Saturday, March 22, 2014

የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ስብሰባ በመንግስት ካድሬዎች በሀይል ተደናቀፈ

March 22, 2014
Update:
ከ32 የሚበልጡ የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን ምክር ቤት አባላትና አመራሮች ንብረቶቻቸው ተቀምቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየተጋዙ ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከፓርቲው የተላኩ መሆኑን የሚያሳየውን ደብዳቤ ጨምሮ መታወቂያቸው ሳይቀር በካድሬዎቹ ተነጥቋል፡፡
————————-
የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ደህንነታቸው አደጋ ላይ ነው፡፡
የሟቹን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ ምስል ያለበት ቲሸርት የለበሱ ከ10 የሚልቁ የመንግስት ካድሬዎች በወላይታ ሶዶ እየተደረገ የነበረውን አንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን ምክርቤት ስብሰባን በሀይል ማደናቀፋቸውን ከስፍራው ለፍኖተ ነጻነት የደረሰው ዘገባ አመለከተ፡፡
ካድሬዎቹ የስብሰባ አዳራሹን በሃይል በመስበር ከተሰብሳቢዎቹ ላይ የተለያዩ ሰነዶችን የቀሙ ሲሆን ድብደባ በመፈፀም ላይ ናቸው፡፡ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ደህንነታቸው አደጋላይ መሆኑን ለፍኖተ ነፃነት ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፣ ፍኖተ ነጻነት
ከታሰሩት የአንድነት አመራሮች መካከል፣
Andinet party leadershipAndinet party leadership in Southern Ethiopia




lINK:-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11517/

Friday, March 21, 2014

ለነፃነት የምናደርገው ትግል በህገ ወጥ እስርና ማስፈራሪያ አይደናቀፍም! (በሰማያዊ ፓርቲ)

March 21, 2014
ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
“ማርች-8″ የሴቶችን ነጻነትና እኩልነት እንዲሁም ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበር የሴቶች ቀን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን በዓል አስመልክቶ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፈው ዕሁድ የካቲት 30/2006 ዓ.ም ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ ሩጫ ማዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ የሐገራችንም ሆነ የዓለም ሴቶች የነጻነት ቀናቸውን በሚያከብሩበት ዕለት እንደሌሎች ሴቶች ሁሉ የሰማያዊ ፓርቲ አአባላትም አላማውን ደግፈው በዕለቱ ቀኑን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሩጫ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በዚህ በሴቶች የነጻነት ቀን በስርዓቱ ላይ የሚነሱ ብሶቶችን ካሰሙት ተሳታፊዎች ውስጥ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሚገኙበት ሲሆን፣ በተለየ መልኩ በእነዚህ አባላቶቻችን ላይ ያነጣጠረ የአፈሳ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንደዚህ አይነት ህዝባዊ መድረኮችን ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ህዝብ ላይ የሚደርሰው በደል በማጋለጥ መብት እና ለአገራችን ብሄራዊ ጥቅም በመቆም በገዥው ፓርቲ ተደጋጋሚ ህገ ወጥ እርምጃ ሲወሰድበት ቆይቷል፡፡ የተደረገው ህገ ወጥ ድርጊት ከዚሁ ፓርቲው ለህዝብና ለአገር መቆሙን ተከትሎ እየደረሰበት ያለው የከፋ የጭቆና አካል ነው፡፡Semayawi party press conference, Addis Ababa
ህገ ወጥ ድርጊቱን የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገውም አባላቶቻችን የታሰሩበት ምክንያት “የጣይቱ ልጅ ነን” ፣ ህወሓት/ኢህአዴግን ምን ያህል ከታሪክ ጋር የተጣላ መሆኑን ከማሳየቱም በተጨማሪ አባላቶቻችን ለማስር እንግልት ወቅት በአባላቶቻችን ላይ የደህንነት አካላት ነን በሚሉ ግለሰቦች ማስፈራሪያና ዛቻ ተፈፅሞባቸው፡፡ አንዳንዶቹ አባላቶቻችን በሌሊት ጭምር ከእስር ክፍላቸው ወጥተው ቃል እንዲሰጡ ተከልክለዋል፡፡ ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡ ከጠያቂ ቤተሰቦቻቸውና የትግል ጓደኞቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ተከልክለዋል፡፡ የተጠረጠሩበት ክስ የማያስከስስና በነፃ የሚያስለቅቃቸው መሆኑ በየካ ክፍለ ከተማ ፍትህ ፅ/ቤት አቃቤ ህጎች ከተገለፀላቸው በኋላም በድጋሚ ፍርድ ቤት በማቅረብ እያንዳንዳቸው 1300 ብርና የመታወቂያ ዋስ በዋስትና እንዲቀርቡ ተጠይቀዋል፡፡
ፓርቲያችን ይህ እርምጃ በአባላቱ ላይ የተወሰደው ሰማያዊ ፓርቲ በመላው አገሪቱ መዋቅሩን እያደራጀና ህዝብን ከጎኑ እያሰለፈ ባለበት ወቅት መሆኑ፣ የህዝብ ድጋፍ የሌለው ገዥው ፓርቲ በሰበብ አስባቡ ሰማያዊ ፓርቲን ከወዲሁ ለማዳከም የወሰደው ነው ብሎ ያምናል፡፡ በተለይ የምርጫ ወቅት እየቀረበ መሆኑን ተከትሎ ይህን ህገ ወጥ እርምጃ መውሰዱ አሁንም ቢሆን የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ምን ያህል እየጠበበ እንደሄደ ያሳያል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ መቼም ቢሆን ይህንና መሰል የአገዛዙን አፈናዎች አጥብቆ የሚያወግዛቸውና የሚታገላቸው መሆኑን እየገለጸ በሴቶች የነጻነት ቀን ያለአግባቡ ታስረው ህገወጥ እርምጃ በአባላቶቻችን ላይ የወሰዱትን የፖሊስ አካላት በህግ የምንጠይቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ በተጨማሪም ይህን መሰሉ የህገ ወጦች እርምጃ ሳይገታን ትግላችንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
መጋቢት 12 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ
Link:-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11514/

Thursday, March 20, 2014

በጋዜጠኞች ላይ ያለ ማስረጃ የሚሰነዘሩ ውንጀላዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እንጠይቃለን!

March 20, 2014
ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) የተሰጠ መግለጫ
ማህበራችን ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዶ የምዝገባ ሰርተፊኬት ለማግኘት የጀመረው እንቅስቀሴ በቅርቡ ከመንግስት አወንታዊ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ የተቋቋመለትን አላማ ለማሳካት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅና የመናገር ነፃነትን ከማበረታታት ባለፈም ከአህጉራችን አፍሪቃ ጋዜጠኞች ጋር በመተባበር የመላው አፍሪቃ ጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቅና የመናገር ነፃነትን የሚያበረታታ አህጉራዊ ተቋም ለመመስረት ተነሳሽነትን ወስዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡም የምስራቅ አፍሪቃ ጋዜጠኞችን በማስተባበር አህጉር አቀፍ እንቅስቃሴያችንን ለማስጀመር ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተግባር ጋዜጠኛውን ሳይወክሉ የጋዜጠኛውን ስም የያዙት የኢጋማ፣ የኢነጋማና የኢብጋህ አመራሮች ነን የሚሉት ግለሰቦች በመቀናጀት በየሚዲያው እየቀረቡ ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ተቋማትን ለማሸማቀቅ ያለመ ውንጀላና አሉባልታ የመንዛት ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ ግለሰቦቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቀርበው በጋዜጠኞች ላይ ከሽብር ፈጠራ እስከ ሀገር ማተራመስ የደረሰ የውንጀላ መዓት ቢደረድሩም አንዳችም ማስረጃ አላቀረቡም፡፡
ለምሳሌ የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ (ቅጽ13 ቁጥር 737) ላይ ስማቸውን ደብቀው ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ጋዜጠኞች ሀገር ለማተራመስና ሽብር ለመፍጠር እየተዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ “ምን ማስረጃ አላችሁ” ለሚለው የጋዜጠኛዋ ጥያቄ የመለሱት “እኛ እና እነሱ እንተዋወቃለን፡፡” የሚል አስገራሚ መልስ ነው፡፡ ይህ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ጋዜጠኞችን ለማሸማቀቅ የተወረወረ በመሆኑ የኢጋማ፣ የኢነጋማና የኢብጋህ አመራሮች ነን የሚሉት ግለሰቦች ጋዜጠኞችን እና የሚዲያ ተቋማትን ያለ ማስረጃ መወንጀላዎች ባስቸኳይ እንዲያቆሙ ይጠይቀል፡፡
በመቀጠልም በሪፖርተር ጋዜጣ (የዕሁድ እትም ቅፅ 19 ቁጥር 1446) የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም “ኢጋማ በምስረታ ላይ ያለውን የጋዜጠኞች መድረክ አስጠነቀቀ” የሚል ዜና ተመልክተናል፡፡ ሆኖም በጋዜጠኞች ስም ተሰባስበው ጋዜጠኛውን የሚጠቅም አንዳች እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ከመተኛታቸው ብዛት አልጋቸው ለረገበ ማህበራት ማስጠንቀቂያ ምላሽ በመስጠት ጊዜ በመሆኑም ምለሻችን በዝምታ መስራት ነው፡፡
የግለሰቦቹ የውንጀላ ንግግር የሚያስረዳው ከህግ፣ ከሞራል እና ከሙያዊ ስነምግባርም በላይ ራሳቸውን ለመሾም የሚፍጨረጨሩ መሆኑን ነው፡፡ ግለሰቦቹ በተለያዩ ጊዜያት መንግስት የፕሬስ ተቋማት ላይና ጋዜጠኞች ላይ የወሰዳቸውን ኢ-ህገመንግስታዊ እርምጃዎች እንደ ጋዜጠኛ ማህበር መሪ ከመኮነን ይልቅ የመንግስትን እርምጃ ሲያወድሱ ተስተውለዋል፡፡ በተጨማሪም በእስር ላይ ሆነው ህክምና በመከልከላቸው ለከፋ ስቃይ ስለተዳረጉ ጋዜጠኞችም ትንፍሽ ሲሉ አልታየም፡፡
እነዚህ የጋዜጠኛ ማህበራት መሪዎች ነን ያሉት ግለሰቦች እንደማህበር መሪ ሳይሆን እንደ ስለላ ተቋም ጋዜጠኞች እና አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ሃገር ለማተራመስና የሽብር ጥቃት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ መረጃ እንዳላቸው በይፋ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም
1ኛ. የሶስቱ ማህበራት መሪዎች አለን የሚሉትን መረጃ ለመንግስት በአፋጣኝ ሳይሰጡ መቆየታቸው በሀገራችን ህግ መሰረት ሊጠየቁው እንደሚገባ እንዲሁም
2ኛ. የሶስቱ ማህበራት መሪዎች በጋዜጠኞች እየተቀነባበረ ነው ካሉት የሽብርና ሀገር የማተራመስ እንቅስቃሴ ጀርባ እንዳሉ የጠቀሷቸውን ኤምባሲዎች በግልፅ ጠቅሰው ለመንግስት እና ለህዝብ እንዲያስታውቁ እንጠይቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ)
መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም
Link:-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11487/

Wednesday, March 19, 2014

“ነገረ-ኢትዮጵያ” የሰማያዊ ፓርቲ ጋዜጣ (ቅፅ 1 ቁጥር 4)

March 19, 2014

Negere Ethiopia Issue 4ነገረ-ኢትዮጵያ ርዕሰ አንቀጽ የህዝብ የአገልግሎት ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ ያሻል!

