ዳዊት ዳባ
ህዘባዊ እንቢታ ማለት ዜጎች የስርአት ለውጥን ሆነ መብታቸውን ለማስከበር በብዙ ቁጥር ሆነው በጋራ አንድን ነገር ማደረግ ወይ አለማድረግ ነው። አለቀ። ብብዙ ቁጥር ተቃውሞ አደባባይ መውጣት በጋራ ልናደርጋቸው ከምንችላቸው በትንሹ ከሺ ነገሮች ውስጥ አንዱ የህዝባዊ ተቃውሞ አካል ነው። ተቃውሟችንን ለመግለፅ በጋራ ልናደርጋቸው የሚቻሉን ነገሮች ሁሌ የግድ ከባድም አጋላጭም መሆንም የለባቸውም። በይበልጥም ስንጀምረው።
ማወቅ ያለብን አምላክ የሰውን ልጅ ሲፈጥር እስከነፃነቱ እንዲሆን አልሞ ነው። ሲፈጥረው ባስፈለገው ጊዜ አፈጣጠሩን በሙሉ ነፃነቱን ማስጠበቂያ አድርጎ እንዲጠቀምበት ነው። ሀሰት የሚል ካለ ይህንን አፈጣጠሩን ነፃነቱንና መብቱን ማስከበርያ አድርጎ ሊጠቀምበት አይችልም ይበል። እኛም ኢትዬጵያዊያን ሰዎች ነን። የሰው ልጅ እንደመሆናችን ስሜታችንን ፤ አካላዊ እንቅስቅሴያችንን፤ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ አካላችንን ፤ድርጊታችንን፤ አኗኗራችንን፤ የማሰብ ችሎታችንን፤ ፍላጎችንን፤ድምፃችንን ብቻ ሁለንተናዊ አፈጣጠራችንን መጠቀሙን እናውቅበታለን አናውቅበትም ነው እንጂ ጉልበታሞችን ልክ ማስገቢያ ካምላክ የተሰጠ ሀይላችን ነው።
ነፃነቱን ገፋፊው አንድ ግለሰብ ሲሆን ተገፋፊው ይሰራል ያለውን አፈጣጠሩን ተጠቅሞ በመዝጋትም ሆነ ልክልኩን በመንገር እንደሁኔታው አናቱን በድንጋይ በመበርቀስ ነፃነቱንና ክብሩን ማስመለስ ይችላል። ነፃነቱን የቀማው መንግስት ሲሆን ግን ብቻውን ሆኖ አደባባይ ላይ ወጥቶ በመጮህ ሆነ ተኩሶ እንዳሰበው ተፅኖ ፈጣሪና ውጤታማ ትግል ለማካሄድ ሁሌ የተሳካ ላይሆን ይችላል። በወረደ ምሳሌ፤- አንድ ሰው ብቻውን አገዛዝን ለመታገያና ተቃውሞውን ለመግለፅ አስቦ እደጅ ቢፀዳዳስ። ሲጀመር እስከጭራሹ ለምን እንዳደረገውም ላይታወቅ ሁሉ ይችላል። ነግር ግን ነፃነታቸውን የተነፈጉ በሙሉ አንድ ቀን ወስነው እጅ ለእጅ ተያይዘው እደጅ ቢፀዳዱስ። ይህ በቀጥታ ነቅንቅ የሆነ ተቃውሞ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ አይገባም። { አይዞን ምሳሌ ነው። ካስፈለገ ተባብሮ ማፅዳቱንም ቀጣይ የተቃውሞ አይነት ልናደርገውም እንችላለን }።
ወያኔ ምርጫውን የትላልቅ ልጆችች እንኳ ሳይሆን የሚጢጢዎች እቃቃ ጫወታ አደረገው አይደል!። የሚፈለግ ነው። ፋይዳው ይህን ያህል ነው እንጂ ስለማሳጣት ከሆነ ከዚህ በላይ ያማያሳጣ የተዘርበጠበጠ ነገር ታይቶም ተሰምቶም የሚታወቅ አይመስለኝም። ለለውጥ እየታገለ ባለው ክፍል አላማው በዋናነት ማሳጣት ስላልሆነ ግን አሁንም ወጥሮ መያዝ ነው። ይህ መዘርጠርጥ የት ሊዶል እንደሚችል