Monday, May 11, 2015

Ethiopia-Crisis-and-Conflict-US-Aid


እንደ ኢትዮጵያ ከልመናና ከምጽዋት ጋር ስሙ የሚነሳ ብዙ አገር የለም። ላለፉት ሰላሳና አርባ አመታት የቆየ ሀቅ ነው። በችጋር ጊዜ መለመን ግድ ሊሆን ይችላል። ሁሌ መለመን ግን ህመም ነው። እኛ ግን ከልመና ጋር ከመለማመዳችን የተነሳ ይመስላል ፈጽሞ ሲረብሸን አይታይም። እንዲያውም የተመቸን ነው የሚመስለው። ፖለቲካችን ሁሉ ልመና ተኮር ነው። የአገሪቱ ዲፕሎማቶች ዋነኛ ስራቸው ተግቶ መለመን ሲሆን ሲሳካላቸው ‘በተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይህን ያህል ርዳታ ተገኘ’ ብለው በሚቆጣጠሩት ቲቪ ያውጃሉ። እንደ ድል ብስራት እኮ ነው የሚያዩት። አንዳንድ ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ ርዳታ እንዳይገኝ ማሰናከል (ማቃጠር በሉት) ላይ ተጠምደዋል። ሃያላን መንግስታትና እነሱው የሚቆጣጠሯቸው እንደ አለም ባንክ ያሉ ድርጅቶች ርዳታ እንዳይሰጡ መወትወት። እንዴት ያሳፍራል። ሁለቱም አቅመቢስነትን ከመቀበል ይመነጫሉ፤ እኛ ምንም ለማድረግ አቅም የለንምና ይሄን ስጡኝ ወይ ደግሞ ያን አትስጡብን እኮ ነው ነገሩ። ስለራስ አቅም ሳይሆን በሌላ ሰው ወይም አካል ቁጥጥር ስር ያለን ሀብት/አቅም አንጋጦ የማየት በሽታ ነው። ልመናውም ምጽዋት ማከላነሉም (ምቀኝነቱ) የጥገኝነት አባዜን ከማንጸባረቅ ባለፈ ግን አንድም ነገር አይለውጥም። የሞራል ጥያቄውን ብንተወው እንኳን በአለም ታሪክ በልመና ታሪክ የሰራ አገር የለም፤ ቢኖር ኖሮ ማን ይቀድመን ነበር? በአንጻሩ ምጽዋት ጠባቂነት አንድን ህዝብ ከልመና ለመውጣት ከሚያዳግትበት አዙሪት ውስጥ ሊቀረቅረው ይችላል። እዚያ አዙሪት ውስጥ አይደለንም ብሎ መናገር የሚቻል አይመስለኝም። ይህን አዙሪት ለመረዳት ሀብታሞች ለምን እንደሚረጥቡን መጠየቅ ያስፈልጋል።

ሀ. ምዕራባዊያን የሚረጥቡን ለምን ብለው ነው?
በርግጠኝነት ምዕራባዊያን የሚረጥቡን ስንራብ እያዩ አንጀታቸው አልችል ስላለ አይደለም። ስለሚያዋጣቸው እንጂ። ካላዋጣቸው አፍሪካዊ ሞተ ብለው እንቅልፍ አያጡም። ለምንስ ያጣሉ? ሩቅ ሳንሄድ ከሩዋንዳ ጀኖሳይድ እስከ ኤች አቪ ኤይድስና በቅርቡ ስለተከሰተው ኢቦላ ድረስ ብናይ የአፍሪካዊያን ስቃይና ሞት ሀብታም አገራትን በፍጹም የማያሳስባቸው መሆኑን ነው። በተለይ ከኤች አቪ ኤይድስ ጋር በተገናኘ ከአስራምስት አመት በፊት የሆነውን ማስታወስ ያስፈልጋል። በወቅቱ በምዕራባዊያን መድሀኒት አምራቾች የሚመረትና የሚሸጠው ጸረ-ኤች አቪ ቫይረስ መድሀኒት በሰው እስከ ፲፭ ሺ ዩኤስ ዶላር ያወጣ ነበር፤ በአመት። ይህ ደግሞ ከአብዛኛው አፍሪካዊ አቅም በላይ ነው። ስለሆነም በወረርሽኙ ክፉኛ የተመታችውና አቅሙ ያላት ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙን ለመቋቋም መድሀኒቱን በአገሯ ማምረት ትጀምራለች፤ በማንዴላ በተፈረመ ህግ። ደቡብ አፍሪካ የምታመርተው መድሀኒት በጣም ርካሽ ስለነበርና ጥራቱ ደግሞ ምዕራባዊያን ከሚያመርቱት ጋር ተመሳሳይ (ጀነሪክ ድረግ)ስለሆነ የሚሊዮኖችን ህይወት ይታደጋል። ያ ግን በሀብታሞቹ ዘንድ ከቁብ የሚጣፍ ቁም ነገር አልሆነም። ዋናው ጉዳይ አሁን እጅግ ውዱ የምዕራባዊያን መድሀኒት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ገዢ የማያገኝ መሆኑ ነው። በመሆኑ ምዕራባዊያን መድሀኒት አምራች ኩባንያወች ደቡብ አፍሪካን ወጥረው ያዟት። ከሚሊዮኖች ህይወት የጥቂት ኩባንያወች ትርፍ ይበልጣልና አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ደቡብ አፍሪካን መፈናፈኛ አሳጧት። በተለይ አሜሪካ ደቡብ አፍሪካ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ዝታ ነበር፤ የሀገሬን ኩባንያወች አዕምሯዊ ንብረት መብት የጋፍተሻል በሚል (ኩባንያ አዕምሮ ያለው ይመስል)። በወቅቱ የተፈጠረው ከፍተኛ አለማቀፋዊ ውግዘት እንድታፈገፍግ አስገደዳት እንጅ። ታዲያ የነብስ አድን መዳኒት ማምረት የማይፈቀድላት አፍሪካ የስንዴ ምፅዋት በገፍ የሚቀርብላት ለምንድን ነው?
፩. የውስጥ ፖሊቲካ፤ ሀብታሞችን ስለመደጎም
ሀብታም አገራት ለገበሬወቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ ሁለት ስለት አለው። አንደኛው በውስጥ ፖለቲካ ተጽኖ ያላቸው ሀብታም ገበሬወችና ምግብ አከፋፋዮችን መደጎም ነው። በምዕራባዊያን ሀገሮች ለብዙ አስርት ዐመታት ከፍተኛ የሰብል ምርት መትረፍረፍ አለ። ስላቅ ቢመስልም ምርት ሲትረፈረፍ ገበሬዎቻቸውና ሱፐርማርኬቶች ይጎዳሉ፤ ዋጋ ስለሚወርድ። አጠቀላይ ኢኮኖሚውም ይጎዳል። በመሆኑም በ፲፱፩፸ቹ ችጋር አገራችን ሲመታት የምዕራባዊያን መንግስታት ገበሬወቻቸውን ለመርዳት ትርፉን ሰብል ባህር ብንጨምረው ይሻላል ወይንስ በርካሽ ዋጋና በርዳታ መልክ ደሀ አገራት ዘንድ ብንደፋው ይሻለል (ወጪ ከመቆጠብ አንጻር) እያሉ ይጨነቁ ነበር፤ እንዲያም አይነት ጭንቀት አለ። ቁም ነገሩ በተሻለ ኪሳራ ገበሬወቻቸውን መደገፍ ነው። ስለሆነም ለምሳሌ ኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግስት ለተመጽዋች አገራት ከያዘው የርዳታ በጀት ላይ ድርሻየዋን በጥሬው (ብሩን) እንዲሰጣት ብትጠይቅ የሚያቀምሳት የለም። ለምን? የአሜሪካ መንግስት የሚለግሰው የምግብ ‘ርዳታ’ የሚሸመተው ከአሜሪካ ገበሬወች ነው የሚል ህግ ስላለ። ሌላው ቀርቶ እዚያው ሄዳችሁ ስንዴውን ስጡን ብትሉ የሚያቀምሳችሁ የለም። ርዳታው በአገሬው መጓጓዣ ድርጅቶች እንዲጓጓዝ ህግ ስልሚያዝ። ስለዚህ ሀብታም አገር ለደሀ ስንዴ ሲረጥብ ቁምነገሩ የድሀ ነብስ መሰንበቱ አይደለም። ያ የአጋጣሚያዊ ውጤት ነው (ግን ክፉወች ሊባሉ አይገባም፤ ማንንም የመርዳት ግዴታ የለባቸውምና)። ዋናው የአገሩ ገበሬወችና የትራንስፖርት ድርጅቶች የመንግስት ድጋፍ ማግኘታቸው ነው። በሌላ አነጋገር ርዳታው በዋነኝነት ካገሬው ደሀ ግብር ከፋይ ወደ አገሬው ሀብታም ገበሬወች ነው የሚሄደው (ልክ አሜሪካ ‘ለወዳጆቿ’ የምታደርገው በቢሊዮን የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ ከግብር ከፋዮች በፔንታጎን ዞሮ ወደ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያወቿ የሚሄድ ድጎማ እንደሆነው ሁሉ)።
፪. አለማቀፍ የንግድ የበላይነትን ማስቀጠል
ሁለተኛውና ዋነኛው በአለም አቀፍ ገብያ የምርታቸውን ተወዳዳሪነት (የበላይነት) ማስቀጠል ነው። ይህ በራሱ ሁለት ፈርጅ አለው። የመጀመሪያው ምርቶቻቸውን በርካሽ ሽያጭና በርዳታ መልክ ደሀ አገሮች ዘንድ በማራገፍ (ዳምፕ በማድረግ) ድሀ አገሮች ተወዳዳሪ ሳይሆን የነሱ ጥገኛ ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ ነው። ነገር ግን የደሀ ገራት ጉዳይ ያን ያህል የሚያሳስባቸው አይደለም። ሁለተኛውና ዋነኛው በሀብታም አገራት መካከል ካለው የርስበርስ ሽኩቻ ይመነጫል። ይኸውም ካለም አቀፍ የንግድ ህግ አንጻር አገራት ለገበሬወቻቸው የሚሰጡትን ከፍተኛ ድጋፍ ለመቀነስ ስምምነት አለ። ስለዚህ ለገበሬወቻቸው ቀጥታ ብር ከመስጠት ይልቅ ለደህ አገራት የምንሰጠው ርዳታ ነው በሚል ትርፉን እህል ከመንግስት ካዝና በሚወጣ ገንዘብ በመግዛት (በዚያውም የምግብ ዋጋ እንዳይወርድ) ገበሬወቻቸውንና ሱፐርማርኬቶቻቸውን በተዘዋዋሪ መደገፍ ነው። ይህ አልሸሹም ዘወር አሉ በተለይ አሜሪካንና የአውሮፓ ህብረትን ከሚያጨቃጭቋቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። ግብር ከፋዩን ህዝብ ገንዘቡ ለድሆች የሚሰጥ ምጽዋት ነው በሚል ለናጠጡ ሀብታሞች የሚሰጥ ድጎማ መሆኑን እንዳያውቅ መሸወድ ይቻላል። አውሮፓና አሜሪካ ግን ርስበርሳቸው ሊሸዋወዱ አይችሉም።
በደሀ አገራት ላይ ያለውን የኢኮኖሚ ትጽዕኖ ስናይ እንደሚታወቀው አብዛኞቹ ደሀ አገራት ለአለም ገበያ የሚያቀርቡት ባመዛኙ የእርሻ ውጤቶችን ነው። ከዚህ ውስጥ ፹ በመቶው የምግብ ውጤት ነው። ምግብ ደግሞ የሰባት ቢሊዮን ህዝብ የየቀን ፍላጎት ነው። የምግብ ንግድን ከተቆጣጠርህ ሌላውን ሁሉ መቆጣጠር አይከብድም። ከንጹህ ኢኮኖሚክስ አንጻር እንኳን ቢታይ በአለም ገብያ የእርሻ ውጤቶች ድርሻ ተወዳዳሪ የለውም። ቡና ብቻ ከነዳጅ ቀጥሎ ሁለተኛው የንግድ ምርት ነው (በአለም ላይ በቀን ከ ፪ ቢሊዮን ስኒ በላይ ቡና ይጠጣል)። በመሆኑም በአለማቀፍ ንግድ የእርሻ ውጤቶችን ያህል አገራትን የሚያጨቃጭቅ ጉዳይ የለም። በሀብታም አገራት መካከል ከፍተኛ ፉክክርና ፍትጊያ አለ። ከርስበርስ ፉክክሩ በተጨማሪ ደሀ አገሮች በተለይ እንደ ቡና፣ ካካዋ፣ ሙዝ በመሳለሉት ከፍተኛ ትርፍ ባላቸው ሰብሎች ጥሬ ምርቱን ከማቅረብ ባለፈ የጥቅሙ ተካፋይ እንዳይሆኑ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ መንገዱን መዝጋት ሌላው ስልት ነው። ለምሳሌ እኤአ በ፪ ሺ ፯ ዓም አንድ ፓውንድ በጸሀይ የደረቅ የሲዳሞ ቅሽር ቡና በስታርባክስ ከረጢት ፳፮ የአሜሪካ ዶላር ተሸጧል። ከዚያ ውስጥ ግን ቡናውን አምርቶ አጥቦ ያደረቀው ደሀ የሲዳሞ ገበሬ ፩ ዶላር ብቻ ነበር ያገኘው። ከዚያ ውጭ ሁሉም የነ ስታርባክስ ትርፍ ነው። ደሀ ይለፋል፤ ሀብታም ይከብራል (‘ቢዝነስ አዝ ዩዡወል’ ነው የሚሉት?)። በሚቆጣጠሩት ገብያ ማን ይጠይቃቸዋል? አራት ኩባንያወች ብቻ በአለም ላይ ከሚካሄደው የቡና ንግድ ፵ በ መቶ ድርሻ አላቸው። ስድስት ቾኮሌት አምራቾች የአልምን የካካዋና ቾኮሌት ንግድ ግማሽ ይቆጣጠራሉ።
ከተክኖሎጂ ክፍተቱ በተጨማሪ የድሀ አገራት የእርሻ ምርቶች በሁሉም ያደጉ አገራት ማለት ይቻላል የሚገጥማቸው የታሪፍና ታሪፍ ያልሆኑ መሰናክሎች በጣም ከፍተኛ ነው። በተለይ ታሪፍ ያልሆኑት መሰናክሎች ሀብታም እገራት እንደፈለጉ የሚጠቀሙባቸው መሳሪያወች ናቸው። ለየትኛውም አይነት ምርት የጥራት ደረጃ የሚሰጡት የነሱው ድርጅቶች። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቡና የሚታወቀው በጥራቱ ነው። የአባይን ግድብ የለሰራችልን ወዳጃችን ጃፓን ግን የኢትዮጵያ ቡና የጥራት ችግር አለበት በሚል ለብዙ አመታት ወደ አገሯ እንዳይገባ እገዳ ጥላ ነበር። አቅም ከሰው ቤት ሆነ እንጂ ቶዮታ መኪና ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መከልከል ነበር! ሀብታም አገራት ከሚጥሉት እንዲህ አይነት ግፈኛ መሰናክል በተጨማሪ የትሮፒካል የእርሻ ውጤቶች ላይ ከቴምፕሬት ምርቶች በተለዬ ከፍተኛ ታሪፍ ይጥላሉ። በተለይ የድሀ አገራት ከፍተኛ ትርፍ ባላቸው የተቀነባበሩ(ፕሮሰስድ) የእርሻ ውጤቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ይጥላሉ። ለምሳሌ ካናዳ በተቀነባበሩ የደሀ አገራት ምርቶች የምትጥለው ታሪፍ በጥሬ ምርቶች ከምትጥለው በ፲፪ እጥፍ ይበልጣል። ስለዚህ ደሀ አገራት ተስፋ ቆርጠው ሁሌ ጥሬ እቃ ነጻ በሚባል ዋጋ ሲያቀርቡ ይኖራሉ ማለት ነው። ስንዴ እየተደጎሙም ቢሆን ጥሬእቃ ካቀረቡ ሌላ ምን ይፈለጋል? ያ እስካልተቀየረ ድረስ ድሀ አገራት በድህነት ይቀጥላሉ። ነዳጅ ዘይትን ሳይጨምር ጥሬ እቃ በመሸጥ ከድህነት የወጣ አገር በታሪክ የለምና።
