላይ መቁጠሩ ለአሠራር ካለመመቸቱም በላይ ብሔረሰቦች ተዋሕደው በአንድ ሰው ደም ላይ መኖራቸው ከታወቀ እያንዳንዳቸው የመቆጠራቸው የመጠቀሳቸው አስፈላጊነት የሚታይና የሚያሳምን ጠቀሜታና ፋይዳ ያለው ጉዳይ አይደለም፡፡
ከሳምንታት በፊት ከጂማ ዩኒቨርስቲ (መካነ-ትምህርት) በቀረበብኝ ክስ ምክንያት በፌደራሉ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ማዕከላዊ) ቁጥጥር ስር ነበርኩ፡፡ ምርመራው በኃይለኛ ክርክርና አለመግባባት ተሞልቶ ለአራት ሰዓታት (ከ8-12 ሰዓት) የቆየ ነበር፡፡ ከመርማሪዎቹ ጋራ ሲያወዛግበኝ ረዘም ያለውን ሰዓት የወሰደው ይህ የዘር ጉዳይ ነበር፡፡ ላቀረብኩላቸው ቁልፍ ቁልፍ ጥያቄዎች ምላሽ አጥተው ስለነበር በኋላ መጨረሻ ላይ የምርመራውን ፎርም (ቅጽ) ሲሞሉ “ብሔር” በሚለው መጠይቅ ስር “የለም” የሚለውን ቃል ለማስፈር ተገደዋል፡፡
ነገር ግን ወገኖቸ እስኪ እንዲያው ከየ ማነቋችን ወጣ ብለን እውነት እውነቱን እንነጋገርና ብሔረሰቦች ማለትም አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ ወዘተ. የሚባሉ ዘሮች ወይም ብሔረሰቦች ሀገራችን ውስጥ አሉ??? ይገርማቹሀል እንዳትሳሳቱ መልሱ የሉም ነው አራት ነጥብ፡፡ አለመኖራቸውን በሚገባ አሳያቹሀለሁና ልብ ብላቹህ ተከታተሉኝ፡፡ ከነኛ ስድስቱም መርማሪዎችና አለቆች ጋር ያወዛገበኝም ይሄው ዐቢይ ሐሳብ ነው፡፡
እርግጥ ነው ምንም እንኳ ዛሬ ላይ አማራ ባይኖርም የአማራ ብሔረሰብ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶች ሁሉ አሉ፡፡ የአማራ እንዳለ ሁሉ ሌሎቹ ሰማንያው ብሔረሰቦች ባይኖሩም የሰማኒያውም ብሔረሰቦች ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶችም አሉ፡፡ መኖራቸውም መልካም ነው ለእሴቶቹም ጥበቃ እንክብካቤ ማድረግ ይኖርብናል ግዴታም አለብን ማዳበር ማበልጸግም ይጠበቅብናል፡፡ የማንነታችን መገለጫዎች ናቸውና፡፡ ያለእነሱ እራሳችንን መግለጽ አንችልምና፡፡ የሀገርም ሀብት ናቸውና፡፡ ለነገሩ እነዚህ እሴቶችም ቢሆኑ በአንደኛው ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶች ሁሉ የሌላኛው ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶች ተቀላቅሎ ተቀይጦ ተወራርሶ ነው እንጅ የአንደኛው በሌላኛው ላይ ያልተወራረሰበት ያልተዋሐደበት የብሔረሰብ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶች አንድም እንኳን የለም፡፡ በመሆኑም በተጨባጭ የአማራ ብቻ፣ የኦሮሞ ብቻ፣ የትግሬ ብቻ፣ የጉራጌ ብቻ ወዘተ. የምንለው ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶች ሁሉ የለም ማለት ነው፡፡ የአማራው ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶች ሁሉ የሌሎችም ነው ማለት ነው፡፡ የሌሎችም የአማራ ነው ማለት ነው፡፡ የቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶች ሁሉ ትስስሩን ውሕደቱን የፈጠረው ሌላ ምንም ሳይሆን በደም መዋሐዳችን መቀላቀላችን መዋለዳችን ነው፡፡ መዋለድ መዋሐድ መቀላቀል በሌለበት ሁኔታ የቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶች ሁሉ መወራረስ መቀያየጥ መዋሐድ መተሳሰር ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከቶውንም የለም፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያን ታሪክና እሴቶች በሙሉ ከአንድ ብሔረሰብ ጋር አጎዳኝቶ የጥቃት ሰለባ ማድረግና (በነገራችን ላይ የአንድ ብሔረሰብ የሆኑ ቢኖርም እንኳ እንዲጠፉ የሚደረግበት ምክንያት አስገራሚና እንቆቅልሽ ነው) የሀገርን ታሪክ እንደ ታሪክ ከታሪክነት ተፈጥሯዊ ባሕርይው ማለትም ከትምህርታዊ መስፈርቱ፣ ከተጨባጭነቱ(it’s tangibility)፣ ከእውነታነቱ (it’s factuality)፣ ከተአማኒነቱ (it’s credibility)፣ ከተገማችነቱ (being speculative)፣ የአሻራ ቅሪት ምልክት (remainder) ከመያዙ፣ ከክስተታዊ ባሕርይው (it’s phenomenal essence)፣ ከጎላ ወቅታዊ እንቅስቃሴ ወይም ተሳትፎና በሌሎቹም መገለጫዎቹ በራሱ ጊዜ ራሱን የሚሠራ የሚፈጥር ሆኖ እያለ ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ “የሀገሪቱ ታሪክ የብሔር ብሔረሰቦች መሆን አለበት” በሚል አስቂኝ ሰበብ ታሪክ የብሔረሰቦች ቤተ መዘክር ይመስል ለዚህኛው ብሔር እንዴት ብለን ምን እንጻፍለት ምን ያህል ድርሻ እንስጠው በማለት  የጨበራ ተዝካር ማድረግ ፍጹም ድንቁርና የተጫነው አስተሳሰብና እብደት ነው፡፡ ይህ በየትም ሀገር ተደርጎም አያውቅ፡፡ ታሪክና ቤተመዘክር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የውክልና ጉዳይ የሚነሣው በብሔረሰቦች ቤተመዘክር ውስጥ እንጅ ታሪክ ላይ አይደለምና፡፡ ታሪክ በተፈጥሮው ለዚህ የሚመችና ይሄንን ጥያቄ የሚያስተናግድ አይደለም፡፡ ተወደደም ተጠላ ታሪክ ተለይቶ የበረታው የታገለው የሚጽፈው መጽሐፍ ነው የዓለም ታሪክ የሚያረጋግጥልን ሀቅ ይሄንን ነው፡፡ ሲጀመር የዚህች ሀገር ታሪክና ሁሉም እሴት የሁሉም ብሔረሰቦች ታሪክና እሴት ነው እንጅ በፍጹም የአንድ ብቻ አይደለም፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ብሔረሰቦች ለዚህች ሀገር ከነጻነቷ እስከ ሥልጣኔዋ አስተዋጽኦዋቸውን በሚገባ አድርገዋል፡፡ በዚህች ሀገር እስካሉ ጊዜ ድረስ አስተዋጽኦ ላያደርጉ የሚችሉበት ምንም ምክንያት የለም ሊኖርም አይኖርም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ስሕተት ሀገር በምሁራኑ ያለመመራት ዕጣ ሲገጥማት ሥራም በትክክል በሚመለከታቸው ያለመሠራት አጋጣሚ ሲፈጠር ከሚያጋጥሙት ችግሮች ዋነኛው ነው፡፡
እናም የብሔረሰቦችን ህልውና በተመለከተ መሬት ላይ ያለው ተጨባጩ ሀቅ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ነው፡፡ ግን ምን ያህሎቻችን ልብ ብለነዋል??? እውነታው እንዲህ በሆነበት ሁኔታ የዘውግ ፖለቲካን (እምነተ-አስተዳደርን) ወይም ብሔረሰብን መሠረት ያደረገ የአሥተዳደር ሥርዓት ስናራግብ ስናቀነቅን እጅግ ለትዝብት በሚዳርግ ደረጃ ምን ያህል ያለንበትንና ተጨባጩን ሀቅ ያልተረዳን ማየት የተሳነን ጠባቦች እንጪጮች መሆናችንን ያሳያል፡፡ በእውነት እራሳችንን ልንታዘበውና ልናፍርም ይገባል፡፡ የተማርን ነን የምንል ከሆነም በትምህርት ሊለወጥ ያልቻለ አሳፋሪ ጥሬ ጎን እንዳለን እንወቅ፡፡