…በውሃ እጥረት ምክንያት ተማሪዎችና አዛውንቶች ካለ አቅማቸው ከሰፈር ሰፈር እየተንከራተቱ በጀርባቸው ለመሸከም ተገደዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ምክንያት ህዝብ ስልክና ኢንተርኔት መጠቀም አልቻለም፡፡ ባልታቀዱ ግንባታዎች ምክንያት የሚፈራርሱት መንገዶች ህዝብ በሰዓት ወዳሰበበት ቦታ እንዳይደርስ አድርገዋል፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች የሰማይ ያህል በራቁበት ወቅት ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ህዝብ ሊያገኘው በሚገባው አገልግሎት ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነውበታል… 
[ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]
Link:_http://ecadforum.com/Amharic/archives/11464/

Tuesday, March 18, 2014

በነፃነት ቀን ነፃነት ማጣት!

March 18, 2014
ይድነቃቸው ከበደ
Young semayawi party female activists
ሰብአዊ መብቶች እያንዳንዳችን ሰው በመሆናችን ብቻ የሚገቡን ከሰብአዊነታችን ተለይተው ሊታዩ የማያችሉ መብቶች ናቸው፡፡ መንግስታት እነዚህን በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን ሰብአዊ መብቶች ለማክበር ለማስከበርና ለማሟላት በቀዳሚነት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህም መሰረት ኃላፊነት ከፈረሙ ቀደምት አገራት መካከል ኢትዩጵያ ትገኝበታላች፡፡
ይሁን እንጂ የሴቶች ሰብአዊ መብቶች በሚፈለገው መልኩ ተግባራዊ ካለመሆኑ ባሻገር ኢ-ፍትሃዊነት እጅግ የበዛ ነው፡፡ ይህም በመሆኑም እ.ኤ.አ. በ1908 በአሜሪካ ኒወርክ ከተማ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ይሰሩ የነበሩ ላብአደር ሴቶች ‹‹ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያና የተመቻቸ የሥራ ሰዓት ለሴቶች›› በሚል መፈክር የሥራ ማቆም አድማ በማካሄድ የሴቶች ድምፅ እንዲስተጋባ አድርገዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የዓለም ሴቶች በማህበር በመደራጀት ትግላቸውን በማጠናከራቸው የዓለም መንግስታትን አስተሳሰብ በመለወጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገሮች የሴቶች መብት ስምምነት/ኮንቪክሽን/ እንዲፈራረሙ እብይ ምክንያት ሆነዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1910 በኮፕን አገር ከተማ በተደረገው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባሄ ላይ የመነሻ ሃሳብ በማቅረብ ማርች 8 በየዓመቱ እንዲከበር ያደረጉት ሴቶች ለመብታቸው ያደረጉትን አስታውጾ ለመዘከር ዓለም አቀፍ መድረክ ለማመቻቸት በመቻላቸው ስማቸው በአክብሮት ይነሳል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉን ያከበሩት ጀርመን፣አውስትራሊያ፣ሲውዘርላንድ እና ዴንማርክ ለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

መንግስት ስለ ጣይቱ ልጆች ጨንቆት ዋለ (Semayawi Party Update)

March 18, 2014
Semayawi Party- Ethiopia (Update)
ምንም የረባ መከራክሪያ ያላቀረበው ፖሊስ መናገር አቅቶት ሲንተባተብ ነው የዋለው በተጨማሪ ሌሎች መያዝ የልቻልናቸው 20 እሩጫው ላይ የነበሩ ሴቶች ስላሉ በማለት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል ሲጀምር ችሎቱ የታየው በጽ/ቤት ነው የነበረው የሰዉ ብዛት ያስጨነቀው መንግስት ሰዉ በችሎት እንዳይታደም ክርክሩን እንዳይሰማ በጣም ጠባብ በሆነችው ቢሮ ከአቅሙዋ በላይ የሆኑ ተከሳሾችን ለማሰተናገድ ተገዳለች ውሳኔ መስጠት የማይችለው ዳኛ ለነገ መጋቢት 10/2006 በመደበኛ ይታይ በሚል ተልካሻ ምክንያት ቀጥሮአቸዋልየጣይቱ ልጆች ግን በጣም በሚያሰድሰት ሞራልና የትግለ ሰሜት ላይ ሆነው ለማየት ችለናል፡፡
ችሎቱንም ለመከታተል የተለያዩ ሀገራት የኢንባሲ ተወካዮች፤ የሰማያዊ ፓረቲ አባላትና ደጋፊዎች እነዲሁም ጋዜጠኞች ተገኝተዋል
እወነት ሁሌም ታሸንፋለች ሁሌም ከጎናችሁ ነን!!!

Monday, March 17, 2014

በዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ዝክር፤ በእህቶቻችን ኮርተናል! (ግንቦት 7)

March 17, 2014
Ginbot 7 weekly editorial
ለዘንድሮው ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን መታሰቢያ በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው የሩጫ ትዕይንት ላይ ወጣት ሴቶች ባሳዩት ልበ ሙሉነት ኮርተናል። የሩጫውን ትዕይንት አስታከው፣ በአብዛኛው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እንደሆኑ የተነገረላቸው ወጣት ሴቶች ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለህሊና እስረኞች መፈታት እና ለሀገር አንድነት ድምፃቸውን ከፍ አድረገው ጮኸዋል፤ ዘምረዋል። እነዚህ ወጣት ሴቶች በሥርዓቱ ምን ያህል እንደተማረሩ በቃላትም በአካል ንቅናቄም አሳይተዋል። ዘረኛውና ፋሽስቱ ወያኔ ግን “ለምን ተቃወማችሁኝ” ብሎ አስሯቸዋል፤ ከፊሎቹም የደረሱበት አይታወቅም። በእህቶቻችን ቆራጥነት ኮርተናል፤ በወያኔ የፈሪ ዱላ ደግሞ ተቆጥተናል። በ1997 እና 98 “የወላጆቻችን ድምጽ ይከበር” ያሉ ሕፃናትን የጨፈጨፈው ወያኔ በ2006 ወጣት ሴቶችን ከማሰቃየት ይመለሳል ብለን አናምንም። ወያኔ እስካልተወገደ ድረስ የፈሪ ዱላው የማይቀር ነገር ነው።

የወንዶቹን ያህል የተዘገበ አይሁን እንጂ በክፉም በደጉም ሴቶች ያልተሳተፉበት የኢትዮጵያ ታሪክ የለም። የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን እንኳን ብናይ በፋሽስት ወረራ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በአርበኝነት ዘምተው አዋግተዋል፤ ተዋግተዋል። በተለያዩ ምክንያቶች መዝመት ያልቻሉት ደግሞ በውስጥ አርበኝነት ተሰልፈው የጠላት ምስጢሮች ለአርበኞች እንዲደርሱ በማድረግ ከፍተኛ ጀብዱዎችን ፈጽመዋል። ከፋሺስት ወረራ ወዲህ በነበሩ ዓመታት ውስጥም ለፍትህ እና ለነፃነት በተደረጉ ተጋድሎዎች ሴቶች ጉልህ ተሳትፎ ነበራቸው። በተማሪዎች ትግል ውስጥ ለምሳሌ፣ ወጣት ሴቶች በአመራር ደረጃ በመሳተፍ ትግሉን መርተዋል፤ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍለዋል። ከዚያ ወዲህም በነበሩት ዓመታት በኢሕአፓ እና ሌሎችም ድርጅቶች አመራርና አባልነት ተሳትፈው ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ነበሩን። በቅርቡም በምርጫ 97 እንቅስቃሴም የሴቶች በተለይም የወጣት ሴቶች ተሳትፎ ምን ያህል ጉልህ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነውና እናስታውሳለን። ለምርጫ ድምጽ መከበር ወጣት ሽብሬ ደሣለኝን ጨምሮ በርካታ ሴቶች ሕይወታቸውን ሰውተዋል፤ ከዚያ የበለጡት ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዛሬም እንደ ርዕዮት ዓለሙ የመሳሰሉ ጀግኖች በወያኔ ወህኒ ቤቶች እየማቀቁ፤ በየእለቱ ሰቆቃ (ቶርቸር) እየተፈፀመባቸው መሆናቸው በሀዘንና በቁጭት እናስባቸዋለን።
በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ አስፈላጊነት በመፈክር ደረጃ አንስተን የምንተወው ጉዳይ አይደለም። የሴቶች ተሳትፎ ያልታከለበት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ግቡም አይመታም፤ ቢመታም ዋጋ የለውም።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የተካሄዱትን የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ አብዮቶችን በአንክሮ የተከታተለ ማንኛውም ሰው ከሚገረምባቸው ነገሮች አንዱ ሴቶች ያሳዩት ቆራጥነት እና ያካሄዱት ብስለት የተሞላው ትግል ነው። በቱኒዚያ የወጣቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ወጣት ሴቶች ከመጀመሪያው ጀምሮ የአመራር ቦታ በመያዝ ተሳትፈዋል። በግብጽም የወጣት ሴቶች እልህ ከወንዶቹ በልጦ ታይቷል። አሁን በዩክሬን ውስጥ የምናየው ሀቅም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

Saturday, March 15, 2014

አንድነት – የአማራውን ሕዝብ ክብር የደፈሩና ያዋረዱ አምባገነን ገዥዎች ለፍርድ ይቅረቡ!!!(መግለጫ)

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

«ጉድ ሳይሰማ…» እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በስርዓቱ እየተፈፀመበት ካለው ጭቆናና በደል፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ገፈፋ፤ አፈናና ስደት፤ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት በተጨማሪም በአምባገነን ገዥዎች እየተዋረደ፣ በአደባባይ እየተሰደበና ሰብዓዊ ክብሩ እየተጣሰ ይገኛል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖም ሀገራችን ላይ ያለው ስርዓት ህዝቡን የሚያዋርድ፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ስልጣኑን የሚያስቀድም፣ ለህዝብ ጆሮ የሚሰጥ አስተዋይ መሪ የሌለው ነው፡፡

ለዘመናት ያልተፈቱ ችግሮችና በመሪዎቹ የሚፈጠሩ ችግሮች ትከሻውን ያጎበጡት የኢትዮጵያ ህዝብም ስርዓቱን ከነችግሩ መሸከሙ አልበቃ ብሎ መሪ ነን በሚሉት እየተበሻቀጠና ለውርደት እየተዳረገ ይገኛል፡፡