ማን ያውቃል። አሳምርን እንደምናውቀው ወያኔዎች ምርጫ ተካሂዷል። በውጤቱም እንደእስካሁኑ በቃ አሸናፊ እኛ ነን ብለው ፋይሉን ሊዘጉ የሚችሉባቸው በድንብ የሚያውቋቸው ሌሎች መንገዶች ነበሩ። በዛ ላይ ተቃዋሚዎች በአፈናው ምክንያት ተዳክመው ባሉበት። ያበረና ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሌለ እኛም እነሱም እያወቅን። ታዲያ ይህ ሁሉ ቦኩሀራማዊ(ለመረዳት አስቸጋሪ) እርምጃ ለምን? ለሚለው መልስ ለመስጠት ስንሞክር ብቻ ነው በእጅጉኑ ያሰፈራቸው ጉዳይ እንዳለ የሚገለፅልን። ከዚህ ውጪ የሆኑት ሌሎቹ መንገዶች በሙሉ አስበውበት የፈሩትን ነገር ሊያስከትል የሚችሉበት የተሻለ እድል ያላቸው ሆነው ታይቷቸዋል ማለት ነው ብለን በእርግጠኛነት እንድናምን የሚያደርገን። ታዲያ የፈሩት ምንድን ነው?።
በበዛው ዜጋ ዘንድ ከፍተኛ ምን አልባትም መጨረሻው ደረጃ የደረሰ የታመቀ ቁጣ አለ። ለብዙዎች መራብ ደረጃ የደረሰ የመረረ ችግረር አለ። መሰልቸት አለ። በውርጂብኙ በቀጥታ ተጎጂ መሆን አለ። መረን የለቀቀው አዶሎ ለሁሉም ዜጋ ሰውነት የሚያመነምን ደዌ ሆኗል። ይህንን አይነቶቹ ህዘብ እንዲያምፅ የሚያደርጉ ምክንያቶች ፈልትው ፈልተው ያሉበት ሁኔታ ማንም ቢገመግመው የሚደርስበት ተጨባጩ የአገራችን እውነታ ነው። የሰሞኑ ቦኩሀራማዊ ድርጊቶቻቸው ሁሉ ገላጭነቱ ይህንን ዜጋው እንዲያምፅ ሊያደርገው የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለክተው ደረጃውን አሳምረው ማወቅ መቻላቸውን ነው የሚያሳየን። ልናምፅ ይሆናል የሚለው ሀሳብ እጅጉኑ እንዳስፈራቸው የሚያመላክት ነው። በየትኛውም አገር ምርጫ ብዙ ዜጎች በቀጥታ ተሳትፎ የሚያደርጉበትና ፖለቲካዊ ትኩሳትና መነቃቃት የሚጨምርበት ጊዜ ስለሆነ አጋጣሚውን ተገን አድርጎ የታመቀው ቁጣችን ይፈነዳል የሚል ድምዳሜ ላይ አስረግጠው መድረሳቸውን ያሳያናል።
ያም ሆኖ በነሱ በኩልም ሆኖ ለማየት ቢሞከርም ያዋጣል ብለው ከያዙት ፈላጭቆራጭ ከሆነው መንገድ ውጪ ሌላ አይነት የተሻለ መንገድ አልነበረም ማለት ግን አይደለም። የሚያሳየን የፍራቻቸውን ጥልቀትና እውነተኛነት ነው። ባዛ ላይ የምናወራው ለጉድ ስለነገሱብን ስለወያኔዎች ነው። ከደረጃቸውና ከባህሪያቸው አኳያ ሌላው መንገድ አዋጭ ሆኖ ሊታያቸው ባይችልም አይገርምም። ስለዚህም በወሰዱት እርምጃ የምናለቅስበት መሆን የለበትም። ካወቅንበት ጠሩም ጠቃሚም ነው። በእርግጥ አዛላቂና አዋጭ እየሆናቸው ይቀጥል ወይ?። ሁላችንም በቶሎ መልስ ልንሰጥበት የሚገባ ጥያቄ ነው። ይህ የታመቀ የህዝብ ስሜት በምን መንገድ?፤ በምን ጥንካሬ?፤ በምን አይነት አብሮነት?