ዛሬ ላይ ይህ ሥርዓት ባመጣው መርዘኛ ስብከት ተከፋፍለን እኔ የእከሌ ነገድ ነኝ እኔ የእከሌ ብሔረሰብ ነኝ እኔ የእከሌ ጎሳ ነኝ እያልን በዐይነ ቁራኛ እንተያይ እንጅ እንደ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ማንነት፣ እሴቶቻችን ሁሉ በደምም ተቀላቅለናል ተቀያይጠናል ተዋሕደናል፡፡ በእርግጠኝነት ለመናገር እያንዳንዱ ዜጋ ነገዴ፣ ብሔረሰቤ፣ ጎሳየ ብሎ ከሚጠራው ሌላ በደሙ ውስጥ ቢያንስ የአንድና የሁለት የሌላ ነገድ፣ ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ደም በውስጡ አለ፡፡ የሦስትና የአራት ደም ያለበት ዜጋ በርካታ ነው፡፡ ማንነታችንን እራሳችንን የማናውቅ ወይም ተደብቆን ካልሆነ በስተቀር እኔ እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ነገዴ፣ ብሔረሰቤ፣ ጎሳየ ይሄ ነው ከምንለው ሌላ የሌላ ነገድ ብሔረሰብ ጎሳ ደም የሌለበት አንድም ሰው የለም፡፡ ይሄንን ለመረዳት የሚያስችል የአመለካከት አድማስ ስፋትና መረጃ ካላጣን በስተቀር ይሄንን እውነት መረዳት ቀላል ነው፡፡ እንዲያው በከንቱ ነው እየተናቆርን ያለነው፡፡
ብዙ ጊዜ ይሄ ችግር የሚፈጠረው የአብዝሐውን ቁጥር (majority rate) ይዘናል ከሚል የተሳሳተ ግንዛቤና በራስ መተማመን ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ የአገዛዝ ሥርዓት የወጡ የሥነ ሕዝብ መረጃዎች (statistical data) በአንድም በሌላም ምክንያት የተዛቡና የተሳሳቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ሥርዓት የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠረው አስፈሪ የዘር ልዩነትና በአንድ ዘር ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ዘር ማጥፋት እርምጃዎች ምክንያት በወቅቱና ከዚያም በኋላ እስከ አሁንም ድረስ እራሳቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲሉ “አማራነታቸውን” ለውጠው ደብቀው “ኦሮሞ” ነን ያሉ ከሰባት እስከ ዐሥር ሚሊዮን (አእላፋት) የሚደርሱ አማሮች ኦሮሚያ ብለው ከሚጠሩት የሀገሪቱ ክፍል ይገኛሉ፡፡ በሌሎቹም ሥርዓቱ “ክልል” ሲል በሚጠራቸው የሀገሪቱ ክፍሎችም ያሉ “የአማራ ተወላጆች” ሁኔታም ከዚህ ጋራ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ከሥጋት የመነጨ የማንነት ሽሽት የሠራው የፈጠረው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት እኔ አማራ ነኝ እኔ ኦሮሞ ነኝ እኔ ትግሬ ነኝ ወዘተ. የሚለውን ትክክለኛ ውጤት በከፍተኛ ደረጃ አዛብቷል፡፡ የጥፋት ኃይሎችንም ትክክለኛ ላልሆነ በራስ መተማመን ዳርጓል፡፡ በዚህች ሀገር ላይ ሕዝቡ ከምንም ዓይነት ሥጋት ነጻ ሆኖ ነኝ የሚለውን ነገድ ብሔረሰብ ጎሳ የመግለጽ ዕድል ቢያገኝ ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እኔ አማራ ነኝ እንደሚል አያጠራጥርም፡፡ እንግዲህ ይህ እንዳለ ሆኖ ከላይ ለማስረዳት እንደሞከርኩት ትክክለኛውና ተጨባጩ ሀቅ ግን አማራ ኦሮሞ ትግሬ ወዘተ. የሚባል ወይም ተብሎ የሚጠራ ማናቸውም ከማናቸውም ጋራ ያልተቀላቀለ አለመኖሩና ዘር የሚባለው ነገር ውሸት መሆኑ ነው፡፡ እናም ክትፎ ብቻውን የለም ዶሮ በቻውን የለም ሽሮ ብቻውን የለም ጥብስ ብቻውን የለም ፓስታ ብቻውን የለም ሌላም ብቻውን የለም ያለው ሁሉንም በአንድ ላይ የያዘው “ማኅበራዊ” ብቻ ነው ማኅበራዊያቹህን ብሉ፡፡
እስኪ ይሄንን ጉዳይ ጥቂት ማሳያዎችን በመጥቀስ ያለውን እውነታ ተጨባጭ እናድርገው፡፡ ሀገራችን ከ80 በላይ በሐውርት ባለቤት ናት እነዚህ ብሔረሰቦች አንደኛው ከሌላኛው እንዴት ባለ ሁኔታ እንደተዋሐዱ እንመልከት፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ ስንጀምር ባሕረ-ምድር ውስጥ (ባዕዳን ኤርትራ ይሏታል) ሐማሴን የሚባል የትግሬ ብሔረሰብ ክፍል አለ፡፡ ስለ የት መጣሽነታቸው ሲናገሩ ምን ይላሉ? ከበጌምድር (ጎንደር) የፈለሱ እንደሆኑና አማራ እንደነበሩ በጊዜ ሂደትና በታሪካዊ ኩነት ግን ወደ ትግሬነት እንደተለወጡ ይናገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ትግርኛቸው ከሌሎች ትግርኛ የተለየና የአማርኛ ተጽዕኖ ጎልቶ የሚታይበት፡፡ ከሰሜን ወደ ምሥራቅ ልውሰዳቹህና ሐረር ላይ ሐረርን የመሠረቱ የመጀመሪያዎቹ በጊዜ ሒደትና በታሪካዊ ኩነት ዛሬ ላይ ከቋንቋቸው እስከ የተቀረው መገለጫቸው ድረስ ተቀይሮ ሌላ የሆኑት ከሐማሴን ፈልሰው የሄዱ ትግሮች እንደሆኑ አለቃ ታየ ከ100 ዓመታት በፊት በታተመው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡
ከዚያው ከሰሜኑ የሐገራችን ክፍል ሳንወጣ ያ አካባቢ ከጥንት ጀምሮ የጠላት መግቢያ በር ከመሆኑ የተነሣ በተቀረው የሐገራችን ክፍል የሚኖረው ዜጋ ሀገሩን ለመከላከል ጠላትን ለመደምሰስ ወደዚያ ከትቶ እየሄደ አካባቢው የጦርነት አውድማ ሆኖ ኖሯል፡፡ የሩቁን እንተወውና የቅርቡን የደርግ ዘመኑን የአካባቢውን ገጽታ ብናይ በነበረው የተራዘመ የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ደርግ ከተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ወታደር መልምሎ በአካባቢው ያሰፍር ያሰማራ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ከደርግ ወታደር ባሕረ-ምድር (ኤርትራ) ወይም ትግራይ ካለች ሴት ጋር በጋብቻም ይሁን በሌላ ያልወለደ ብትፈልጉ ማግኘታቹህን እጠራጠራለሁ፡፡ አንዳንዱማ እንዲያውም ከአራት አምስቱ የወለደ ሁሉ አለ፡፡
ወደ ደቡባዊው የሀገራችን ክፍል ስንወርድ በዐፄ ምኒልክና በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ከውጭ ወራሪ ኃይል ጋር በተደረጉት ጦርነቶች መሥዋዕትነትን ከፍለው ሀገራቸውን ለታደጉ አርበኞች መንግሥት ደሞዝ አይከፍልም ነበርና እንደመካሻ አድርጎ ከኗሪው ዜጋ የተረፈ ወይም ሰፋፊ መሬት ወዳለው ዛሬ ኦሮሚያና ደቡብ ወደሚባለው የሀገራችን ክፍል መሬት ሰጥቷቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ አርበኞች (ነፍጠኞች) አማሮች ብቻ እንዳልሆኑ ልብ ይሏል፡፡ ከእነዚህ ነፍጠኞች ታዲያ ከዚያው ካለው ከተወላጁ ያልወለደ ነፍጠኛ (ባለ መሣሪያ) በመብራት ቢፈለግ አንድ እንኳን አታገኙም፡፡ እንዲሁም ዛሬ ኦሮሚያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አስቀድሞ የነበሩ ጎሳዎች በጊዜ ሂደትና በታሪካዊ ኩነት ተለውጠው ኦሮሞ ሆነዋል፡፡