ፓርቲያችን በትኩረት እየተከታተለው ያለውና ሰሞኑን የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይና በኢሳት ይፋ የተደረገው የአማራ ክልል ም/ ፕሬዘዳንትና የብአዴን ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን፣ የአማራውን ህዝብ በአደባባይ መሳደባቸውንና ማዋረዳቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች መለቀቃቸውና የክልሉ መንግስት ለማስተባበል እንኳ ዝግጁ አለመሆኑ የሚያሳየው ንቀትንና ጥላቻን ብቻ ሳይሆን እንመራዋለን የሚሉት ህዝብ ትከሻ ላይ ተቀምጠው ፀረ ህዝብ አቋም እንደሚያራምዱ ነው፡፡ ፓርቲያችን የብአዴን/ኢህአዴግ ባለስልጣን በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀሙትን ክብር የሚነካ አሳፋሪ ድርጊት በቸልታ ሊመለከተው እንደማይችል አስረግጦ ለመናገር ይወዳል፡፡ ፀረ ህዝብ አቋም የሚያራምዱ አምባገነኖችንም ከህዝብ ትክሻ ለማውረድ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡ አንድነት በቅርቡ በጉራ ፈርዳና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በዜጎች ላይ የተወሰደው የማፈናቀል ተግባር ስርዓቱና የስርዓቱ መሪዎች የፈጠሩት ችግር እንጅ የአካባቢው ሕዝብ የፈጠረው እንዳልሆነ ያምናል፡፡
አቶ አለምነው መኮንን የተባሉት ባለስልጣን የአለቆቻቸውን የዘወትር አባባል በማስረገጥ እመራዋለሁ የሚሉትን የአማራ ህዝብ «ሰንፋጭ የሆነ ትምክህተኝነት የተጠናወተው፣ ትምክህተኝነቱን ያልተወ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ መርዝ ንግግር የሚናገር ወዘተ» ካሉ በኋላ «የትምክህት ልጋጉን ማራገፍ አለበት» በማለት እንደሌሎች ብሄረሰቦች ሁሉ ለዚች ሀገር ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል ዋጋ የከፈለውን የአማራ ክልል ህዝብ ዋጋ በማሳጣትና የሌሎች ጠላት አድርጎ በማቅረብ የማጥላላት ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
ፓርቲያችንም ይህንን አሳፋሪና የዜጎችን ክብር የደፈረ የባለስልጣኑ አባባል በቸልታ የሚታይ ሆኖ አላገኘውም፡፡
ስለዚህ፡-

1. ግለሰቡ በዚህ የተዛባ አመለካከቱ ለአማራ ክልል ህዝብ መሪ ሊሆን ስለማይችል በአስቸኳይ ከፓርቲና ከመንግስት ኃላፊነቱ እንዲነሳና ለህዝቡ ይፋ እንዲደረግ፤
2. ህዝቡን ያዋረደው ባለስልጣን ላይ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ግን የግለሰቡ አመለካከት የብአዴንና የክልሉ መንግስት አቋም አድርገን የምንወስድ መሆኑ እንዲታወቅ፤
3. አንድነት ፓርቲ ፀረ-ህዝብ አቋም ያለው ግለሰብ ባደረገው የህዝብ ጥላቻ ንግግር (Hate speech) ተነስቶ ለሕግ የሚያቀርብ መሆኑ እንዲታወቅ፤
4. ፓርቲያችን ህዝቡን በማስተባበር በባህርዳር ከተማ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠራና ድርጊቱን የማውገዝና እንዲቆም የማድረግ ርምጃ የሚወስድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
ስለዚህ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የክልሉን ህዝብ እየመራው ያለው ብአዴን/ኢህአዴግ ለህዝብ ክብር የሌለው ድርጅት መሆኑን አውቆ ከፓቲያችን ጎን በመቆም እንዲታገለው ጥሪ እናቀርባለን፡፡


ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም
Link;_https://www.andinet.org/
Posted by Bethel Solomon

የኢህአዴግ ማመልክቻ ድጋሚ ውድቅ መደረግ አለበት!

በመጀመሪያ አፋኝ ሕጎች መሠረዝ አለባቸው!

የተፈጥሮ ሃብትን በትክክለኛ መንገድ ለሕዝብ ጥቅም መዋሉን በመከታተል ለአገራት እውቅና የሚሰጠው The Extractive Industries Transparency Initiative (EITI) ለተሰኘ ዓለም ዓቀፋዊ ተቋም ኢህአዴግ በድጋሚ ያቀረበው የእውቅና ጥያቄ ማመልከቻ ውድቅ መደረግ እንዳለበት ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት (Human Rights Watch) ድርጅት አስታወቀ፡፡ ኢህአዴግ የእውቅና ማመልከቻ አስገብቶ ውድቅ ተደርጎበት የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ የታወጁት አፋኝ ሕጎች እስካልተወገዱ ድረስ ድጋሚ ማመልከቻው ውድቅ ሊደረግ እንደሚገባው ጨምሮ ተነግሯል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ከሳምንታት በፊት “ኢህአዴግ ራሱ ባወጣው አፋኝ ሕግ ታፈነ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና ጉዳዩን በስፋት ዘርዝሮ ነበር፡፡ “EITI የዛሬ 11ዓመት አካባቢ የተቋቋመ በተፈጥሮ ሃብት ዙሪያ ዕውቅና የሚሰጥ ድርጅት ሲሆን ድርጅቱ የተፈጥሮ ሃብት የህዝብ መሆኑን የሚያምን ሲሆን ማንኛውም የተፈጥሮ ሃብት – ማዕድን፣ ዘይት፣ ብረታብረትና ጋዝ – ከመሬት በሚወጣበት ጊዜ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚኖረውን ያህል ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለባቸው አገራት ድርጊቱ ለሙስና እና ግጭት በር እንደሚከፍት ይናገራል፡፡ በመሆኑንም ድርጅቱ (EITI) አገራት ለሚያቀርቡት የዕውቅና ጥያቄ ማሟላት ያለባቸውን መስፈርት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ልማትና እድገት በሚል ሰበብ የሕዝብ ሃብት የሆነውን የተፈጥሮ ሃብት በማውጣት የህዝባቸውን መብት ለሚረግጡ አገራት የሚያቀርቡትን የዕውቅና ማመልከቻ ውድቅ ያደርጋል፡፡”
በወቅቱ ጎልጉል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው “ኢህአዴግ ያቀረበው የእውቅና ጥያቄ ውድቅ መደረጉ እውነት ነው። ምንጩ እንዳሉት ኢህአዴግ በውሳኔው በመበሳጨት ይግባኝ ለመጠየቅ በዝግጅት” ላይ መሆኑን ጠቁሞ ነበር፡፡
የEITI ዕውቅናን ለማግኘት ቋምጦ የነበረው ኢህአዴግ በድርጅቱ ውሳኔ ባለመደሰት ጥቂት ዓመታትን ቆጥሮ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ በአቶ ሃይለማርያም በመመራት በድጋሚ የዕውቅና የማግኘት ዘመቻውን ማጠናከር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የማዕድን ሚ/ር መ/ቤትም የEITI ዕውቅና ማግኘቱ በጣም የሚያስፈልግ እንደሆነ በይፋ በመናገር ዘመቻውን አጧጡፎ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ለዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን አሠራር በዓለምአቀፉ ድርጅት ላይ ተግባራዊ በማድረግ ኢህአዴግ Ethiopia Revenue Transparency Initiative (ERTI) የሚባል “ተለጣፊ” ተቋም በመመሥረት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደቆየ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ለEITI በጻፈው ደብዳቤ ላይ መግለጹንጎልጉል ጨምሮ ዘግቦ ነበር፡፡
clare
ክሌር ሾርት
ዛሬ የወጣው የሰብዓዊ መብት ድርጅት መግለጫ ይህንኑ የኢህአዴግን ጥያቄ የሚያስረዳ ሲሆን በአፋኝ ህጎቹ ላይ አንዳችም ለውጥ ያላሳየው ኢህአዴግ ማመልከቻው ውድቅ መደረግ እንዳለበት መግለጫው በአጽዕኖት ይናገራል፡፡ ምክንያቱንም ሲጠቅስ “የኢትዮጵያ መንግሥት ሚዲያውን አፍኗል፤ (ሰብዓዊ መብት እንዲከበር) እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሁሉ አድቅቋል” በማለት ያስረዳል፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ በፊት ባስገባው ማመልከቻ ላይ የEITI ቦርድ ውሳኔውን ሲያስተላልፍ “የመያዶች ሕግ የተሰኘው አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆን እስካልተደረገ” ማመልከቻው ሊታይ እንደማይገባው በዋንኛነት ማመልከቻው ውድቅ እንዲደረግ የተደረገበት ምክንያት እንደነበር የጠቀሰው የሰብዓዊ መብት ድርጅት መግለጫ EITI አሁንም ይህንኑ ውሳኔውን እንዲያከብር ጠይቋል፡፡
ማመልከቻው እንደገና እንዲታይና የቦርዱ የቀድሞ ውሳኔ እንዲቀለበስ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የቀድሞ የእንግሊዝ ዓለምአቀፍ ትብብር ሚ/ር የሆኑት ክሌር ሾርት መሆናቸውን መግለጫው ያስረዳል፡፡ እኚህ ግለሰብ የአፍሪካ አምባገነኖችን በመደገፍ የሚታወቁ ሲሆን ይህ ከጥቅማቸው ጋር የተሳሰረው ግንኙነታቸው አሁንም ኢህአዴግን እንዲደግፉ እንዳደረጋቸው ይነገራል፡፡ እንዲሁም በሌሎች ኢህአዴግ ባቋቋማቸው ዓለምአቀፋዊነት ሽፋን በተላበሱ ድርጅቶች ውስጥ የአመራር አባል በመሆን ሚስ ሾርት እንደሚያገለግሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የእንግሊዝ ፓርላማ አባል በነበሩበት ወቅትም ያላወጡትን ወጪ አውጥቻለሁ በማለት በብዙ ሺዎች የሚገመት ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ መሆናቸው በወቅቱ ዴይሊ ቴሌግራፍ ባወጣው መረጃ አጋልጦ ነበር፡፡ የተወሰነውን ገንዘብ የመለሱ ቢሆንም ጋዜጣው በወቅቱ ያወጣው መረጃ ግለሰቧ የሕዝብን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው የተጠቀሙ “ሙሰኛ” መሆናቸውን ያስረዳል፡፡
ከእነዚህና ሌሎች መረጃዎች አኳያ ኢህአዴግ በየቦታው እየደለለ “ባስቀመጣቸው” በመጠቀም የፈለገውን ለማድረግ ሲሞክር ዝም ሊባል እንደማይገባው በዚሁ ጉዳይ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የሚንቀሳቀሰውን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን ጠቅሶ ጎልጉል መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ መሠረት ኢህአዴግ የEITI አባል መሆን ከፈለገ ያወጣቸውን አፋኝ ሕጎች በሙሉ መሠረዝ እንዳለበትና የመናገር መብትን፣ የፕሬስ ነጻነትን፣ የመሰብሰብ፣ ወዘተ መብቶችን በይፋ ማክበር እንዳለበት እና የEITI የአባልነት ቅድመ መስፈርቶችንም በሙሉ ማሟላት እንደሚገባው ጨምሮ ገልጾዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ድርጅት ያወጣው መግለጫ ከዚህ በታች ይገኛል፡፡

Friday, March 14, 2014

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ተጨማሪ አራት ቀን እስር ቤት እንዲቆዩ ተደረገ