፤ በምን አይነት አመራር? ይተገበራል በሚለው የሚወሰን ይሆናል። በይበልጥ በተሻለ ነፃነት ውስጥ በሚሰሩ ድርጅቶች ሁኔታውን መጠቀም መቻል ጋር። ለለውጥ የቆሙ ሜዲያዎች ሁሉ ህዝባዊ እንቢታውን እውን በሚያደረግ መንገድ በዋናነት መቃኘት መቻል ጋር። ትግሉ ላይ በየትኛውም መንገድ ጎልቶ የሚሰማ ተፅኖ አሳዳሪ ድምፅ ያላቸው ዜጎች ዋና ትኩረት መሆን መቻል ጋር በቀጥታ ይያዛል።
አገር ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች ያለው ሁኔታ በሚፈቀደው ጥሩ ይዘዋል። አሁንም ያለው አማራጭ አበርትቶ አዳዲስ ፈጠራና ማሰብ በታከለበት መቀጠል ነው። ዛሬም የዚህ ጥረት ፋይዳ ላልታየን ግን አገር ውስጥ ሆነው፤ ለዛወም በቀጥታና በዋናነት የሚቀጠቀጡት እነሱ ሆነው ሳለ የተያያዙት ትግል መከራ ስለበዛበት ብቻ ትተን አንቀመጥም። ምርጫውንም ወጥታችሗል እስክንባል አንጫወተዋለን ማለታቸው ትክክል ናቸው። የትግሉ ሻማ እንደበራ ሲቀጥል ብቻ ብዙዎቻችንን ጨምሮ ትግሉ መሰረታዊ ባህሪውን ቀይሮ ወደ ህዝባዊ ንቅናቄ እንደሚቀየር አሳምረው ስለወቁ ነው። በእርግጥ ሂደቱን ያፈጥኑ የነበሩ ጉዳዬች ገና አልተሟሉም። ህዝባዊ እንቢታው ባለቤት የለውም። ባብዛኛዎቻችን ለአፍ እንጂ ዋና ትኩረት ገና አልሆነም።
ይህም ሆኖ የምርጫውን ሂደት ትግሉን በሚጠቅም መንገድ መጠቀምን በተመለከተ በዜጎች በኩልም ልንመዛቸው የምንችላቸው ጥሩ ጥሩ ሾጥ ማድረግያ ዱላዎች አሁንም አሉት። እየመዘዝን በመጠቀም አስቸጋሪም ግራ የሚያጋባቸው፤ ተስፋ አስቆራጭ እንዲሆንባቸው ማድረግ የምንችልባቸው። ተናበን የምርጫ ካርዳችን ላይ “ እናታችሁ አፈር ትብላ “ብለን ፅፈን ወርውረንላቸው መውጣት ችለን ከነበረ አሁንም በተመሳሳይ በጋራ የምናደርገጋቸውን ነገሮቸ ማሳደግና ይህን አይነቱ በጋራ ልናደርጋቸው የምንችላቸው የተቃውሞ አይነቶች ላይ መካን ነው የሚፈልገው።
በጥቂቱ ምርጫ ውስጥ ያሉ ታቃዋሚዎች ቀን ቀጥረው ወደኛ ሁሌ እንዲመጡ አንጠብቅ። እኛ በብዙ ቁጥር በየጥያቄዎቻችንና ብሶቶቻችን ተቧድነን ወደነሱ እንሂድ። ይሄ አንድ ክፉየሆነ ሾጥ ማድረግያ ድላ ነው። ተቃዋሚዎቹም የሚቻልና ብዙ መሆናችንን ሲያዩ ለምርጫ ቅስቀሳም ብለው ይሁን ትኩሳቱን ለማታለቅ ቀጠሮ ይዛው ሊያገኙን የምርጫው ሂደት ከለላቸው ነው። ያኔ ደግሞ ግልብጥ ብለን አደባባዩ ላይ እንፈስና አስደንጋጭ እናደርገዋለን። ቀላሉ ደግሞ ምርጫ አለ እስካሉ ሁላችንም ስለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ማውራት የተፈቀደም የምንችለው ነው። ሆን ብለን በአንመርጥህም፤ በአትመረጡም ወሬ አገሩን ከነገ ጀምረን መሙላት እንችላለን። ትግል አድርገን