ደቡብ ውስጥ ካሉ ብሔረሰቦች ጥቂት የማይባሉ ምንጫቸውን ስትጠይቋቸው ከበጌምድር (ጎንደር) እንደፈለሱ በጊዜ ሒደትና በታሪካዊ ኩነት ምክንያት ቋንቋቸውን ጨምሮ ብዙ ነገራቸው እንደተለወጠ ይነግሯቹሀል፡፡ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ቅኝ ገዥዎች መጥተው ሶማሊያ የሚባል ሀገር ፈጥረው አስቀሩብን እንጅ የታላቂቱ ኢትዮጵያ የውጭ ንግድ በሮች ከሆኑት ዘይላን ሞቃዲሾን ወዘተ. ለመጠበቅ በመንግሥታዊ ግዳጅ እየሔዱ እዚያው የቀሩ ዛሬ ላይ ግን ከሌላው ሱማሌ የማይለዩ ሱማሌ ሆነው የቀሩ ታሪክ ግን ታሪክ ነውና ስለማንነታቸው ሲናገሩ ከላይ ያልኩትን የሚያወሱ በሌሎቹ ዘንድም የጥንት ማንነት ሲነሣ በጎሲጥ የሚታዩ ዛሬ ላይ ከተለያዩት የሶማሌ ጎሳዎች የራሳቸውን ጎሳ የያዙ አሉ፡፡
ዐፄ ሱስኒዮስ ዐፄ ያዕቆብን ድል አድርገው የንጉሥነቱን ሥልጣን ሲይዙ ከሸዋ ይዘውት ከመጡት ጦር በተጨማሪ ለዚያ ላበቋቸው ከወለጋ ይዘውት ለመጡት የኦሮሞ ተወላጆች ጦር የጎንደርን ገዳማትና አድባራት ርሥትና ጉልት ከፊል ከፊሉን እየነጠቁ በተለያዩ የበጌምድር አውራጃዎች የእርሻ መሬት በመስጠት አስፍረዋቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ በእነዚያ የበጌምድር (ጎንደር) አውራጃዎች ያኔ የሠፈሩትን ወገኖች ልጆች ብትጠይቋቸው አማሮች ነን ይሏቹሀል እንጅ እኔ ኦሮሞ ነኝ ብሎ እራሱን የሚገልጽላቹህ አይደለም ይሄንን ታሪክ የሚያውቅ የሚኖር አይመስለኝም ካለም ከመቶ አንድ ቢኖር ነው፡፡ በጊዜ ሒደትና በታሪካዊ ኩነት ማንነታቸው ተቀይሯልና፡፡ እንግዲህ እነዚህ ጥቂቶቹና ከፊቴ ትውስ ያሉኝ ብቻ ናቸው ሌሎች በርካታ ተመሳሳይ ኩነቶች አሉ ሁሉ ቢዘረዘሩ ወረቀት የሚበቃም አይመስለኝም፡፡
እንግዲህ ይሄ ሁሉ አንዱ ነገድ፣ ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ከአጎራባቹ ጋራ አኙዋኩ ከመዠንግሩ አፋሩ ከሱማሌው ወዘተ. ጋር አብሮ ሲኖር በጋብቻ እየተሳሰረ የሚዋለድበትን ቋሚ የመዋሐጃ መንገድ ሳንቆጥር ነው፡፡ እንግዲህ እውነታው ይሄ ከሆነ ማን ነው አማራ? ማን ነው ኦሮሞ? ማን ነው ትግሬ? ማን ነው ጉራጌ? ማን ነው ሌላ? ለዚህ ነው ብሔር ተኮር ፖለቲካ የደነቆረና በተጨባጭ መሬት ካለው ሀቅ ጋር የማይጣጣም በሌለ ነገር ላይ የተመሠረተ ከንቱ ነገር ነው የምለው፡፡ በመሆኑም ዛሬ ላይ አማራ የለም፣ ኦሮሞም የለም፣ ትግሬም የለም፣ ጉራጌም የለም፣ ሌሎቹም የሉም፡፡ አማራ ከሌለ ኦሮሞ ከሌለ ትግሬ ከሌለ ጉራጌ ከሌለ ሌሎቹም ከሌሉ የአማራ ሀገር የኦሮሞ ሀገር የትግሬ ሀገር የጉራጌ ሀገር የሌሎቹም ሀገር የለም፡፡ ያለውና የሚኖረውም ሕዝብ “ሐበሻ” ነው ያለችውና የምትኖረውም ሀገር “ኢትዮጵያ” ብቻ ናት፡፡ አማራው ለብቻው ኦሮሞውም ትግሬውም ሌሎቹም ለየብቻቸው የኔ የራሴ የብቻየ የሚሉት የሚካለሉት መሬት የሀገር ክፍል የለም፡፡ ሐበሻ ማለት የአቢስ ሕዝብ ማለት ነው አቢስ ከጥፋት ውኃ በኋላ ከነገሡት ከመጀመሪያዎቹ አንዱ ነው፡፡ ከሱም ስም የተነሣ ሀገራችን አቢሲኒያ (የአቢስ ሀገር) ተባለች ሐበሻ ማለት የተደባለቀ ሕዝብ ማለት ለው የሚሉም አሉ፡፡