March 14, 2014
Semayawi Party- Ethiopia
Blue Party’s executives and female members
ባለፈው ሰኞ ፖሊስ መረጃ ለማሰባሰብ በሚል ፍርድ ቤት የ14 ቀን ጊዜ ጠይቆ 5 ቀናት እንደተፈቀደለት ይታወቃል፡፡ ዛሬ መጋቢት 5 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ችሎት ቢቀርቡም ፖሊስ አሁንም ‹‹ምርምራውን አልጨረስኩም፣ ተጨማሪ የምይዛቸው ሰዎች አሉ፣ የተያዙትም ቢለቀቁ ሌላ ወንጀል ይሰራሉ›› በሚል ሰባት ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡
በአንጻሩ የታሳሪዎቹ ጠበቃ ሆነው የቀረቡት የጋዜጠኛ ርዕት አለሙ አባት አቶ አለሙ ጌደቦ በበኩላቸው ፖሊስ ተሰጥቶት የነበሩት ሰባት ቀናት መረጃ ለማሰባሰብም ሆነ ሌሎች የምይዛቸው ተጨማሪ ሰዎች አሉ ያላቸውን ቢኖሩ ኖሮ ለመያዝ በቂ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ታሳሪዎቹ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሰሩና ቋሚ አድራሻ ያላቸው በመሆኑ በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን መከታተል ስለሚችሉ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ተከራክረዋል፡፡
Semayawi party activist court show up
በሌላ በኩል ታሳሪዎቹ በምርመራ ወቅት በፖሊስና ‹በደህንነቶች› እየተፈጸመብን ነው ያሉትን በደል ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ‹‹የታሰርነው በያዝነው አስተሳሰባችን ምክንያት ነው›› ያለው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ መታወቂያ ለማሳየት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች ‹‹ሰማያዊ ከሚባል አሸባሪ ወጥታችሁ ከእኛ ጋር ካልሰራችሁ መቼ እንደምንገላችሁ አታውቁም፡፡›› በሚል እንዳስፈራሩዋቸው ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ወንድ ፖሊሶች ሌሊት ሴቶች እስር ቤት ውስጥ በመግባት እንደሚያስፈራሩዋቸውም ተገልጻል፡፡ ሴቶቹ ታሳሪዎች ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ወንድ ፖሊሶች ከታሰሩበት እያስወጡ እንደሚያስፈራሩዋቸውም የየራሳቸውን አጋጣሚዎች ለፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ ወጣት አቤል ‹‹ከእኛ ጋር ከሰራህ የተሻለ እንከፍልሃለን›› ብለውኝ አልፈልግም በማለቴ እንገልሃለን ብለውኛል በማለት ገልጹዋል፡፡
በተቃራኒው ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ሌሎች ታሳሪዎች ላይ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን፣ በጋራ እንደሚዘምሩ፣ ቃል ለመስጠት ፈቃደኛ እንደማይሆኑ በመግለጽ ተጨማሪ 7 ቀን እንዲሰጠው በድጋሜ ጠይቋል፡፡ ዛሬ ጠዋት ወደ ችሎት ሲመጡ የታላቁን ሩጫ ቲሸርት ካለበስን አንሄድም ማለታቸውንም ታሳሪዎቹ በቀጣይነትም ወንጀል ሊሰሩ ይችላሉ ለሚለው መከራከሪያው እንደ ማስረጃ አቅርቧል፡፡ ዳኛው ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ እንዳደረሰው የተገለጸውንና ታሳሪዎቹ ሌሎች ታሳሪዎችን በማቀስቀስና በመረበሽ ያቀረበውን ክስ ላይ ምክር አዘል መልዕክት ካስተላለፈ በኋላ ተጨማሪ 4 ቀን የምርመራ ጊዜ ሰጥቷል፡፡
ችሎቱ መደበኛ ስራውን ይጀምራል ከተባለበት አንድ ሰዓት ዘግይቶ ሊጀምር ችሏል፡፡ በክርክሩ ወቅት መረዳት እንደተቻለውም ጠዋት ታሳሪዎቹ ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡበት ጊዜ በሩጫው ዕለት ለብሰውት የነበረውን የታላቁን ሩጫ ቲሸርት መልበሳቸውን ፖሊስ በመቃወሙ በነበረው አለመግባባት መዘግየቱ እንደተከሰተ ታውቋል፡፡
ፖሊስ ሰኞ ዕለት ያስመዘገበው የክስ ጭብጥ እንደሚያመለክተው ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋለው ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል፣ የጣይቱ ልጆች ነን፣ የምኒልክ ልጆች ነን፣ ዳቦ ራበን፣ ብለዋል በሚል ነው፡፡ በዛሬው የክርክር ሂደት እንደተስተዋለው ግን ፖሊስ የመጀመሪያዋን ጭብጥ ብቻ መዝዞ ተከራክሯል፡፡ መርማሪ ፖሊሱ በወቅቱ አሉኝ ያላቸውን የክርክር ነጥቦች በሚያስረዳበት ወቅት አለመረጋጋት ጎልቶ ይታይበት እንደነበር ተስተውሏል፡፡
Link:-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11410/
Posted:- Bethel Solomon

በአሜሪካ የሚኖረው የሕወሐት ወንጀለኛ

March 14, 2014
ከኢየሩሳሌም አርአያ
The Ethiopian author, former TPLF torture czar and spymaster “Professor” Bisrat Amare
Bisrat Amare former head of TPLF Intelligence
የሕወሐት አባል የሆነውና በአሜሪካ የሚኖረው ብስራት አማረ በርካታ ወንጀሎችን እንደፈፀመ የቅርብ ምንጮች አጋለጡ። ሕወሐት በረሃ እያለ የባዶ 6 እስር ቤት ዋና ሃላፊ የነበረው ብስራት አማረ የኢ.ህ.አ.ፓ አባላት የነበሩት እነ ፀጋዬ ገ/መድህን (ደብተራው) ጨምሮ በሕወሐት የተያዙትን በሙሉ ወረኢ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በነበረ እስር ቤት በጅምላ አሰቃይቶ እንደገደላቸው ምንጮቹ አረጋግጠዋል። በሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ሰዎች « ኢዲዩና ፊውዳል..» በሚል ባዶ 6 ተብሎ ይጠራ በነበረው እስር ቤት ተሰቃይተው እንዲገደሉ የተደረጉት በብስራት አማረ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቹ ከዚህ በተጨማሪ የድርጅቱን በርካታ አባላት እንዳስገደለ አያይዘው ገልፀዋል። እነተክሉ ሃዋዝ በዚህ ወንጀለኛ ከተገደሉት ይጠቀሳሉ ሲሉ ያክላሉ። በ1983ዓ.ም ሕወሐት/ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የሟቹ የደህንነት ሹም ክንፈ ገ/መድህን ምክትል የነበረው ብስራት አማረ ከቤተ መንግስት የጃንሆይ የነበረ ከፍተኛ ወርቅ በመዝረፍ መውሰዱን ያጋለጡት ምንጮቹ በዚህ የዘረፋ ወንጀል ሆለታ እስር ቤት እንዲገባ መደረጉን ያመለክታሉ። በነስብሃት ነጋና መለስ ዜናዊ ትእዛዝ እንዲፈታ ተደርጐ ወደ አሜሪካ የተሸኘው ብስራት አሜሪካ ሲጓዝ የዘረፈውን ወርቅ ይዞ እንደነበረ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ምንጮች በግርምት ይገልፃሉ። ብስራት አማረ አሜሪካ ከመጣ በኋላ ቅርስ የሆኑትንና የዘረፋቸውን ወርቆች መሸጡንና አንዲት ሴት ለማሻሻጥ የተቀበለችውን 1ኪሎ ወርቅ ከወሰደች በኋላ እንደካደችው ማወቅ ተችሎዋል። ብስራት አማረ ስለዚሁ ጉዳይ ተበሳጭቶ የነገራቸው ምንጮች ማረጋገጫ ይሰጣሉ። የብስራት ታናሽ ወንድም የሆነውና በደህንነት ቢሮ ይሰራ የነበረው ታጋይ ጠስሚ (ጠስሚ -ትርጉሙ ቅቤ ማለት ነው) ከስራው በመልቀቅ የአስመጪና ላኪነት ትልቅ ቢዝነስ መክፈቱን የጠቆሙት ምንጮቹ አክለውም፥ ድርጅቱ የተከፈተው ብስራት አሜሪካ ከገባ በኋላ በላከለት ገንዘብ መሆኑን አስታውቀዋል። (ስለዚሁ ጉዳይ በ1995 ዓ.ም በኢትኦጵ ጋዜጣ መረጃው ይፋ መደረጉና የብስራት ወንድም ቅቤ ኢትኦጵ ቢሮ ድረስ በመምጣት የጋዜጣውን አዘጋጅ በድንጋጤ ተውጦ “የራሴን ቢዝነስ ተቋም ነው፤ እነማን መረጃ እንደሚሰጧችሁ አውቃለሁ። እባካችሁ የእኔንም፣ የወንድሜንም ስም አታንሱ?” በማለት ተማጽኖ አቅርቦ ነበር።) ብስራት አማረ ከሽማግሌው ስብሃት ነጋ ጋር ባለው የጠበቀ ግንኙነት ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለስ መቆየቱን ያወሱት ምንጮቹ፣ ወንጀለኛውና ዘራፊው መቀሌ ሄዶ አስገደ ገ/ስላሴን እንደከሰሰ አስታውቀዋል። የደርግ ወንጀለኞች ከአሜሪካ በገዢው ፓርቲ እየተወሰዱ ነገር ግን የኢ.ህ.አ.ፓ አባላትንና ሌሎች ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ የፈጀና የአገር ቅርስ የዘረፈ ወንጀለኛ ጠያቂ ማጣቱ አስገራሚ ነው ብለዋል ምንጮቹ። ጠያቂ አካል ካለ በወንጀለኛው ብስራት አማረ ላይ ለመመስከር ፈቃደኛ መሆናቸውን አክለዋል። ይህን ምስክርነትና ማረጋገጫ ሊሰጡ የሚችሉና በአሜሪካ የሚኖሩ ሶስት የቀድሞ የሕወሐት ሹሞች እንዳሉና የብስራትን ወንጀል ጠንቅቀው የሚያውቁ መኖራቸውን አያይዘው ጠቁመዋል።
Link:-http://ecadforum.com/Amharic/archives/11408/
Posted by :- Bethel Solomon

አሜሪካ የበለጠ ትናገር! (ከጸጋዬ ገ/መድህን አርአያ)