የበተጸጉት(OECD)አገራት ለገበሬወቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ በቀን ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ነው። ይህ እንዲቀጥል ደግሞ ገበሬወቻቸው ሎቢ ያደርጋሉ። በቢሊዮን የሚቆጠር የመንግስት ድጋፍ የሚያገኙ የሀብታም አገራት ገበሬወች ምርቶቻቸውን በኪሳራ መሸጥ ይችላሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሀ አገራት ያሉ ገበሬወች ደግሞ እንኳን የመንግስት ድጋፍ ሊያገኙ በግብርና የማዳበሪያ ዕዳ የርሻ በሬያቸውን ሸጠው ስራ ፍለጋ ወደ ከተማ እንዲሰደዱ ይገደዳሉ። ኪሳራው ለደህ አገራት ገበሬወች ነው የሚሆነው። ለምሳሌ እኤአ በ፪፲፻፩በጥጥ ምርት የምትታወቀው ማሊ ፴፯ ሚሊዮን ብር በርዳታ አግኝታለች፤ ነገር ግን አሜሪካ ለጥጥ አምራቾቿ በምሰትጠው ህገወጥ ድጋፍ የተነሳ ማሊ ከአጠቃላይ አመታዊ ምርቷ (ጅዲፒ) ፫ ፐርሰንቱን አጥታለች። ገበሬወቿ ርሻቸውን ጥለው ስራ ፍለጋ ወደከተማ ተሰደዱ። የብዙ ርዳታ ጠባቂ አገሮች ታሪክ ተመሳሳይ ነው።
ለ. የፖለቲካ ቃላትና ትርጉማ(ልባነታ)ቸው
በየጊዜው በሚዲያ የምትሰሙትን የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት ርሱት። የአለም ፖሊቲካኢኮኖሚ መገለጫ ትብብር ሳይሆን ውድድር ነው። መቸም ከዚህ የተለየ ሆኖ አያውቅም። የማሸነፊያ ካርዱ ደግሞ ቴክኖሎጂ ነው። ቴክኖሎጂ ደግሞ በቀላሉ እይገኝም። ሀብታም አገራት ከምንም በላይ ቴክኖሎጂያቸው ለሌሎች እንዳይተላለፍ ከፍተኛ ጥበቃ ያደርጋሉ። ይህ የግብርና ቴትክኖሎጂን ይጨምራል። የወሬና የመረጃ ልዩነት ግር የሚላቸው የኢቲቪ ጋዘጠኞች ገበሬወች ማዳበሪያ ተጠቅመው ለማለት ‘የግብርና ቴትክኖሎጂ ተጠቅመው’ ሲሉ ትሰሙ ይሆናል፤ ማዳበሪያ ግን የትም የምትገዛው ሸቀጥ እንጂ ቴትክኖሎጂ አይደለም። የአፍሪካ ህዝብ በርሀብ የሚያልቅ ቢሆን እንኳ ሀብታም አገራት የግብርና ቴትክኖሎጂን አያቀምሷትም። ያ የማይታሰብ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት ወዘተ የሚባለው ከሪቶሪክ ያለፈ ትርጉም የለውም። በተግባር ወሳኝ ያልሆነና ጊዜው ያለፈበት ካልሆነ በስተቀር ተክኖሎጂ በሽያጭ እንኳን አይግኝም። ወቅታዊ ቴክኖሎጅ የሚገኘው አንድም በፈጠራ አለያም በኩረጃ (አይን ባወጣ ስርቆት ጭምር)ነው። በርግጥ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በኩረጃ መካክል ያለው ልዩነት ሁሌ ግልጽ ላይሆን ይችላል። ሳይኮርጁ መፍጠር አይቻልምና። በቴክኖሎጂ ስርቆት የማይታማ አንድም አገር የለም። እንዲያውም እኮ የቴክኖሎጅ ስርቆት የየትኛውም አገር የስለላ ድርጅት ዋነኛ ስራ ነው። ታሪክንም ብናይ ከሌላው ያልጎረጀ አገር አይገኝም። ለምሳሌ አሜሪካ በ፲፱ኛ ክ/ዘመን ጨክና ከአውሮፓውያን በመስረቅ ትወቀስ ነበር። የአምሯዊ ንብረት ጥበቃ ተቃዋሚ ነበረች። ዛሬ የተራቀቀ ቴክኖሎጅ ባለቤት ስትሆን ደግሞ በተራዋ ዋነኛዋ የአምሯዊ ንብረት ጥበቃ አቀንቃኝ ሆና እነቻይናን በሌብነት ትከሳለች።
ሐ. ለመሆኑ ቴክኖሎጂ የማን ነው?
የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት ትርጉም የሌለው ባዶ የፖለቲካ ቋንቋ ነው ብያለሁ። በመጀመሪያ አብዛኛው ቴክኖሎጂ ያለው በአገራት እጂ ሳይሆን በሀብታም ኩባንያወች ስር ነው። ስለዚህ ለምሳሌ የአሜሪካ መንግስት ቢፈልግ እንኳ የሞንሳንቶን ያመራረት ሚስጥር አሳልፎ ሊሰጥህ አይችልም። ሁለተኛ ወቅታዊ ቴክኖሎጂን ለሌላ አሳልፎ መስጠት ጦር ለጠላት እንደማቀበል ያለ ጅልነት ነው። ስለዚህ አታስቡት። ከዚያ ይልቅ ሞንሳንቶና የሚደጉማቸው ‘ምሁራንና ሚዲያወች’ አፍሪካን ከርሀብ ለመታደግ ሌላ መፍትሄ አላቸው፤ በዘረመል ቴክኖሎጂ የተባዛ ምግብ። ለምን መሰላችሁ? ሞንሳንቶ ኩባንያ የአለምን የዘረመል ዘር (ጀነቲካሊ ኢንጂኔርድ ሲድ)ÒÇ በመቶ (ሙሉ በሙሉ በሉት) ስለሚቆጣጠር። የዘረመል ምግብ በጤና ላይ ሊያስከትል በሚችለው አደጋ ምክንያት ወደ አውሮፓ ወይ ጃፓን እንደፈለጉ መላክና ማትረፍ አልተቻለም። ስለዚህ ‘በአፍሪካ ብንሞክረውስ?’ ነው ነገሩ። በርግጥ በጀነቲክ ምህንድስና የተቀየጡ ምግቦች በጤና ላይ ስለሚያደርሱት ጉዳት ብዙ ውዝግብ አለ። ግን የጤና ጉዳይ ነውና በጥንቃቄ መታየት አለበት። ለምሳሌ አውሮፓውያን በምንም አይነት በጤናቸው መደራደር አልፈለጉምና በአርቲፊሻል ሆርሞን የተመረተ የአሜሪካ ስጋ አገራቸው እንዳይገባ በማገዳቸው ብዙ ውዝግብ ተፈጥሯል። የሚያስደንቀው፤ የአሜሪካ ሸማቾች ማህበር (ኮንሱይመር ፌዴሬሽን ኦፍ አሜሪካ) ራሱ በአውሮፓ ውሳኔ በመበሳጨት ፋንታ አውሮፓ የጣለው እግድ አሜሪካ ውስጥም እንዲጣል ጠይቆ ነበር፤ የአቅም ጉዳይ ሆነና
አልተሳካለትም እንጂ።

መ. ዋኝቶ ይውጣው እንጂ ሌላ ማን ሊረዳው
ለማኝነት ሞት ነው። ውርደት ነው። ይህን ውስጣችን ስለሚረዳ እኮ ነው የኔቢጤ ምናምን እያልንን ለመሸንገል የምንሞክረው። ግን ለማኝን የኔቢጤ በማለት ዝቅ ብሎ ሲለምን ያጣውን ክብር መመለስ አይቻልም። ወይ ደግሞ በልመና ሞያ የተሰማሩ ወገኖቻችን እያሉ በማንቆለጳጰስ ልመናን እንደምንም ስራ ማስመሰል አይቻለም። ቀበሮ እንኳን የትም አድና ራሷንና ልጆቿን ትመግባለች። ተፈጥሮን ህግ ትረዳለች፤ አትለምንም። መለመን ከቀበሮ ማነስ ነው። የሞራል ጥያቄውን ብንተወው እንኳ ለማኝ በተግባር የትም አይደርስም። ሀብታሞች አሳ ሊሰጡህ ይችላሉ፤ ያም ደስ ካላቸው ነው። አሳ ማጥመዱን ግን የግድ በራስህ መማር ይኖርብሀል። ሌላ ምንም መንገድ የለም፤ ኖሮም አያውቅም። ስለዚህ ኮፈዳን ጥሎ ዶማ ማንሳት ብቻ ነው መንገዱ። በተግባር ዳቦም ይሁን ነጻነት ማረጋገጥ የራስህ ግዴታ ነው። ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው።
ሰላም ሁኑ

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.