Friday, April 17, 2015

የደቡብ አፍሪካው የስደተኛ ጠልነት መነሻው ምንድነው? (የሰባት ኪሎ ወቅታዊ አጭር ትንተና)

ethiopia south africa


ደቡብ አፍሪካን በቅርቡ የማይከታተሉ ሰዎችን በእጅጉ ያስደነገጠ ቢኾንም በአገሪቱ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ኹከት ሲካሄድ የአሁኑ የመጀመርያው አይደለም። እ.ኤ.አ በግንቦት ወር 2008 አሌክሳንደር በተባለ የጆሃንስበርግ ታውንሺፕ የተነሳ ኹከት ወደ ደርባን እና ሌሎች ከተሞች ተዛምቶ ቢያንስ ለዐርባ ስደተኞች መሞት ምክንያት ኾኗል። በኹከቱ ብዙ ንብረት ወድሟል። ከዚያ በፊት እና በኋላም ቢኾን ሌሎች በርካታ አነስተኛ ጥፋቶች ተፈጽመዋል። ይህ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው “በጉርብትና የሚኖሩ ሰላማዊ ስደተኞችን በእንደዚህ ዐይነት ጭካኔ ማቃጠል፣ መግደል እና መደብደብ ለምን?” የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳል። በደቡብ አፍሪካ እንዲህ ዐይነት ከፍተኛ የኾነ ስደተኛ ጠልነት ለምን ተስፋፋ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ምናልባትም ወደ አገሪቱ የመጀመርያዎቹ የዴሞክራሲ ዓመታት መለስ ብሎ መመልከት አስፈላጊ ነው።
gejera south africa
ከኻያ ዓመታት በፊት አፓርታይድ ተገርስሶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ሲጀመር በደቡብ አፍሪካ ሁለት ነገሮች ተፈጠሩ። በመጀመርያ ብዙኃኑ ጥቁሮች ከጥቂት ነጮች ጭቆና ተላቀው እነርሱ በመረጡት መንግሥት አስተዳደር አማካኝነት ከነበሩበት የኢኮኖሚ ችግር እንደሚወጡ ተስፋ ሰነቁ። በጊዜው የወጡ የሕዝብ አስተያየት ጥናቶች እንደሚያሳዩት በርካቶች ከነጭ ሀብታሞች ተቀንሶ ለድኾች የሚሠጥበት የኢኮኖሚ መልሶ ማከፋፈል (economic redistribution) ይኖራል የሚል ተስፋ ነበራቸው። ከፍ ያለ የትምህርት ዕድል፣ ቀስ በቀስ የሚያድግ ገቢ፣ የተሻለ የመኖርያ ቤት የማግኘት ፍላጎት ጨመረ። በሌላ በኩል በተለይ በምዕራብ አገሮች መንግሥታት እና ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ አዲሱ ዴሞክራሲ የንብረት መብትን ይሸረሽራል፣ የኤኤንሲ መንግሥት ከመራጮች በሚመጣ ጫናም ይኹን በውስጥ ፖለቲካው ምክንያት መልሶ ለማከፋፈል ሲል ንብረት ይወርሳል፣ ከባድ ግብር ይጥላል ወዘተ . . . የሚል ስጋት ነበር።
ይኹንና የድኻ ጥቁሮች ተስፋም ይኹን የሌሎቹ ስጋት እውን አልኾነም። ማርቲን ፕላውት እና ፖል ሆልደን “Who rules South Africa?” በሚል መጽሐፋቸው እንደሚያትቱት ኤኤንሲ ሥልጣን ላይ እንደወጣ ከወሰዳቸው የመጀመርያ ‘ርምጃዎች መካከል አንዱ እ.ኤ.አ በ1955 የነጻነት ቻርተር ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ይዞት የቆየውን ሶሻሊስታዊ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ትቶ በቅይጥ ኢኮኖሚ መተካቱ ነበር። የቅይጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎቹም ቢኾኑ ብዙም ተግባራዊ ሳይደረጉ ተራግፈዋል። ግራ ዘመም የሚባለው እና በኔልሰን ማንዴላ ይደገፍ የነበረው መልሶ የመገንባት እና የልማት ፕሮግራም (Reconstruction and Development Programme) ለሁለት ዓመታት እንኳን በቅጡ ተግባራዊ ሳይኾን በጊዜው ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩት እና አሁን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየተዘዋወሩ ‘ኒዮ-ሊበራሊዝምን እቃወማለሁ’ እያሉ በሚናገሩት ታቦ ምቤኪ ውትወታ ወደ ቀኝ ባዘመመው የዕድገት፣ የሥራ እና የመልሶ ማከፋፈል ስትራቴጂ (Growth, Employment and Redistribution Strategy) ተተካ። በመጀመርያው