March 13, 2014
ከጸጋዬ ገ/መድህን አርአያ
ነፃነቴን ካልሰጣችሁኝ ሞትን እመርጣለሁ
ፓትሪክ ሔንሪ Give me Liberty or Give me Death
ፍሬደሪክ ዳግላስ (1818- 1895) ከባርያ እናትና ከነጭ አባት የተወለደና ራሱም ቢሆን በቦልቲሞር (ሜሪላንድ) የቤት አሽከር ሆኖ የቆየ ሰው ነበር። አንድ ማለዳ ጁላይ 4 ቀን 1852 ን ተንተርሶ (አንተርሶ) በሮቼስተር ከተማ (ኒውዮርክ) ንግግር እንዲያደርግ ጥሪ ይደርሰዋል። ደብዳቤው ሲደርሰው እንደ እብድ ከራሱ ጋር መነጋገር ያዘ። መቸም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ለማመን የሚከብድ አጋጣሚ ሲመጣብህ ናላህ ይበጠበጣል። ፍሬደሪክ ዳግላስም “በእርግጥ ይህ ደብዳቤ ለእኔ የተጻፈ ነው? የተቀባይ ስምና አድራሻ ስሕተት ተፈጽሞ ይሆን?” ሳይል አልቀረም። ዳግላስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ጭንቅላቱን ሲበጠብጥ ቆይቶ ትንሽ አረፍ አለ። ሲነቃ ይኸ ዕድል እንዳያመልጠው ፈለገ። ይልቁንም የሚናገርበት ርዕስ መጣለት። “ በመሰረቱ እኔን ባርያውን በዚህ በዓል ላይ እንድገኝ- ለዚያውም ተናጋሪ መሆኔን ሳስበው ይህ ሁሉ ግብዝ- የግብዝም ግብዝ ነው አለ። ይበልጥ ደግሞ ለተሰብሳቢው ስለጁላይ 4 (ነፃነት በዓል) እንድናገር እኔን ባርያውን መጋበዛቸው ሌላው ግብዝና ነው ” አለ። ለማንኛውም ንግግሩን አዘጋጀ። በዚያ ወቅት በሮቼስተር ከተማ ያደረገው ንግግር እስከ ዛሬ ድረስ ከዓለም ታላላቅ ዲስኩሮች አንዱ ለመሆን በቅቶአል። “ጁላይ 4 ቀን ለመሆኑ ለባርያው ምኑነው? What to the Slave is the Fourth of July?
ዛሬ ከብረት በከበደ ክንድ ኢትዮጵያን እየገዙአት የሚገኙት ጌቶች- አዳዲስ መሳፍንት- አዳዲስ መኳንንት፣ አዳዲስ ዲታዎች…የንግስ በዓል ከሳምንታት በኋላ ይከበራል። (በዩጐዝላቩ ጂላስ The New Class, ወይም ከሮማውያን ዘመን አንስቶ Nouveau Riche ቀላል ድግስ አያውቁም። ስለዚህ ጉንበት 20 ቀን በታላቅና ታይቶ በማያውቅ ድምቀት ይከበር ዘንድ ዝግጅቱ እየተሟሟቀ ነው። አገር ያፈራው ትልልቁ የሐረር ሰንጋ፣ ወደል ወደል የሚያክለው የወለጋ ላታም በግ ወዘተ ተመርጦ ተመርጦ ይቀርባል። ሻምፓኙ፣ ውድ ውዱ አይሪሽ መጠጥ- ዊስኪ፣ ድራንቡዬ፣… የፈረንሳይ ኮኛኮች፣ ምርጥ ወይን ጠጆች..ያልፍላቸዋል። ምንም ማጋነን የለበትም። ጫካ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ እንኳ ለድግስ ስንትናስንት ሚሊዮን ብር ሲያወጡ እንደነበረ ከጉያቸው የወጣው ጠንካራ ኢትዮጵያዊ…ገብረ መድኅን አርአያ ገልጦታል።
“ኑና ጉንበት 20ን አብረን እናክብር” ተብለው የተጠሩ ወይም እንጠራለን ብለው ቀኑን እንደወላድ እየቆጠሩ- የራቀባቸው ሰዎች የሉም አትሉም። እናንተም እንደኔ። ከውጭ የሚጋበዙ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። አዳራሾች-ሆቴሎች- በየደረጃው… ላይበቁ ነው። እሸሸ ገዳሜው፣ አስረሽ ምቺው ደግሞ የሚጠበቅ ነው። ስለገዢዎቻችን ሀብትና ንብረት ያልተባለ ነገር የለም። ይኸ ደግሞ የሞራሉን ቁልቁለት ምንኛ እንደ ተያያዙት ስም እየጠቀሰ መረጃ የሚሰጠንን ውስጥ አወቅ ኢየሩሳሌም አርአያን ማድነቅ እወድዳለሁ። በሽምግልናና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ በሚገባቸው ዕድሜ የእኝኝ ብላ ባዝራዎች፣ አንድና ሁለት (በቀን) የማይበቃቸው የወንድ መለኮኖች አሉባቸው። ከዚህ ተራ ውስጥ ሁለት ሰዎችን ብቻ (በረከተ-መርገም ስምዖንና ስዬ አብርሃ) ነፃ ያወጣቸው ደግሞ ተስፋዬ ገብረ-አብ ነው። ስለሆነም ዳንኪራውና ስድ የሆነው በዓል የሚጠበቅ ነው። እኛም የኢትዮጵያ ጉስቁሎች የሌላ ሕዝብ በዓል በሥነ ሥርዓት መጠበቅ አለብን። የበዓሉን መንፈስ ማደፍረስ፣ ማደናቀፍና ማቃወስ በአሸባሪነትና በመሳሰለው አንቀጽ ያስቀጣል። አዎን ጉንበት 20 ቀን የድግሦች ድግሥ፣ አውራ በዓልና የድግሦችና የበዓሎች ሁሉ እናት ናት። ማን ያውቃል? ድሮ ጃንሆይ አጤ ኀይለ ሥላሴ ሐምሌ 16ን “የትዮጵያ የልደት ቀን” እንዳሉአት እነዚህ አዳዳሶቹ መሳፍንትም ጉንበት 20ን “እውነተኛው የኢትዮጵያ ናጽናት ቀን” ቢሉት አይደንቀኝም። ( ብቻ ማን ነበር- የአንዱ ሕይወት የሌላው መርዞ ነው- ያለው?)
let America speak
በአገራችን የድግስ ነገር ሲነሳ ትንሽ የማስታውሳቸው ነገሮች አሉ። በአጤው ጊዜ ጃንሆይ የተወለዱበት (ሐምሌ16) እንዲሁም የነገሱበት (ጥቅምት 23) ይከበሩ ነበር። ለኢትዮጵያ ባሕልና ፖለቲካ እንግዶች የሆናችሁ ወጣቶች ምናልባት አታውቁት ይሆናል እንጂ በክብርም ቢሆን ቤተ መንግስት ስትጠሩ ግርግሩ ብዙ ስለሆነ ትንሽ ጨፈቃ ትቀምሳላችሁ። እንጀራው በእግር የተቦካ ነው ይባላል። ለማንኛውም “የንጉስ በረከት” አይናቅም ትባላላችሁ። (ይህንን የበለጠ ለማወቅ ፍቅር እስከ መቃብርን ያነብቡአል) ወደኋላ ጊዜ የሐምሌ 16 በዓል አከባበር ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተሰጥቶ ነበር።
የድግስ ነገር- በመንግስት ሰፈር- ብዙ ምልኪ አለበት። ስለ ጃንሆይ መንግስት አወዳደቅ ብዙ ቢባልም ለጊዜው አንዱን አነሳለሁ። አንዳንድ ሚኒስትሮች እጅግ ከቅብጠትም ባሻገር ስለሄዱ ክራር ይዘው ወደ መሸታ ቤት መሄድ አብዝተው ነበር። የዛሬዎቹ ከእነዚያ ጋር ባይወዳደሩም ትንሽ ትንሽ ሕዝብንና አኗኗሩን ወደ መርሳቱ ደርሰው ነበርና ሌላው ቀርቶ ከመሳፍንቱ አንዱ የነበሩት ጄኔራል ዐቢይ- “አውቀን እንታረም” የሚል መጽሐፍ ደርሰው ነበር። ጠንቃቃው ጄኔራል “አውቀን ካልታረምን ሌላው ቀርቶ ሬሳችን እንኳ የወደቀበት አይታወቅም” ብለው ነበር። አዎን አርማጌዶን በዓለም ፍጻሜ ላይ የሚከሰት ሳይሆን ያልታሰበ የእልቂት መውረድም አርማጌዶን ሊባል ይችላል። ያ ወቅት የሞራል ድቀት ሥጋና ደም ገዝቶ የሚታይበት፣ ሕዝብ ሲያልቅ አንዳንድ ሹማምንት መንደላቀቅ ያበዙበት ነበር። ደርግ ጃንሆይን ከሥልጣን ሲያወርድ “ሕዝብ በሺህ ቤት ሲረግፍ እነሱ በእሸሸ ገዳሜ ተጠምደው…” እያለና የቀለጠ ድግስ በቴሌቪዥን እያቀረበ ነበር። ድግስ….
ደርግ ራስዋ በራስዋ ያመጣችው ጣጣም አለ። ወደ ሥልጣን የመጣበትን ቀን ለማክበር ብልጭልጩንም ማናምኑንም ሰልፉንም…ሲያበዛ የእንግሊዝ ጋዜጠኞች በሁለት መቶ ሺህ ዶላር ውስኪ ሸጥን አሉና…የደርግ መሰላል ወደታች ብቻ የሚያወርድ ሆነ። ድግስ እየተኮነነ መጣ። ድግስ እየተጠቀሰበት ወረደ። ሁለት መቶ ሺህ ሕዝብ በረሃብ አለቀ ብሎ ተሳለቀ ተባለ። በራሱ ጊዜ ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ ተርቦ ውስኪ ተራጩ ተብሎ ለወያኔ ፕሮፖጋንዳ ተመቸ። እዚህ ላይ ያነሳሁት የጉንበት 20 አከባበር ያንኑ እድል ይከተል ይሆናል- ይከተላልም- ቁልቁለቱን ጀምሮአል በሚል ነው። ድግሶች በሦስቱ መንግስታት- የሥልጣን መልቀቂያ ጊዜ ምልክቶች- ብልሽትሽቱ የወጣ መንግስት ማክተሚያ ወቅቶች ሆነው አይተናቸዋል። ( ሁሉም የእጁን ያገኛል- ብድሩን ወይም ብድራቱን ተከፈለ- በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም የሚባል አነጋገር ያለ ይመስለኛል። የእንግሊዝኛው ፈሊጥ ግን Poetic Justice ይለዋል) “ያርግላቸው!” አሜን ያድርግላቸው!!