እናም ወገን ሆይ በሚገባ የምናውቀውን ነገር ግን ያልተቀበልነውን እውነት ተቀብለን መኖር ለእኛ ብቸኛው መፍትሔ ነው፡፡ ይሔንን በደም ተሳስሮ ተዋልዶ ተዋሕዶ ያለውን ደማችንን ማንነታችንን አውቀንና አክብረን እኔ እከሌ የሚባለው ነገድ ብሔረሰብ ጎሳ ነኝ እያልን ዛሬ ላይ በአካል የሌለ ነገድ ብሔረሰብ ጎሳ እየጠራን መከፋፈሉን መቧደኑን መናቆሩን ጣል እርግፍ አድርገን ትተን እውነት የሆነውን ዛሬ ላይ በአካል ያለውንና ወደፊትም የሚኖረውን ተጨባጩን ሐበሻነት አንድ ደምነት ይዘን እንነሣ፡፡ ያኔ እንደምቃለን፣ እንበራለን፣ እንፈካለን፣ እንደ ብረት እንጠነክራለን፣ እንከብራለን፣ እንበለጽጋለን፣ ሰላምና ፍቅርን እንጠግባለን እንደ ሸማ እንከናነበዋለን፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ካለን የምናጣው ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ከእግዚአብሔር የተሰጣት የተተወላት ብቸኛው የመዳኛ መንገዷ ነው፡፡ ይሄንን እውነታ (አንድ ደምነት) ሊያስተባብል የሚችል አንድም ነገር እስከሌለ ጊዜ ድረስ ይሔንን መንገድ ላንቀበል የምንችልበት አንድም ጤናማ ምክንያት የለምና ይሄንን እውነት እንመን እንኑርበትም እንጠቀምበታለን እንጅ አንጎዳበትም እንድንበታለን እንጅ አንጠፋበትም፡፡ የዚህችን ሀገርና ሕዝብ ህልውና የሚመኝ የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ ይሄንን እውነት ሳያቅማማ ይቀበላል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር ይህ የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ነው ማለት እንችል ይመስለኛል፡፡
በእርግጥ አዎ ይሄ አስተሳሰብ የማይጥማቸው እራሳቸውን ለጠላቶቻችን የቀጠሩና በጥፋት ኃይልነት ያሰማሩ ይኖራሉ፡፡ ለእነኝህ ወገኖቻችን አንዲት ጥያቄ ላቅርብ፡፡ እንዲህ የምትሆኑላቸው ባዕዳን ከራሳቹህ ይበልጡባቹሀልን? እባካቹህ ዐይናቹህን ግለጡ የምናተርፍበትን እንጅ የምናጎድልበትን፤ ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበትን እንጅ ማናችንም ተጠቃሚ የማንሆንበትን አማራጭ እንደ አማራጭ ለመውሰድ ፈጽሞ አትፍቀዱ፡፡ ግድ የላቹህም የያዛቹህት መንገድ የጥፋት ነውና ተውት፡፡ እስኪ ሰይጣን ይፈር እንቢ በሉት ለራሳቹህም ቢሆን የማይጠቅም ነውና፡፡ ይህ እውነታ ከእናንተ የማሰብና የመረዳት አቅም በላይ ይሆናል ብየ አልገምትም፡፡ መሆን አለመሆኑን በቀጣይ ግዜያት በምትሰጡት ምላሽ ወይም እርምጃ የምናውቀው ይሆናል፡፡ ከግል ጥቅም የሀገር ጥቅም ይቅደም፡፡ የሀገር ጥቅም ካልቀደመ የግል ጥቅምም አይኖርምና፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
satenaw

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.