ከያዝነውና ሁላችንም ከተሳተፍንበት ማውራቱ ብቻ በራሱ እንኳን ለዶሮ ለለአንበሳም ፈንጋይ ነው። ስለምርጫ ማውራት አሸባሪነት ነው። በሞት ያስቀጣል የሚል አዋጅ ያወጡና ደግሞ ያኔ ሙድ እንይዝባቸዋለን። ተመስገንን በማሰብ ሁላችንም ሻርብ አንገታችን ላይ ጣል ለሳምንት ማድረግ እንችላለን። ይህን አይነት አንድ ሺ በጋራ ልናደርጋቸው የምንችላቸውን ቀላል ነገሮች መዘርዘር ላሰበብት በጭራሽ ከባድ አይደለም።?።
ይህን ወይ ያንኛውን ተቀናቃኝ ከምርጫው አገደ። ይልቃልን ወይ ወይንሸት “በእጣ” ምርጫውን እትወዳደሩም አሏቸው። ይህን ስለ አንድነት ፓርቲ ወይ ሰለሰማያዊ ፓርቲ ወይ ስለወይንሸት አድርጎ የሚወስድ ካለ ኢትዬጵያዊ ሆኖ ባልተፈጠረ ይሻለን ነበር። ለክብሩም፤ ለነፃነቱም ለመብቱም ዋጋ አይሰጥምና። ጭራሹኑ እየተደረገ እየሆነ ያለው የገባውም የሚገባውም አይደለምና።
በግልፅ መታወቅ ያለበት አማራጭ አትሆኑም ብለው የከለከሏቸው ጊዜ ያኔ ስለነሱ መሆኑ ያቆማል። ስለኛ ስለዜጎች ሆኗል። ቢገባቸው ለወያኔ ደጋፊዎችም ጭምር። ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን አገደ ወይ ከለከላቸው ማለት ምርጫዎቻችን ልናደርጋቸው እንችልም ማለት አይደለም። ሁለተኛ ዱላ በሉ። ምርጫዎቻችን መሆናቸውን ሊደበቅ በማይችል ተሸናፊም በሚያደርግ መልኩ አለም ሁሉ እንዲያውቀው ማሳየት አንችላለንና። መምረጫ ካርዳችንን ወደላይ በጃችን ይዘን። ደረታችን ላይ የተከለከሉትን ድርጅቶች ወይ ግለሰቦች ፅፈን። በነቂስ ወጥተን በየምርጫ ጣቢያው ለመምረጥ መሰለፍን ማን ነው የሚከለከልን። ወያኔ እንደተጨማለቀ የምርጫው ሂደት ይቀጥላል እስካለ ልናደርገው የሚቻለን ሌላ አሀ ብለን ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ኮሮጆ ገልብጦ አሸንፌያለው ለማለት ያቆበቆበ ባለበት ምርጫችንን በሆዳችን በድብቅ የሞኝ ነው። ድምፃችንን ለቀማኛ ያለምንም መግተርተር እንዳሻችሁ ብሎ መተው ይሆናል። በመጨረሻ የተሻለ ውጤታማ ነው ተብሎ ውሳኔ ላይ ከተደረሰበትና ከታዘዝን ደግሞ የምርጫውን ቀን በቤት ዘና ስንል የምናሳልፈው የእረፍት ቀናችን ማድረጉንስ ማን ከልክሎን?።
ይህን አይነቱ ትግል በዚህ ዘመን በየሰኮንዱ ጢዝ ስሊ መረጃ እጃችን ላይ በሚመጣበት ዘመን ማስኬድ ቀላል ነው። በጋር ሆነን የምናደርጋቸው ተግባራትና ድረጊቶች ወሳኝና ጉልበታም ናቸው። አይደለም በጋራ ሁላችንም አድርገነው ልባሞች ብቻቸውን ሆነው ጊዜ፤ ቦታና ሁኔታዎችን አመቻችተው የሚያደረጉት ትግል ምን ያህል ነቅንቅ ሊሆን እንደሚችል በተደጋጋሚ አይተናል። በዛ ላይ በጋራ ማድርግ እንደሚቻል ለማስረገጥ እርቀን ከሌሎች ተጨቋኝ ህዝቦች ተሞክሮ ማፈላለግ የለብንም። በዚሁ ዘመን እኛው አገር የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ከዚሁ ክፍል ጋር ውጤታማ በሆነ መንገድ ሲታገሉበት እያየን ነው።