ደርግ የተወነጀለበት 200ሺህ ዶላር ዛሬ አንድ ባለ ጊዜ ወያኔ ለልጁ ልደት ከሚደግሰው በታች ነው። በ1997ዓ.ም አባዱላ ገመዳ ለልጃቸው ዘኪያስ አባዱላ 24ኛ ልደት በዓል የ100ሺህ ዶላር ኮብራ ዘመናዊ መኪና በስጦታ መልክ አበርክተዋል። በ1994ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 14ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጦ ነበር። መለስ ዜናዊ ከ10 ዓመት በኋላ “በቀን ሶስት ጊዜ ትበላላችሁ” ባሉበት ዓመት መሆኑ ነው። የመለስ ዜናዊ መንግሥት ለተራቡት ወገኖች ደንታ አልነበራቸውም። በድርጅታቸው የተፈጠረው ቀውስ ላይ በማተኮርና ለእርሳቸው የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ሲሉ “ተሃድሶ” ብለው ለሰየሙት ቱማታ 280ሚሊዮን ብር ባጀት መድበው ካድሬዎቻቸውንና ተከታዮቻቸውን በድግስና በውስኪ ያምነሸንሹ ነበር። በዛው ዓመት ልጃቸው ሠማሃል መለስ የልደት በዓልዋን በግዮን ሆቴል ዳስ ተጥሎ አክብራለች። ለኬክ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ብር ነበር ወጪ የተደረገው። የመለስ ልጅ ልደትዋን በምታከብር እለት በግዮን ሆቴል ደጃፍ በርካታ በረሃብ የገረጡ ወገኖች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ወድቀው ነበር።
ስለ ድግስ ዝርዝር ለመጻፍ ፍላጐቱ የለኝም። ደግሼም አላውቅም። መንግስት ሲቀናጣ፣ እሸሸ ገዳሜው ልክ ሲያጣ፣ የሞራል ድጡ መጠነ ቢስ ሲሆን፣ ሰብአትካትን- ሰዶምና ገሞራን ወይም የጥፋት ውሃን ዘመን ሊያመለክተን ይችላል። ራስ ተፈሪዎች “ባቢሎን” ይሉታል። እንዲያውም በቀድሞው መንግስት በጠቅላይ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ሥዩም ሐረጐት The Bureaucratic Empire, Serving Emperor Haile Selassie በሚለው መጽሐፋቸው ያነሱት አንድ ነጥብ ስለድግስና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ነበር። ኮረኮረኝ። ሥዩም ሐረጐት እንደጻፉት የቀ.ኀ.ሥላሴ ባለስልጣኖች የታሰሩት ጠጅ ለመጣል ምቹ ቅዝቃዜ በነበረው ሥፍራ ነበር። ከላይ የደርግ አባላት ስብሰባ ሲካሄድ፤ ሑካታ ሲፈጠር፣ ጭብጨባ ሲበዛ ወዘተ በእሥረኞቹ ላይ ይፈጠር የነበረውን የመንፈስ ጭንቀት ይነግሩናል። አሳሪዎች የእሥረኞች ሥቃይ ሊታያቸው ከቻለ በእርግጥ “ሰው” የመባል ሙሉ ባሕርይ አላቸው ለማለት ይቻላል። (የደርጉን ዘመን ግፍ ለማውራት የምደፍርበት ወኔ የለኝም። ራሳቸውን እየቀደሱ በሌሎች ግለሰቦች ላይ ከሚደነፋፉም ጋር ጠበል የምጠጣ አይደለሁም። አንድ ነገር ላይ ከተስማማችሁልኝ ደርግ በውሃ አጥምቆ ቢሆን ወያኔ ይኸውና በእሳት እያጠመቀ ይገኛል። የጥምቀቱ ተቀባይ ደግሞ መላው ወገኔ ነው።)
የአሜሪካ መንግሥት ባለፉት ቀናት የኢትዮጵያን ድንኳን ገለጥለጥ አድርጐ የአገሪቱን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ፣ የፖለቲካ እሥረኞች አያያዝ፣ በገጠር ያለውን ብሔረሰቦችን የመከፋፈል መንግስታዊ ጫናና ወንጀል አሳውቆናል። አሳውቆልናልም። በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሰማንያ ሺህ የፖለቲካ እሥረኞች አሉ። ከእነዚህም መካከል ስድሳ ከመቶው አእምሮ እስከ መሳት መድረሳቸውን በምስክርነት አቅርቦልናል። ዝርዝሩ ብዙ ነው። ታላቅ ወንድም (የተጠጋኸው ትልቅ መንግሥት በፖለቲካው ቋንቋ ቢግ ብራዘር ይባላልና) ምናልባትም የእሥረኛውን ቁጥር ቀንሶት ይሆናል እንጂ በኢትዮጵያ እየኖረ ወያኔንና ትውልደ ወያኔ ያልሆነ ለመሆኑ ያልታሰረ – አለዚያም እሥራት የማያስጨንቀው ማነው? ብለው የሚጠይቁ የትየለሌ ናቸው። ያልታሰሩ የሚመስላቸው ሰዎች ደግሞ የጥርስ ችግር እያለው ሕመም ሳይሰማው በመጨረሻ ላይ አምስትና ስድስት ጥርሶቹ ሲረግፉለት ለቃቅሞ ወደ ሐኪም ቤት እንደሚሮጥ ሰው ናቸው።
እንደሁም ልጆቻቸው ወይም የአገር ወጣቶች በነቂስ እየታረዱ ኅዘኑ ከቤታቸው የማይገባ፣ የቤተሰብ አውራ በባለቤቱ ፊት ታስሮ ሚስት ስትነወር፣ ንብረቱ ሲድፋፋ፣ ጐታው ሲደፋ ልቅሶውና ዋይታው ከጆሮአቸው የማይደርስ ጐረቤት ወገናችን አለ። የድንጋይ ልብ የገባለት። አንዳንድ የማውቃቸው ሰዎች – ጐይትኦም ብቻ ሳይሆን- ደባልቄና አምበርብርም ጭምር – ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ሲመለሱ ተመሣሣይ ትዝታ ይዘው ይመጡላቸዋል። አዲስ አበባ ውስጥ የሚሠራው የእድገት ምልክት የሚገለጥ አይደለም። የአለቃ ደስታና የተሰማ ግጽው መዝገበ ቃላት በቂ ቃላት የላቸውም። “እንዲያውም በእንግሊዙ ንገረኝ” ትለዋለህ። አንተም አሿፊ እሱም አሹዋፊ ትባላላችሁ። ጓድ መንግሥቱ ኅይለማርያምን ብጠቅስ እንደማትቀየሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በኢትዮጵያ ራዲዮ በሠራሁባቸው ዓመታት አንድ ቀን ስለ ራዲዮ አሠራር ስንገልጽላቸው ምርር ትክን ብለው “ ዘፈኑና ጭፈራው አልበዛም ወይ? ለመሆኑ ወገኖቻችን በጠላቶቻችን ሰይፍ እየተመቱ፣ አብዮታዊ ሠራዊታችን በግራም በቀኝም – በሰሜንም በምሥራቅም፣ በመሐል አገር ደግሞ በአምስተኛ ረድፈኞች ጓዶቻችን ሁሉ እተየረሸኑ..እያለቅን አይደለም ወይ? ኢትዮጵያ ራስዋ እንደ አንድ ልቅሶ ቤት መታየት የለባትም ወይ? እንዴት ነው በዚህ ሁሉ ልቅሶኛ ላይ እሸሸ ገዳሜ ዘፈን ለማሰማት ፈቃድ የምትፈልጉት? ፈቃድ የሚጠየቅበት አይደለም። እንደየስሜታችሁ ነው። ደስ ካላችሁ ዝፈኑ። አስዘፍኑ። አለዚያም ዳኝነቱ የእናንተ ነው” ብለው ነበር። አንዱ ሲደሰት ሌላው ያዝናል። ዓለም ጉራማይሌ!
ሕይወት ከዚህ መሠረታዊ አመለካከት ይጀምራል። ግን ከአለቃችን ንግግር ውስጥ ማንንም ሊነካ የሚገባው ለአገራቸው ባበረከቱት ቅንና ሕጋዊ አገልግሎት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ወደ ወህኒ ዓለም የተወረወሩትን ሰማንያ ሺህ ኢትዮጵያውያን በዓይነ ሕሊናችሁ ጐብኙልን። አሜሪካ የምትነግረን- የማናውቅወን አይመስለኝም። ራስዋን በምስክርነት አቅርባለች። ከተጠቀምንበት። ወይም ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ አንድ ሰሞን ይሉ እንደነበረው “በደርግ ጊዜ አሜሪካ በክምር ሳር ውስጥ የወደቀች መርፌ ይታያት ነበር። አሁን ግን በእልፍኝ ውስጥ የቆመው ዝሆን እንዳይታያቸው አንድ ዓይነት ግርዶሽ (ማዮፕያ) ተፈጥሮባቸዋል” አይደለም? ጉዳዩ የኢትዮጵያውን ጉዳይ ነው ተባብለናል። የኢትዮጵያን ዋና ዋና ትግሎች (ጦርነቶች) በቅጥረኛና ካልሆነም በአሜሪካ አማካይነት የምንዋጋቸው አይደሉም። ይልቁንም ዛሬ አሜሪካ የነገረችን ሁላችንም እሥረኝነት እንዲሰማን ይመስላል። ጐበዞቻችን በወህኒ እየማቀቁ ነው።
ስለ እስክንድር፣ ስለ በቀለ፣ ስለ አንዱዓለም፣ ስለ ርእዮት….ሰምተን ነበር? ከእነሱ ሌላ ሰማንያ ሺህ ማን ያውቃል 180ሺህ ሰዎች በወህኒ ዓለም ይማቅቃሉ። ሌሎች ያልታሰሩ ግን “በመተካካት መልክ” ሊገቡ ወረፋ እየጠበቁ ናቸው። አፍጥጦ የመጣብን- እስካሁንም ያልተመለሰው ከባድ ጥያቄ- ለመሆኑ እኛስ አልሞትንም ወይ? መቸም ወደፊት እንደምንተሳሰበው ከሞቱት አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ አምሳ ሺህ ውስጥ አይደለንም ወይ? የመኖር ያለመኖር ማረጋገጫ (ምናልባት ሰርተፊኬት ወይም ሊቸንሳ) አግኝተናልን? ራስ ቢተወደድ መኮንን እንዳልካቸው “አልሞትሁም ብዬ አልዋሽም” ነበር ያሉት? ሙኩሼዬ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ቀዌሳ ደግሞ ልዑል ሐምሌት የሚያንበለብለውን ዘላለማዊ ስንኝ እንዲህ ብሎ በከፊል ወደ አማርኛ መልሶታል።
መኖር አለመኖር እዚህ ላይ ነው ምሥጢሩ
የዕድል ፈተና አለንጋ ሲወናጨፍ ወስፈንጥሩ

