‹‹በማላውቀው ምክንያት ፓስፖርቴን ተነጥቄ ጉዞዬ ተስተጓጉሏል›› ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር


በአሜሪካ ከሚገኙ የሰማያዊና የአንድነት ለፍሕትና ለዴሞክራሲ (አንድነት) ፓርቲ አባላት ጋር በተለያዩ ስቴቶች ለመወያየት ወደዚያ ለማቅናት ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ያመሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ባላወቁት ምክንያት ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ጉዟአቸው እንደስተጓጎለ ገለጹ፡፡ 
መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ወደ አሜሪካ ለመብረር ሁሉን ነገር አሟልተው ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸውን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ የአውሮፕላን መሳፈሪያ ሰዓት እስከሚደርስ ሊሸኟቸው አብረዋቸው ከነበሩ ጓደኞቻችው ጋር ሲጨዋወቱ አምሽተው ወደ ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
 የመጨረሻውን ፍተሻ አልፈው ወደ አውሮፕላን መግቢያ በር ለማምራት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ፍተሻ ጋ ሲደርሱ ፓስፖርታቸውን ሰጥተው የይለፍ ማረጋገጫ ለማግኘት እየተጠባበቁ ሳሉ የኦፕሬሺን ሠራተኛዋ ‹‹ከዚህ ቀደም ሌላ ፓስፖርት ነበረዎት?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበችላቸው ገልጸዋል፡፡ እንደነበራቸውና ከዚህ በፊትም ወደ አሜሪካ ለመሄድ እዚያው ፍተሻ ላይ ሲደርሱ ‹‹ከፓስፖርትዎት መካከል አንድ ገጽ ጎድሏል፤›› ተብለው መመለሳቸውን እንደነገሯት አክለዋል፡፡ ለ20 ደቂቃ ያህል በኢንተርኔት ላይ አንዳንድ ነገሮችን ስታነብ የነበረችው ሠራተኛዋ፣ ‹‹አለቆቼን ላነጋግር›› ብላቸው ወደ ቢሮ መግባቷንና ወዲያው በፍጥነት ተመልሳ ሥራዋን በመቀጠል ‹‹ይጠብቁ እያዩት ነው›› እንዳለቻቸውና ለ50 ደቂቃዎች ያህል መጠበቃቸውን ኢንጂነር ይልቃል ገልጸዋል፡፡
ከረዥም የደቂቃዎች ቆይታ በኋላ አንድ ሰው ከቢሮ ወጥቶ ‹‹እርስዎ ዛሬ መሄድ አይችሉም፤›› ብሏቸው ስማቸው፣ ዜግነታቸውና የፓስፖርት ቁጥራቸው ተጽፎ፣ የታገዱበት ምክንያት ያልተገለጸበት ወረቀት እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱንም ሲጠይቁ ‹‹እኛ የኦፕሬሽን ሠራተኞች ነን፣ ምክንያቱን አናውቅም፡፡ ነገ መጋቢት 24 ቀን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ መጥተው ከአለቆቻችን ምክንያቱን ያውቃሉ፤›› ብለዋቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
 በማግሥቱ መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሄዱ ‹‹በዚህ ወረቀት መግባት አትችሉም፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ሄደው ይጠይቁ፤›› ብለው እንደመለሷቸውም አስረድተዋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል በዕለቱ ወደ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምሪያ ዋና መሥሪያ ቤት የሄዱ ቢሆንም፣ ‹‹ሰዓቱ መሽቷልና ነገ ጠዋት ይመለሱ፤›› ተብለው ሳይሳካላቸው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ 
መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠዋት ሦስት ሰዓት ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት የሄዱ ቢሆንም፣ ፓስፖርቱ እንዳልደረሳቸው ሠራተኞቹ ነግረዋቸው በስልክ እየደወሉ እንዲጠይቋቸው ስልክ ሰጥተዋቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ማታ ሲደውሉ ፓስፖርቱ እንዳልመጣ ነገር ግን እነሱ እንደሚደውሉላቸው ነግረዋቸው ስልካቸውን መውሳደቸውን አስረድተዋል፡፡ ፓስፖርታቸውን አለማግኘታቸውንና የታገደቡበትን ምክንያት ሳያውቁ ጉዟቸው ተስተጓጉሎ መቀመጣቸውን የሚናገሩት ሊቀመንበሩ፣ በፕሮግራማቸው መሠረት ሄደው ቢሆን ኖሮ መጋቢት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. (ቅዳሜ) ከዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ጋር በዋሽንግተን ከደጋፊዎቻቸው ጋር ይገናኙ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የዋሽንግተን ነዋሪዎችን ጨምሮ በሰባት ስቴቶች ከሚኖሩ የሰማያዊና የአንድነት ፓርቲዎች ደጋፊዎች ጋር የተለያዩ ስብሰባዎችን ያደርጉ እንደነበር የገለጹት ኢንጂነር ይልቃል፣ ጊዜ ካላቸው ካናዳ ቶሮንቶ ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸውም ጋር ለመገናኛት ዕቅድ እንደነበራቸው አስታውቀዋል፡፡ 
በአጠቃላይ የሚቆዩት ለአንድ ወር እንደነበር የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ወደ አገር ቤት ሲመለሱ በእንግሊዝ ፕሮግራም ይዘው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ስብሰባው በሁለቱ ፓርቲዎች ደጋፊዎች የተዘጋጀ ስለነበር ለየት ያለና በጉጉት ይጠበቅ የነበረ ዝግጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብዙ ሰዎችን ልብና አዕምሮ መያዝ በመቻሉ፣ ብዙዎች እየተቀላቀሉትና በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች መታየት የጀመረ ፓርቲ በመሆኑና በገዥው መንግሥት ስላልተወደደ እንቅፋቶቹ እየበዙ ናቸው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 
ወቅቱ የምርጫ በመሆኑ በአገር ውስጥ ዝግጅቶችን በማድረግ ሁኔታ ወደ ውጭ መሄድን ለምን እንደመረጡ ተጠይቀው፣ ‹‹የእኔ እንቅስቃሴ ድርጅቱን የሚያሳድግና የድርጅቱን አቅም የሚያጠናክር ነው፡፡ ይኼም ትግል ነው፡፡ የምሄደው ለሥራ ነው፡፡ እዚያም ያሉትን ደጋፊዎቻችንን እናነቃቃለን፡፡ አዳዲስ አባላትንም እናገኛለን፡፡ የምሄደው ሰማያዊ ፓርቲን ይዤ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆኜ ነው፤›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ 
የኢንጂነር ይልቃልን ጉዳይ በመለከተ ከመንግሥትም ሆነ ከሚመለከተው አካል እስከ ዓርብ ሌሊት ድረስ ምንም የተሰጠ መግለጫ አልነበረም፡፡ 
Source:: Ethiopian Reporter