“ሕዝብን መታዘዝ ይገባል!”
በቅርቡ በሥልጣን ላይ እያሉ በምርጫ መሸነፋቸውን ባመኑበት ጊዜ ሥልጣናቸውን ያስረከቡት የናይጄሪያው ጉድላክ ዮናታን በአፍሪካ የ65 ዓመታት የምርጫ ዴሞክራሲ ጉዞ ከሚጠቀሱ ጥቂቶች መካከል አንዱ ሆነው ሰንብተዋል፡፡ ይህም ተግባራቸው በናይጄሪያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ታላቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው የፖለቲካ ሰው አድርጓቸዋል፡፡
በአፍሪካ በተካሄዱ በርካታ ምርጫዎች የሕዝብን ድምጽ በማክበር ሥልጣናቸውን ለተቀናቃኛቸው በማስረከብ የሕዝባቸውን ድምጽ ያከበሩ መሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሁሉንም ለአሁኑ ማቅረብ ባንችልም የተወሰኑት ተጠቃሾች እነዚህ ናቸው፡-
1. ኤደን አብዱላ ኦስማን ዳር (ሶማሊያ) – በተለምዶ ኤደን ዳር ተብለው የሚጠሩት እኚህ ፖለቲካኛ የሶማሊያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ በሥልጣን በነበሩበት ጊዜ ሶማሊያን እኤአ ከ1960 እስከ 1967 መርተዋል፡፡ (በዚህ ጽሁፍ ላይ የሰፈሩት ዓመታት በሙሉ እኤአ ነው)
የሶማሊያ ወጣት ሊግ አባል በመሆን የፖለቲካ ጉዟቸውን የጀመሩት ዳር አገራቸው በ1960 ነጻነቷ ስትጎናጸፍ ስመጥር እየሆኑ በመምጣታቸው የሶማሊያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠው ለ7 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ሆኖም በ1967 በተደረገ ምርጫ በቀድሞው ጠ/ሚ/ር አብድራሺድ አሊ ሸርማርክ ተሸንፈው ሥልጣናቸውን በጸጋ አስረክበዋል፡፡ በዚህም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለተመረጠ መሪ ሥልጣን በማስረከብ ከአፍሪካ የመጀመሪያ ተብለው ከሚጠቀሱት አንጋፋው በመሆን ታሪክ ሠርተዋል፡፡
2. ኬነት ዴቪድ ካውንዳ (ዛምቢያ) – ከነጻነት በኋላ ኬነት ካውንዳ የአገራቸው የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት በመሆን ከ1964 እስከ 1991 መርተዋል፡፡ አገራቸው ከእንግሊዝ ቅኝ ነጻ ለመውጣት ባደረገችው ትግል ቀዳሚውን ሥፍራ በመያዝ የታገሉት ካውንዳ በሥልጣን ዘመናቸው የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በሙሉ አግደው የራሳቸው ፓርቲ ብቻ እንዲንቀሳቀስ ማድረጋቸው በታሪካቸው የሚነሳ አንዱ አሉታዊ ጉዳይ ነው፡፡
ሆኖም እኤአ በ1970ዎቹ በተከሰተው የነዳጅ ዘይት ቀውስ ጋር በተያያዘ የዛምቢያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመግባቱ በካውንዳ አገዛዝ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መስሎ ቢታይም በተቃራኒው ፕሬዚዳንቱ በሥልጣን እንዲቆዩ ምክንያት ነው የሆናቸው፡፡ በሌላ ጎኑ ይኸው ቀውስ ውሎ አድሮ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በአገሪቷ እንዲጀመርና ዛምቢያ ወደ ነጻ ምርጫ እንድትደርስ አድርጓታል፡፡
በ1991 በተካሄደ ምርጫ የካውንዳ ተቀናቃኝ ሆነው የተወዳደሩት ፍሬዴሪክ ቺሉባ አሸናፊ ሆኑ፡፡ በዚህ ወቅት ካውንዳ የወሰዱት እርምጃ ዓለምን አስደመመ፤ አስደነቀ! ኬነት ካውንዳ ገና ከጅምሩ ምርጫውን ማጭበርበር ይችሉ ነበር፤ አላደረጉም፡፡ በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበሩ በመሆናቸው የምርጫውን ውጤት ወደፈለጉት አቅጣጫ እንዲሄድ ማድረግ ይችሉ ነበር፤ ይህንንም አላደረጉም፡፡ ከዚህ ይልቅ በምርጫ መሸነፋቸውን አምነው ተቀበሉ፤ ሥልጣናቸውን ሕዝብ ለመረጣቸው ቺሉባ አስረከቡ፤ ሕዝባቸውን አከበሩ፤ አገራቸውን ታደጉ!
3. ሩፒያ ብዌዛኒ ባንዳ (ዛምቢያ) – ኬነት ካውንዳ በጀመሩት የምርጫ ዴሞክራሲ ፈር ተከትለው ሥልጣን የያዙት መሪዎች በሥልጣን ላይ እያሉ በምርጫ ሲሸነፉ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ ብዙም ሲቸገሩ አልታዩም፡፡ ምክንያቱም የካውንዳ ራዕይና ውርስ (ሌጋሲ) ለትውልድ የሚተላለፍ በመሆኑ ነው፡፡
በመሆኑም ዛምቢያን ከ2008 እስከ 2011 በፕሬዚዳንትነት የመሯት ባንዳ በ2011 በሥልጣን ላይ እያሉ በተደረገ ምርጫ ሲሸነፉ ለሕዝብ ድምጽ አክብሮት በመስጠት ሽንፈታቸውን በጸጋ በመቀበል መደበኛ ኑሯቸውን ጀምረዋል፡፡ በካውንዳ ዘመን የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ሲያከናውኑ የኖሩት ባንዳ እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ደርሰው ነበር፡፡ በወቅቱ ዛምቢያን ይመሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ሌቪ ምዋናዋሳ በድንገት በደረሰባቸው የጤና መታወክ ባንዳ ቦታቸውን ተክተው ሠርተዋል፡፡ ወዲያውኑ በተደረገ ምርጫ ባንዳ በጠባብ ውጤት በማሸነፍ የመሪነቱን ሥልጣን በይፋ ተቆጣጠሩት፡፡
ሩፒያ ባንዳ በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣናቸውን ለተቀናቃኛቸው እንደሚለቁ ባስታወቁበት ሽንፈትን የመቀበያ ንግግር የዛምቢያ ሕዝብ በዴሞክራሲዊ መንገድ ሃሳቡን መግለጹን ጠቁመውሕዝብን መታዘዝ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ጊዜው አሁን አርቆ የማሰብ፣ የመረጋጋትና የርኅራኄ ነው፤ ለአሸናፊዎች ይህንን ልበል፡ ያገኛችሁትን ድል በደስታ የማክበር መብት አላችሁ ግን በቸርነትና በበጎነት አድርጉት፤ እያንዳንዱን ሰዓት ተደሰቱበት፤ ነገር ግን የመንግሥት ሥልጣን ዓመትን ጠብቆ የሚያበቃ መሆኑን አስታውሱ”፡፡
4. አብዱ ዲዩፍ (ሴኔጋል) – ወደ ሥልጣን ሲመጡም ሆነ ሲለቁ በሰላማዊ መንገድ ያጠናቀቁ ሁለተኛው የሴኔጋል ፕሬዚዳንት አብዱ ዲዩፍ ናቸው፡፡ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በተለያዩ የመንግሥት መ/ቤቶች በኃላፊነት በማገልገል በአጭር ጊዜ ውስጥ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ታዋቂው ሊዎፖልድ ሴዳር ሴንግሆር ካቢኔ ዳይሬክተር ሆኑ፡፡ ቀጥሎም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ በማደግ ሴንግሆር ሥልጣን ሲለቁ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡
በሴኔጋል በተደጋጋሚ በተካሄዱ ምርጫዎች ያሸነፉት ዲዩፍ የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዳከም ሲሉ ፓርቲዎች በቁጥር በዝተው በኅብረት ተዳክመው ምርጫ እንዲወዳደሩ ማስደረጋቸው፤ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጥምረት እንዳይፈጥሩ በሕገመንግሥት ማስከልከላቸው (በኋላ ቢፈቀድም) የሚወቀሱበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም የረጅም ጊዜ ተቀናቃኛቸው