ይህ ዕድል ያልደረሰውና የፈተናውም አለንጋ ያልገረፈው አለ ወይ? ይለናል። ኦስካር ዋይልድ ይመስለኛል በሶሻሊዝም ሥር የሰው ነፍስ (The Soul of Man under Socialism) ድርሰቱ “መኖር እጅግ ብርቅ ከሆኑ ባሕርያት ዋነኛው ነው። ብዙ ሰዎች እንዲሁ አሉ። ግን አይኖሩም ” ያለው (To live is the rarest thing in the World. Most people exit, that is all ) ይለናል በአንክሮ። የእኔው የትግል አድባር (አያውቀኝም) ፕሮፌሰር ሐጐስ ገብረ ኢየሱስ እናቱን ለመጠየቅ ጓድ መንግሥቱ ሔሊኮፕተር አዘዙለትና ወደ አድዋ ሔዶ ነበር። ሲመለስ A Requiem of History በሚል ያቀረበውን መጣጥፍ አልረሳውም። በዚያው ሰፊ ጽሑፉ ውስጥ እንደ ፈርጥ ያየሁለት “እናቴ በእርግጥ በሕይወት አለች። እየኖረች ግን አይደለም። She was alive, but Not living.” ይላል።
በ1980ዎቹ ካነበብኋቸው መጻሕፍት መካከል በሔንሪ ኪየምባና በዴቪድ ማርቲን የተገለጡ አስደንጋጭ አጋጣሚዎች በአእምሮዬ ውስጥ የተከሉት ክፉ ትዝታ አለ። በኢዲአሚን ኡጋንዳ ጊዜ የተፈጸመ ነው። እንዲያውም የ“State of Blood” የሚለው ጸሐፊ የኡጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስተር የነበረው ሔንሪ ኪየምባ ነው። ወደ ወጉ እንመለስና ኢዲአሚን በየቀኑ ሥፍር ቁጥር የሌለው ኡጋንዳዊ የሚገድልበትና የጭፍጨፋው ወፍጮ እንበለ እረፍት የሚሠራበት ሥፍራ ነበር። በዚህ “ሥራ” ላይ የተሰማሩት ባለሙያ ነፍሰ- ገዳዮች ትንሽ ፋታ ካገኙ ወደ ሰፈር መሸታ ቤት ይሄዱና ካቲካላና ቡቅር ከሚመስለው “ነፍስን ጭምር” ከሚያስረሳው መጠጥ ይጨልጣሉ። ግድያው እንደ ጫት ሐራራ ስለሆነባቸው በማይገድሉበት ሰዓት ሁሉ ሲያፋሽጉ ይውላሉ።
አንድ ቀን ያለወትሮው ግድያው በምሽት ሰዓት ሊጠናቀቅ ስላልቻለ ዋናው ገዳይ እስረኞቹን ይሰበስብና “ዛሬ ስለመሸ ሄዳችሁ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር እደሩና ነገ በጠዋት መጥታችሁ መቃብራችሁን ቆፍራችሁ ትገደላላችሁ። አሁን ሂዱ። መልካም ዕድል” ይላቸዋል። በማግስቱ እስረኞቹ ተሽቀዳድመው በመሰለፍ መቃብራቸውን ቆፍረው በተሰጣቸው ትልልቅ መዶሻ አንዱ ሌላውን ገደለ ይባላል። ተረት ወይም የፈጠራ ድርሳን አይደለም። ዴቪድ ማርቲን በኦብዘርቨር ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ያቀርብ የነበረውን ሐተታና ከላይ በርእሱ ያመለከትሁትን የሔንሪ ኪየምባ መጽሐፍ ያነብቡአል።
ገዥዎቻች፣ አንዱን ጠባብ፣ ሌላውን ነፍጠኛ በማለት የሰየፉት ወገን ቁጥር ይታወቃል? ከምዕራብ ወደ ደቡብ፣ ከደቡብ ወደ ምዕራብ እያንከራተቱ በየኪሎ ሜትሩ የረገፈው ወገናችን ቁጥር ይታወቃል? በአኅዝ የማይገለጠው መከራውና ሰቆቃው በምን ይተመን? እዚህስ ደረጃ አልደረስንም የሚያሰኝ ምን ምልክት አለ? አሁንም ለእርድ የተዘጋጀን ነን- ሁላችንም ባንሆን አብዛኞቻችን። ንጹሐን ዜጐችን ግደሉ ብንባል ዓይናችንን የማንጨፍን አለን። አሁንም ቢሆን እኛን በእኛ እየጨረሱንም እያጫረሱንም ነው። አይደለምን? የኢዲአሚኑ ሪፖርት ይዘገንናልን?
ያንን የምታውቁትን ለፍቶ ያስተማረኝ የኢትዮጵያ ገበሬ ሲባልለት የቆየውን “ናስቲለው”…አልፎ አልፎ ታስታውሱታላችሁ? ትዝ ሲላችሁ ዓይናችሁ እንባ ይቋጥር ይሆን? (ናስቲለው በሰሜን ኢትዮጵያ ገበሬ ማለት ነው።) አሜሪካ ስለ ኢትዮጵያ ገበሬ በመንግስት መሰቃየት ያርዳን? አቦ! አቦ! እንደ ብዕርና ወረቀት ያስጠላኝ ነገር የለም። ካሣ ተሰማ ትዝ አለኝ። ድንቀኛው ጸሐፊ ጓደኛዬ ብርሃኑ ዘሪሁን ካሣ ተሰማን አንድ ቀን አነጋግሮት ነበር። ለመነን መጽሔት ነበር። ብርሃኑ ወርቅ የሆነውን የካሣን ፕሮፋይል ሲያቀርበው “ቧንቧ ሠራተኛው ካሣ” በማለት ነበር። ካሣ ክራር መደርደር የለመደው በስሜት ነው። ከተቃጠለ አንጀቱ የሚያወጣውን ትንፋሽ በዘፈን ለማብረድ ነው። ካሣ ይዘፍናል። ስሜቱ ወደ ጽርሐ-አርያል ይከንፋል። እሱም ራሱ እንደ ማኰብኰብ ሲለው ክራሩን ሰባብሮ ሲጃራ መግዣ ፍለጋ ይሄዳል።
ይኸ ሁኔታ ዛሬ ይገባኝ ጀምሮአል። ከክራሩ ባሻገር የሚሰማው ድምፅ ያለ ይመስለኛል። ከመላእክት ጋር ሲነጋገር ቆይቶስ ቢሆን? ከአድማስ ባሻገር ከታላላቆቹ ተራሮች ላይ ሆኖ ስለዚች አገር ዕድል- ስለሚደርስባት አደጋ፣ ስለ ትንንሽ ልጆችዋ መቀጨት፣ እንደ ዛሬ ስላለው የመከራ ሌሊት ያጫወቱት እንደሆነ ማን ያውቃል? እንዲያ ሆኖ ሆኖ ካሣ ወደ ቧንቧ ሥራው ይመለሳል። እሱም ዘመንን ቆጥሮ ወደ መሬቲቱ ተመለሰ። ወደ ማኅፀናዋ።
እኛንም ደካሞች ልጆችዋንም እነሱንም ባሊጊዜና ቅምጥል አዳዲስ መኳንንትና መሳፍንት የኢትዮጵያ መሬት እኩል ትበላናለች ወይ? ስለ ጄኔራል ደጐል ያነበብሁት አንድ ታሪክ አለ። ጄኔራል ደጐል ሽባ ሆና የተወለደች ልጅ ነበረቻቸው። ወላጆች እጅግ እያዘኑ ልጅቱ በመንፈስ እንድትጠነክር የማያደርጉት አልነበረም። የሚችሉትን ጥረት ሁሉ ካሙዋጠጡ በኋላ ልጅቱ ትሞታለች። እናት መሆን አይቀርምና ማዳም ደጐል ምርር ብለው ያለቅሳሉ። ያዝናሉ። እሳቸውን ማጽናናትም ከባድ ሆነ። በዚህ ጊዜ ጄኔራል ደጐል ባለቤታቸውን “እስካሁን ድረስ ምኞታችንና ጸሎታችን ሁሉ እግዚአብሔር ከሰው እኩል እንዲያደርጋት ነበር። ይኸውና በሕይወት ባይሆን በሞት ከሁሉ ጋር እኩል ሆናለችና ልቅሶሽን ተይ…” በማለት ባለቤታቸውን አጽናኑአቸው።
ኢትዮጵያውያን ሽባ ሆነን አልተፈጠርንም። ወይም አዳዲሶቹ ዲታዎች (ኖቮሪሽ) በአፋቸው ላይ የወርቅ ፍልቃቂ እየነከሱ ከማኅፀን አልወጡም። ሕዝብ የሚገዛው እንዲህ ነው ተብለው ጊንጥ የሚመስል አለንጋ የሰጣቸው አንዳች ኅይል የለም። ለምን ገዥና ተገዥ፣ ገራፊና ተገራፊ ሆነን ቀረን? አንመራመር። አስፈላጊ ወዳልሆነ እሽኰለሌም አንግባ። ይልቁን ከሞት በፊት ስላለው እኩልነት እናንሳ። በሞት ሕይወትን ስለማምጣት፣ በደምና በአጥንት ነፃነትንና እኩልነትን ስለመቀዳጀት።- ውይይይይ ለአፍ አይገድም። ትግሉን፣ መስዋዕትነቱን በወረቀት ላይ ጨረስነው አይደል? በሃያኛው ክፍለ ዘመን መነሻ የተጫነው የእኩልነት ትግል እነ W.E.B Du Bois የጀመሩት የጥቁር አሜሪካውያን ተጋድሎ ስትራተጂ የሚነደፍበትና ፕሮግራሙ በሥራ ላይ የሚውልበት ስልት የሚወጣበት ነበር። ታላቁ ዱብዋ ተፈጥሮ ለሰው ልጆች እኩል የሰጠችውን መብት ከሰው ልጆች መለመንን የመሰለ ውርደት እንደሌለ ይገልጣል። የመብትና የነፃነት ልመናን የመሰለ ወራዳ አቋም የለም። W.E.B Du Bois The Souls of Black Folk በሚል ድሮ ባሳተመው መጽሐፍ “ተነሥ! የምታጣው ሰንሰለትህን ነው” ወደሚለው የተራማጆች ፍልስፍና ያመራል። እንዲያውም ሎወልን በመጥቀስ-
Twixt old systems and the word
Truth forever on the scaffold
Wrong forever on the throne
yet that scaffold sways the future
And behind the dim Unknown
Standeth God within the shadow Keeping watch above His own
ይላል። እውነት ዘወትር በመሰቀያው ሥፍራ፣ ውሸትና የማይገባው ሁሉ ዘወትር በዙፋኑ (በአልጋው) ላይ የመገኘቱ ነገር- ያ የመሰቀያው ጣውላ የወደፊቱን ሁሉ እየነቀነቀ መገኘቱ፣ እነሆ በጭላንጭሉ መሐል ደግሞ እግዚአብሔር ከፍ ብሎ ቆሞ የራሱን ወገኖች የማበረታታቱ ጉዳይ ዘላለማዊ ነው።
ልመለስ ወደ አሜሪካ ዓመታዊ የሰብአዊ መብት መግለጫ። ከላይ ያነሳሁአቸው የዱብዋ (አሜሪካኖች ዱባይስ ይላሉ ፈረንሳዮችን ለማብሸቅ) ወይም የፍሬደሪክ ዳግላስ ታሪኮች ለእነሱ ብዙ ይጥማቸው እንደሆነ አላውቅም። በተለይ ለሪፐብሊካኖቹ። እንደዚያም ሆኖ ይህ በእነሱ ድጋፍና ርዳታ ሞልቃቃ ሆኖ የተወለደውና የሚጨፍርብን ሥርዓት (መንግሥት) ፀረ ሕዝብ፤ ፀረ አገር፣ ፀረ እንጨት፣ ፀረ ሳር፣ ፀረ ሕዝብ፣ ለመሆኑ- እደግመዋለሁ- የእነሱ እማኝነት አለን። ጊዜው- የመለያያው- ደረሰና ነው ምሥጢሩን ሁሉ ያፈነዱት? ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። እዚያ ላይ ያለውን ነጥብ የምንመለስበት ይመስለኛል። ለአሁኑ ግን አሜሪካ በአንድ በኩል ልትረዳን የምትችላቸውን ጉዳዮች ባነሳ- ከአንባብያን ድጋፍ ካገኘሁ።
