July 9, 2015
አሌክስ አብርሃም
‹‹በመንግስት›› ካባ የተጀቦኑት ግለሰቦች ፈፅሞ ‹‹ይቅር ባይ ›› አይደሉም!! …ይቅር የማይባል ስህተት የህዝብ ልጆች ላይ የሚሰሩ ጭፍን ጥላቻ እና የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸው አንባገነኖች እንጅ …አሁንም ‹‹ መንግስት ›› በጭፍን ጥላቻ ያሰራቸውን በርካታ ኢትዮጲያዊያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ … የማንንም አገር መሪ መምጣት ሳይጠብቅ ሊፈታ ይገባል ! እኛ ኢትዮጲያዊያን አባቶቻችን በከፈሉልን ንፁህ መስዋእትነት ከነድህነታችን ተከባብረንና ተፋቅረን የምንኖር የተከበርን ህዝቦች እንጅ …መንግስት ለብድርና እርዳታ ጥማቱ አበዳሪ በመጣ ቁጥር እንደዘንባባ እየዘነጠፈ ሃያላን መሪዎች እግር ስር የሚያነጥፈን ርካሽ ህዝቦች አይደለንም !!
እዝኛለሁ … ከእስሩ የበለጠ የተፈቱበት መንገድ አሳዝኖኛል …መንግስት ለዜጎች ያለውን እጅግ የወረደ ንቀትና ‹‹ማን አለብኝነት›› የሚያሳይ ድርጊት ነው … ኢትዮጲያዊያን ባልቴቶች በምርኩዝ ፍርድ ቤት ድረስ ሂደው እያለቀሱ ሲለምኑት በወታደር እያስገፈተረ ያስባረረ መንግስት …ህዝቦች በአደባባይ ወንድማ እህቶቻችንን ፍታልን እያልን ስንለምን ከነደጋፊወቹ ያሻውን ፀያፍ ስም እየለጠፈ ሲሳለቅና ሲያሽጓጥጥ የኖረ መንግስት… አሁን የባርነት ስነልቦናው በፈጠረው መሽቆጥቆጥ ‹‹ወደቤታችሁ ሂዱ›› ብሎ ከየቤታቸው አፍኖ የወሰዳቸውን ዜጎች መፍታቱ … ብሔራዊ ውርደት ነው !! እንዲህ አይነት ‹‹ስፈልግ አስራችኋለሁ ስፈልግ እፈታችኋለሁ ›› መልእክት ያዘለ ‹ነፃነት› ከጠባብ እስር ቤት ወደሰፊ እስር ቤት ሰዎችን ማዘዋወር እንጅ ፍትህ ያመጣው ነፃነት አይሆንም …አይደለምም!
ህገ መንግስቱን ባሻው ሰአት የሚጥስ ምንም ዋስትና ሊሰጥ የማይችል መንግስት እንዳለን ማሳያም ነው ! መንግስት እስካሁንም ባሰራቸው ጋዜጠኞች ጦማሪያንና ሌሎችም ንፁሃን ላይ ከመረረ የግል ጥላቻ ውጭ ምንም ምክንያት እንደሌለው የሚያሳይ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት !! ህዝብን የማያከብር በህዝብ ስም እርዳታና ብድር ለመለመን የሚሽቆጠቆጥ መንግስት ለአገርም ለዜጎችም ዋስትና አይሆንም !!
ለማንኛውም አንድ አመት ሙሉ ልጆቻችሁ በግፍ ‹‹ለታገቱባችሁ›› ወላጆች… በአሜሪካ መሪ ስም ከእገታ ነፃ ወጥተዋልና እንኳን ደስ ያላችሁ!! በእስር ላይ ያላችሁም ወገኖቻችን ከኢትዮጲያ ህዝብ በላይ የሚከበር የአገር መሪ እስከሚጎበኘን ፅናቱን ይስጣችሁ ! ኢትዮጲያዊነት ዋጋው ምንም እንዲሆን ለሚታትረው መንግስታችንም በክብር የተጠየቀውን በውርደት ስለፈፀመ ‹‹መቶ ፐርሰንት የውርደት ምልክታችን ሁኖ ይኖራል››
Alex Abreham በነገራችን – ላይ
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.