አብዱላያ ዋድ በ2000ዓም በተደረገ ምርጫ በሁለተኛ ዙር በተደረገ ቆጠራ ሲያሸንፏቸው ሥልጣናቸውን አስረክበዋል፡፡ ባላንጣቸው ዘንድ ስልክ በመደወል እንኳን ደስ አለዎት ባሉበት ወቅት ፕሬዚዳንትነት “ታላቅ ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑን በመጥቀስ መልካሙን ሁሉ እመኝልዎታሁ” ብለዋቸዋል፡፡ የ74 ዓመቱ ዋድ የተወዳደሩበት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት “ቅንጅት 2000 ለለውጥ” የሚባል ነበር፡፡
5. አብዱላያ ዋድ (ሴኔጋል) - አብዱ ዲዩፍን አሸንፈው የሴኔጋል ሦስተኛ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዋድ ከ12 ዓመት የፕሬዚዳንትነት ቆይታ በኋላ በ2012 በተደረገ ምርጫ በተቀናቃኛቸው ተሸንፈው መንበሩን አስረክበዋል፡፡ በሥልጣን ዘመናቸው በርካታ አወዛጋቢ ክስተቶች የነበሩና እርሳቸውም በዚህ የሚወነጀሉ ቢሆንም የአብዱ ዲዩፍን ሌጋሲ (ውርስ) ተግባራዊ በማድረግ እውነተኛ “መተካካት” በአገራቸው ፈጽመዋል፡፡
6. ጉድላክ ዮናታን (ናይጄሪያ) - በሰሞኑ ምርጫ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሥልጣናቸውን በምርጫ ላሸነፏቸው ሙሃማዱ ቡሃሪ አስረክበው ተሰናብተዋል፡፡ ዮናታን በሥልጣን ቆይታቸው የሚወቀሱበት በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ይህየሕዝብን ድምጽ የማክበራቸው ጉዳይ ግን የቡሃሪ ደጋፊዎችን ያስደሰተ፤ ምዕራባውያንን አፍ ያስዘጋ፣ አምባገነኖችን ያስደነገጠ፣ ምርጫ ሲመጣ “ሥራ የሚበዛባቸውን” “በእኛ አገር ይህ አይሆንም” ያስባለ ሲሆን “ዮናታን ያሸንፋል” በማለት “ታይቶኛል፣ ተገልጾልኛል፣ ተከስቶልኛል፣ …” በማለት የተናገሩ የሃይማኖት መሪዎችንና ጠንቋዮችን ያሳፈረ ነው፡፡
ኢህአዴግ አካሂደዋለሁ ብሎ ካወጀው ምርጫ አኳያ ለአብነት ያህል በመጥቀስ ለትምህርት እንዲሆን አቀረብነው እንጂ በሥልጣን ላይ እያሉ በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣናቸውን በማስረከብ የሕዝብን ድምጽ ያከበሩ መሪዎች በደቡብ አፍሪካ፣ በቤኒን፣ በኬፕ ቬርዴ፣ ወዘተ ይገኛሉ፡፡
ድል የሚገኘው በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በመሸነፍም ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሽንፈት በቃል ሽንፈት ተብሎ ቢጠራም ዋናው ትርጉሙ የሕዝብን ድምጽ ማክበር ነው፡፡ አንድ ፓርቲ የፈለገውን ያህን አገዛዙ ዴሞክራሲያዊ፣ “መሪው ባለራዕይ”፣ አካሄዱ “ልማታዊ”፣ ርዕዮቱ “አብዮታዊ”፣ ዕቅዱ “ሕዳሴያዊ”፣ … ቢሆንም የማብቂያ ጊዜ (date of expiration) ሊኖረው ይገባል፤ አለበለዚያ መልካም አስተዳደር እንኳን ቢሆን ይሰለቻል፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ለውጥን ይሻል፤ ሕዝብ ይናገራል፤ ሕዝብ ተናግሮ ድምጹን ሲያሰማ ማድመጥ ከውድመት ያድናል፤ ሩፒያ ባንዳ እንዳሉት “ሕዝብን መታዘዝ ይገባል”!
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.