የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በላይ የሆናቸው ሁለት ሕንፃዎች ደረጃቸውን አልጠበቁም በሚል ምክንያት የመጠቀሚያ ፈቃድ ከለከላቸው፡፡ሁለቱ ሕንፃዎች መገናኛ ድልድይ አካባቢ የሚገኘው ቤተልሔም ፕላዛና ሜክሲኮ አካባቢ ከቡናና ሻይ ሕንፃ ፊት ለፊት የሚገኘው ደብረ ወርቅ ታወር ናቸው፡፡
ሁለቱ ሕንፃዎች የተጠቀሙበት የውጭ መስታወት አንፀባራቂ ነው በሚል ምክንያት አስተዳደሩ መስታወታቸው እንዲነሳ ማዘዙ ታውቋል፡፡
መገናኛ የሚገኘው ቤተልሔም ፕላዛ ባለ ሰባት ፎቅ ነው፡፡ ያረፈው በ800 ካሬ ሜትር ቦታ ነው፡፡ ለግንባታው በአጠቃላይ 40 ሚሊዮን ብር መውጣቱን፣ ለመስታወቱ ብቻ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገ ከሕንፃው አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሕንፃው ከሦስት ዓመት በፊት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ በርካታ የንግድ ተቋማት እስከ አንድ ዓመት ድረስ ለመቆየት የኪራይ ውል ፈጽመው ሥራቸውን እያከናወኑበት ነው፡፡
አስተዳደሩ ያሳለፈው ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ተከራዮቹ ለቀው እንደ አዲስ የመስታወት ነቀላና ተከላ መካሄድ ይኖርበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሕንፃው ባለቤት የጣፋጭ ቤተልሔም ባለቤት አቶ ነጋሽ ባልቻ ናቸው፡፡
የደብረ ወርቅ ታወርም ይኸው ውሳኔ ተግባራዊ እንደሚሆንበት ተነግሯል፡፡ ደብረ ወርቅ ታወር ከፍታው 13 ፎቅ ሲሆን፣ ለወርቃማው መስታወት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣ ይነገራል፡፡
ደብረ ወርቅ ታወር በ500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሕንፃ ሲሆን፣ ለሕንፃው የወጣው ወጪ ተሰልቶ እንዳለቀ ባለቤቱ አቶ ተመስገንን ከፍያለው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ሕንፃዎች ባለቤቶች የአስተዳደሩን ውሳኔ አልተቀበሉትም፡፡ ምክንያታቸውም ሕንፃዎቹ የተገነቡት በግልጽ እየታየ ነው፡፡
ከተከራዮች ጋር ውል ገብተው ከሁለት ዓመታት በላይ አገልግሎት ከሰጡ በኋላ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ መወሰኑ አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ መከራከራቸውን ቀጥለዋል፡፡ አቶ ተመስገን እንዳሉት፣ ሕንፃቸው ወርቃማ ቀለም እንዲኖረው ያደረጉት ለውበት ብለው ነው፡፡ በዚያ ላይ ደረጃውን የጠበቀና ድርብ በመሆኑ ሙቀት የለውም፣ አያንፀባርቅም ይላሉ፡፡
የሊዝ አዋጅና የሕንፃ አዋጅ በሕንፃ የመጠቀሚያ መስፈርትን በሚመለከት ድንጋጌ አውጥተዋል፡፡ ማንኛውም ሕንፃ በዲዛይኑ መሠረት ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆን በሕንፃ የመጠቀም ፈቃድ ጠይቆ ሲያገኝ አገልግሎት መስጠት ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አዋጆች ሕንፃዎች ማሟላት ስለሚኖርባቸው ቁም ነገሮች የሚናገሩ ቢሆኑም፣ ይህ አሠራር ብዙም ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል፡፡
እነዚህ ሁለት ሕንፃዎች የድንጋጌዎቹ የመጀመሪያ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሕንፃዎች በአንፀባራቂነት ቢፈረጁም በከተማው ውስጥ በርካታ ሕንፃዎች በዲዛይናቸው ለፓርኪንግ የተተወውን ቦታ ለሱፐር ማርኬትና ለመሳሰሉት ሥራዎች እያዋሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም በዲዛይኑ ላይ የሌሉ ተቀጥላዎችንም እንደሚጨምሩ ይስተዋላል፡፡
አስተዳደሩ በቀጣይነት በእነዚህ መሰል ግንባታዎች ላይ ፊቱን እንደሚያዞር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.