ነጻነታችንን አብዝተን ተርበን ከሆነ። ማልቀሱን ትተን አንድ ነገር ልናደርግ ከወሰንን። የሁላችንንም ተሳትፎ ያለበትን ናፃነታችንን የምናውጅበትን መንገድ በዝርዝር ነግሮን ሲጨርስ ነው የታሰረው። የሚጨመር ነገር የለውም። ህዝብ ውስጥ ስላለና የብሶቱን ደረጃ በየቀኑ መለካት ስለሚችል አደባባዩን አሁኑኑ። ይህን ቁጣ ይዞ በገፍ ፍቱን መድሀኒት መሆኑን ነግሮናል። እነሱ ሊመሩት ይችላሉ ያላቸውም ክፍሎች ነበሩ። የትግሉ እራስ የት እንዳለ ባይታወቅ ይሻላል። ደግሞስ በውጪስ ቢሆን የሚለው አማራጭም በእርግጥ አለ። ይሄንኛው መንገድም የዋዛ እንዳልሆነ ታይቷቸው ለዚህ አይነቱን ትግል ላይ ሀላፊነት ለመውሰድ በሚመስል ወደፊት እየመጡ ያሉ ድርጅቶች አሉ። እሰየው ነው።
እንኳና ብዙ ሆነን በሰሞኑ የውሸቱ ሲኖዶስ መሪ ላይ ጫማ መወርወሩ ሀይለኛ ተቃውሞ ነበር። የሚያሳዝነው ከዚህ በላይ ልናጮህው እንችል ነበር። ግለሰቡ ሲደርገውም ይህን ገምቶ የነበረ ይመስለኛል። ምን ያደርጋል ከነሱ ጎጥ ስለሆኑ ሰውዬውን ፀሀይዬ አፈላልጎ ስልጣኑ ላይ እንዳስቀመጣቸው እያወቁ መንፈስ ቅዱስ ፀሃይዬ ላይ አድሮስ ቢሆን የሚሉ በቃ” የዋሆች” ብዙ ስለሆኑ ሳይካበድ ቀረ። በዛ ላይ ደግሞ ያገዛዙ ሰዎችና ጥራዝ ነጠቆች ተረባርበው ሴትን ልጅ እርጉዝ ነኝ እያለችው ሆድ ቀጥቅጦ ፅንስ ማስወረድ ባህላችን ይመስል የኛ ባህል አይደለም ጫጫታቸውን በቶሎ ጣርያ አስነኩትና ጥረቱን ገደሉት። ከዚህ በፊት ያ መናጢ የሞተ ጊዜ የምናዝንበት መንገድ እንጂ ማዘን ወይ አለማዘን የስሜት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ ባህል እንዴት እንደሆነ ባይገባንም ባህላችን አይደለም ተብሎ ስንሞገትበት እንደነበረው ማለት ነው።
ወንዱሜ አጋጣሚዉን ደግመህ ካገኘህ ሌሎቻችንም ብንሆን ጫማ አይደለም ካልሲ ጨምራችሁ ወርውሩ። ለማሸነፍ ለሚታገል የተቃውሞ ትንሽ የለውምና። እንደውም ውጤት እንዲኖረው ተደርጎ ያልተሰራ የትግል አይነትና ተቃውሞ እንጂ የማይስራ የሚባል ነገር የለም። አንዱ የትግል አይነት ከሌላው ጋር ተዛማጅ፤ ተባዥ፤ ተጋጋዥ ነው። ማሸነፍን ከፈለግን የሚጠቅመን ካልሲ መወርወር እንዴት? መቼ? በምን አይነት ሁኔታ? ቢወረወር የተሻለ ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ሁሌም ማስላትና ነው።
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.