ፕሮግራም ተጀምረው የነበሩ የመኖርያ ቤት አቅርቦት ፕሮጀክቶች፣ ለድኾች የሚሰጡ የተለያዩ ድጎማዎች፣ የመጠጥ ውሃ፣ ንጹሕ የመጻዳጃ ቤቶች እና መብራት ማስፋፋት በሁለተኛው ፕሮግራም እየተዳከሙ መጡ። እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ለድኻ ደጋፊ ፖሊሲዎች ብዙ ቁብ ያልነበረው የዓለም ባንክ ሳይቀር ይህ የፖሊሲ ለውጥ አስጨንቆት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት መጠነኛ ማሻሻያ እንዲያደርግ ምክር ለግሶ ነበር። ኤኤንሲ ሥልጣን ላይ ከወጣ ከዐሥር ዓመታት በኋላ በአገሪቱ የተመዘገበው ኢ-እኩልነት እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ እና በ1980ዎቹ በአፓርታይድ ሥርዐት ወቅት ከነበረው ጋር ተስተካከለ። ከዚያም በኋላ ብልጫ አሳየ። የሚገርመው ኢ-እኩልነቱ በፍጥነት የጨመረው የደቡብ አፍሪካ አማካይ ዕድገት አመርቂ ነው በሚባልበት ወቅት ነበር። ድህነት ቀነሰ ቢባልም ፍጥነቱ እጅግ ዝግ ያለ ነበር። በርግጥ ጥቂት ጥቁር ልሂቃን እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ነጋዴዎች በተለይ የጥቁሮችን የኢኮኖሚ ኃይል ለማሳደግ በወጣው Black Economic Empowerment ፖሊሲ ተጠቅመው የበለጸጉ ቢኾንም ለብዙኃኑ ደቡብ አፍሪካውያን አዲሱ የዴሞክራሲ ሥርዐት ያመጣው የኢኮኖሚ ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዚህም ምክንያት የብዙዎች ተስፋ ተቀጨ። ቁጣ እና ንዴት ጨመረ፤ ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና የአገልግሎት አቅርቦት ችግር ተስፋፋ፣ በየታውንሺፑ በየጊዜው የሚደረጉ ከአገልግሎት አቅርቦት ችግር ጋራ የተገናኙ ዐመጾች ተበራከቱ። ለዚህ እና ለሌሎች ኢኮኖሚ ነክ ዐመጾች መንግሥት የሚሰጠው ምላሽ አንዳንዴ እንዳልተፈጠሩ እና እንዳልነበሩ አድርጎ መርሳት፣ አንዳንዴ ኃይል የተቀላቀለበት ጨካኝ ርምጃ መውሰድ፣ ምርጫ ሲደርስ ደግሞ ሥንዝር ጉቦ እየሰጡ ለማማለል መሞከር ነው። ለምሳሌ፦ እ.ኤ.አ ነሐሴ 2012 የደሞዝ ጭማሪ የጠየቁ በማሪካና አካባቢ በማዕድን ቁፋሮ ላይ የተሰማሩ ጥቁር ሠራተኞች ላይ መንግሥት ተኩስ ከፍቶ 34 አድመኞችን ሲገድል 78 አቁስሏል።
Gejera south africa
ደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲ ስትጀምር ሌላው የተፈጠረ ነገር ወደ አገሪቱ የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር (በተለይ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት) በፍጥነት መጨመር ነበር። የኤኤንሲ መሪዎች ቀስተ ደመናዋ አገር (the rainbow nation) የሚል አገሪቱ ብዙ ዘሮች፣ ብሔረሰቦች እና ጎሳዎች በሰላም፣ በፍትህ እና በፖለቲካ እኩልነት የሚኖሩባት መኾኗን የሚያበስር አካታች (inclusive) መመርያ ይዘው ሥልጣን ላይ ወጡ። በርግጥ ይህ አካታች እሴት የሚመለከተው ደቡብ አፍሪካውያንን ብቻ ይኹን ወይም የውጪ ዜጎችን ይጨምር ግልጽ አልነበረም። በደንብ አልተተነተነም፤ ክርክር አልተደረገበትም። ነገር ግን በተለይ በዴሞክራሲው የመጀመርያ ዓመታት የኮንግረሱ አመራሮች በተግባር ሐሳቡ የውጪ ዜጎችንም እንዲጨምር አድርገውት ነበር። በእነዚሁ ዓመታት ለበርካታ ስደተኞች የመኖርያ ፈቃድ ተሰጥቷል። ደቡብ አፍሪካ ነጻነቷን ስትቀዳጅ በብዙ የአፍሪካ አገራት የፖለቲካ ግጭት እሳቶች ይነዱ ነበር። ከእነዚህ ግጭቶች የሚያመልጡ በርካታ ስደተኞች አገሪቱን መጠለያ አደረጉ። በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ ከብዙ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ የኢኮኖሚ የዕድገት ደረጃ ላይ ያለች እና የገቢ መሻሻል ዕድል የምትሰጥ በመኾኗ የኢኮኖሚ ስደተኞች ማግኔት ኾነች። ከሞዛምቢክ፣ ከዚምባቡዌ፣ እና ከኮንጎ በነፍስ ወከፍ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ አገሪቱ ገቡ። ከምዕራብ እና ምሥራቅ አፍሪካም ቢኾን ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀኑ። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ቀያቸው ያደረጓቸው ጥቁር ድኻ ደቡብ አፍሪካውያን የሚኖሩባቸውን ታውንሺፖች ነው። የስደተኞቹ የኢኮኖሚ ኹኔታዎች ከፍ እና ዝቅ ያለ ቢኾንም ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህ ስደተኞች በታውንሺፖች ያሉትን የኢኮኖሚ ችግሮች እና ኹከቶች ለመቋቋም ጠንካራ የዋስትና ማኅበራዊ መረቦችን ዘርግተዋል፤ በጥቃቅን ንግዶች እና በጥቁር ኢኮኖሚ በብዛት ይሳተፋሉ፣ እጅግ በዝባዥ በኾነ ዋጋ ተቀጥረው ሥራ ለመሥራትም አያቅማሙም።
በብዙ አገራት እንደምንመለከተው እነዚህ ሁለት ነገሮች- በመንግሥት የፖሊሲ ክሽፈት የተባባሰ ድህነት፣ ተስፋ መቁረጥ እና መጠነ ሰፊ ስደት- ሲገናኙ ማኅበራዊ ፈንጂ የመፈጠር ዕድሉ ከፍ ይላል። ፖለቲከኞች (ከፍተኛም ይኹን ዝቅተኛ እርከን ሥልጣን) በራሳቸው ድክመት የመጣ ችግርን ለመሸፈን ጣታቸውን ስደተኞች ላይ መጠቆማቸው ያልተለመደ ድርጊት አይደለም። በግጭት የሚጠቀሙ ነጋዴዎች (conflict entrepreneurs) ይህን አጋጣሚ አያልፉትም። ለምሳሌ፦ በ2008ቱ ኹከት ላይ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከኤኤንሲ ቀበሌ አደራጆች እስከ የታውንሺፕ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ መዋቅር አንቀሳቃሾች በኹከት ቅስቀሳ ላይ ተሰማርተው ነበር። እነዚሁ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የደቡብ አፍሪካውያን የአገልግሎት አቅርቦት ጥያቄዎች ሲጨምሩ- የመዋቅሩ መሪዎች ድጋፍ እና ተደማጭነት እያሽቆለቆለ ሲመጣ – ስደተኞች ላይ የሚያደርጉት ቅስቀሳ ያይላል። የቅስቀሳዎቹ ዋነኛ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦ የደቡብ አፍሪካ ድኾች ከችግራቸው ሊወጡ ያልቻሉት ሥራቸውን በስደተኞች ስለሚነጠቁ ነው፤ ገቢያቸው ከስደተኞች በሚመጣ ፉክክር ይቀንሳል፤ በስደተኞች መብዛት ምክንያት በመኖርያ ቤቶች አቅርቦት ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍተኛ ነው። እነዚህ በሙሉ የአስተዳደርን ክሽፈት የሚደብቁ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የቀስተ ደመናዋ አገር የሚለው ሐሳብ ለደቡብ አፍሪካውያን እንጂ ለውጪ አገር ዜጎች አይሠራም የሚለው አጠቃላይ አመለካከት አግላይ ብሔረተኝነት (exclusive nationalism) በመፍጠር ልዩነቱን አባብሶታል። ከዴሞክራሲ የመጀመርያዎቹ ዓመታት ውጭ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት መሪዎች በንግግራቸው፣ በተግባራቸው እና በፖሊሲያቸው የቀስተ ደመናን ሐሳብ የውጪ ዜጎችን በሚያካትት ኹኔታ ለማስፋት ፍላጎት እንደሌላቸው አሳይተዋል።
የጥላቻ ቅስቀሳ፣ አሉታዊ እና አግላይ ብሔረተኝነት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ካለው ደኅንነትን የመጠበቅ ድክመት ጋር ተያይዞ በየጊዜው ስደተኛ ጠል ጥቃቶች እንዲጀመሩ እና በቀላሉ እንዲባባሱ ምክንያት ኾኗል። ለምሳሌ፦ የ2008ቱ ኹከት ሲቀጣጠል እና ሲስፋፋ የምቤኪ መንግሥት ለቀናት ከሩቅ ተመልካችነት ያለፈ ሚና አልነበረውም። በመጨረሻ ከብዙ ማመንታት በኋላ ኹከት ወዳለባቸው ሥፍራዎች ወታደሮችን በመላክ ጥቃቱን አስቁሞታል። የዙማ መንግሥትስ ይኼን ለማድረግ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅበት ይኾን?

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.