አንደኛ- እስካሁን ድረስ አሜሪካ እንዲህ ያለ በሰብአዊ መብት አከባበር ረገድ የተበላሸ አቋም፣ በፖለቲካና በአገር አንድነት ጥበቃው ረገድ አሳፋሪ ሪኮርድ፣ በሕዝብ ሰላም ጥበቃና የፍትሕ መስተንግዶ መላሸቅ ረገድ ያልሆነላቸውን መንግሥታት ወይ Evil ኤምፓየር- ወይ Rogue State አለዚያም አሸባሪ (Terrorist) ሲሉ ባጅተዋል። ወያኔ ምንድነው? በእኛ ምደባ Terrorist Regime ሊባል ይገባዋልና ስያሜው በዚሁ እንዲሆን እንጠይቃለን።
ሁለተኛ፥ ይኸ ሁሉ ከተወሳና የወያኔዎች መንግሥትም ከሕዝብ የብድርና የርጥባን ገንዘብ 20 ቢሊዮንዶላርስ ጠልፎ ወደግል ሂሳብ ያዋለ እንደመሆኑ- የዋና ዋና ሌቦችን የስም ዝርዝር እናቅርብና ወደየምዕራቡ መዲና ሲገቡ እንዲያዙና እንድንፋረዳቸው።- ገንዘባቸው እንዳይንቀሳቀስ እንዲደረግ- ከምዕራባውያን የሚሰጣቸው ማናቸውም ርዳታ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲቋረጥ- ኢኮኖሚው ራሱ የተጠለፈና ወደ ግል ኩባንያነት የተዛወረ ስለሆነ የትኛውም አገር ከወያኔዎች ጋር የንግድ ልውውጥ እንዳያደርግ ዘመቻችንን እንዲቀበለን ትብብር እንጠይቃለን።- ከናይን ኢለቨን ጋር በተያያዘ አሜሪካ እንዳይደርሱ እግድ የነበረባቸው አንዳንድ ዘራፊና አቀባባይ ሌቦች እንደገና ወደ አሜሪካ ብቅ እያሉ የለመዱትን የሞራል ድቀት ትርኢታቸውን እያሳዩ ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንዱን አረብ ግለሰብ የኢትዮጵያ ትውልድ ሁሉ የሚፋረደው ስለሆነ ተይዞ እንዲመረመር እንጠይቃለን። ወርቃችን፣ ሌሎች የማዕድን ሀብቶቻችን ወዘተ በዚሁ ሰው እንደ ትንሽ ዕቃ በየቀኑ እየተጫነ እንደሚወሰድ እናውቃለን። እናስረዳለንም። …………
በ1980ዎቹ Republic of Fear በሚል ርእስ ስለ ሳዳም ሑሴን ጨለማ አገዛዝ የሚያወሳው መጽሐፍ በእጅጉ ያሸማቅቃል። ጸሐፊው ኬናን ሜኪያ ይባላል። የኢትዮጵያ የዛሬ ሁኔታ ደግሞ ሌላ ባሕርይ ያለበት ይመስለኛል። ስለ ዋናዎቹ አምባገነኖች ሲነሣ አብዛኛዎቹ ነጠላ ናቸው። በቺሊ ፒኖቼ- በሩማንያ ቻይቼስኮ፣ በኢራቅ ሳዳም ሑሴን፣ በሊቢያ ጋዳፊ…ናቸው። ለወርቅ ጥጃቸው የማይንበረከክ፣ ለምስላቸው የማይሰግድ ከሁለት ስፍራ ይከፈላል። ያማቸው፣ ስማቸውን ያጐደፈ…የሚሰቃይበት አዳዲስ መሣሪያ አስፈልፍለዋል። ዝርዝር የማሰቃያውን ስልትና ድርጅት ከማእከላዊ ምርመራ ሠራተኛነት አምልጠው የወጡ ሰዎችን ማነጋገር ይቻላል። ባይሆን አንድ ጥያቄ በአእምሮአችሁ የሚመላለስ ወገኖቼ አትታጡም። መለስ ከሞተ በኋላም ይኸ አገር በአምባገነን የሚመራ ነው ለማለት ይቻላል ወይ? በእኔ በኩል ከሰዎች ጋር ስወያይ “አምባገነኑ የማይታወቅ አምባገነን መንግሥት” A Dictatorship without a Dictator ግን አገዛዙ መንጋ ጨካኖች፣ ነፍሰ- ገዳዮችና በዝባዦች ቢኖሩትስ? የፈረንሳዩ ታላቅ ምሁር ዣን ፍራንስዋ ሬቨል Without Marx or Jesus በሚለው መጽሐፉ እንዲህ ያሉትን አምባገነኖች ባሕርይ Collective Mediocrity and Collective bestiality ይለዋል። ነገሩ እንዲህ ነው። መለስ ሲሞት የእሱ እጓለማውታ (Orphans) መፈላለግ ያዙ። ሰብሳቢ አጣን ብለው ወደ ትካዜው ዓለም ተሰደዱና መጠራራቱን አንድ መፍትሔ አደረጉት። ምንጣፉን ቶሎ ብለው የረገጡት እነ እንቶኔ ደግሞ አራት ኪሎን የተጫጫነውና አሁንም የሚገዛውን መንፈስ በፍጥነት በማናቸውም አስማት ለማስወጣት አልቻሉም። ትንሽ ፋታ ሳያስፈልጋቸው አልቀረም። ጥቂት ጊዜ ከገዙ በኋላ የፕሮፓጋንዳውም መሣሪያ ትንሽ ትንሽ ይደፍረዋል። “መለስኮ ሰው ነው” ማለት ይጀምራል። ሰው መሆኑን ዛሬ ነው ያወቁት አትበሉአቸው። እኛ መለስን ከመቃብር አውጥተን አንፋረደውም። እነሱ ራሳቸው ከሳሽም ፈራጅም ይሆናሉ። ጠብቁ ብቻ።
በደርግ ጊዜ ስለአባካኝነትና አሻጥር ትልቅ ጉባኤ ተዘርግቶ ነበር። በንቁዝ (ኮራፕት) ባለሥልጣኖችና በመሳሰሉት ላይ ጥብቅና ወሳኝ የሆነ ርምጃ ስለሚወሰድበት ሁኔታ ውይይት ሲካሄድ በየቦታው ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ አሳብ ይቀርባል። በዚያ መድረክ ላይ የአገር አስተዳደር ሚኒስትር የነበሩት ጄኔራል ታዬ ጥላሁን የተናገሩት ትዝ ይለኛል። በአጤ ምኒልክ ዘመን እቴጌ ጣይቱ “ለአገሬ ለየጁ ያለው አንድ አፈንጉሥ ብቻ ስለሆነ ሌላ እንዲጨመርለት እጠይቃለሁ” ሲሉ እቴጌይቱን በአደባባይ ተቃውመው የማያውቁት ንጉሠ ነገሥት “እንኳን ሌላ ተጨምሮበት አንዱም ቢሆን አልተቻለም” አሉ ይባላል።
በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ከመለስ ሞት በኋላ አንድ ታዋቂና በአደባባይ ስሙና ሹመቱ የተገለጠ አምባገነን ባይኖርም ሟቹ በመጠኑ ራቅ ያደረጋቸው ሰዎች አልጋው ላይ የተረባረቡ ይመስለኛል። አቦይ ስብሐት፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ዐባይ ወልዱ፣ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ወዘተ ወዘተ…በአንድ አገር የስለላው መረብ እንዳለ ወደ ፍጹማዊ ኅይል ሲለወጥ ደግሞ የዜጐች ሁሉ (መካከለኛ ደረጃ ያሉት ወያኔዎች ሳይቀሩ) መብት ወደ ኢምንትነት ይለወጣል። የሥነ መንግሥት ምሁራን በመንግሥት ውስጥ መንግሥት (ኤስቴት ዊዝን ኤ ስቴት) የሆነውን እንዲህ ያለውን ሥርዓት “መሪ” የሚባለውን ግለሰብ ጭምር ሽባ አድርጐ የሚቀፈድደው ያደርጉታል። በአሁኑ ሁኔታ ቀስ በቀስ የመለስ የቅርብ ሕዝብ አጫራሾች ዕጓለማውታ (ኦርፋንስ) ቢመስሉም ሌሎች በርካታ አምባገነኖች ጡንቻቸውን እያፈረጠሙ ናቸው። ወትሮ አንድ አምባገነን ያልቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የብዙ አምባገነኖች ተሸካሚ ሆኖዋል። ሁሉም ነፍሰ ገዳዮች! ነፍሰ ገዳይ የማይፈራስ ማነው?
ለጊዜው በመንጋ ተንኮለኞች- ነፍሰ ገዳዮችና የዝርፊያ ሠራዊት እየተገዛን እንገኛለን። ስለእነሱ ድግስ፣ ስለ እነሱ ጥቅም፣ እነሱ የትኛዋን ጋለሞታ እንደሚጐበኙ፣ የትኛዋን መለኮን ዛሬ እንደወሰዱ እንወያያለን። በጥቃቅን ጉዳዮች አእምሮአችንን አስጨንቀናል። ወጣጥረነዋል። ይልቁን በሌላው ዓለም እየተቀጠቀጠ ማረፊያ ያጣው መንግሥታዊ አሸባሪነት የሙጥኝ ብሎ የሚገኘው በኢትዮጵያ መሆኑን እንተባበር። ይህን የሽብር መንግሥት ሌላው ቀርቶ በብረት መሞከርን ካህናቱና መነኮሳቱም መደገፍ አለባቸው። ከቶውንም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሺስቶች ጥይት ሊደበደቡ ጥቂት ሰከንዶች ሲቀራቸው “ልጆቼ ኢትዮጵያውያን ለፋሺስቶች እንዳትገዙ አውግዤአለሁ” ማለታቸው ይጠቀሳል። አዳዲስ ካሕናትና የዚህ ትውልድ ቀሳውስት ነገሩን ቸል እንኳ ቢሉ የአቡነ ጴጥሮስ ግዝትና ውግዘት አለብን። ቋሚ ነው- እስከማዕዜኑ።
ትግልና ታጋይ የሚጠይቁት አንድ ነገር ብቻ ነው። በደረትህ ውስጥ ጤነኛ ልብ፣ በጭንቅላትህ ውስጥ ጤናማ አእምሮ ካለህ ማናቸውም ችግር አይፈታህም። ጥይት አይመታህም። ድንፋታ ትርጉም አይሰጥህም። ቅጥፈትና ማስፈራራት ትጥቅህን አያስፈታህም። ልጆቼ ልላቸው የምችለው እነ እስክንድር፣ በቀለ፣ አንዱአለምና ርእዮት ይህን ወኔ በሰፊው የተቀዳጁ ናቸውና እንኮራባቸዋለን። እነሱ ወኅኒ ዓለም ሲገቡ የከዳናቸውና የቆሙለትን ዓላማ ጭምር የረሳንባቸው ከመሰላቸው ደግሞ አደራ በላነት ሊሰማን ይገባል።
ይህን ጽሑፍ የጀመርሁት በወያኔ የልደት በዓል ምክንያት ትንሽ የምለውን ለማቃመስ ነበር። ምናልባትም እንደ ፍሬደሪክ ዳግላስ ለእነዚህ ሰዎች “ጉንበት 20- ጉንበት ሃያ ትሉናላችሁ ጉንበት ሃያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥቃይ ሁሉ እናት የሆነችው ስቃይ የመጣችበት ቀን። ጉንበት 20 የባርነትና ወደር የሌለው ውርደት መታሰቢያ ቀናችን ናት። ጉንበት 20 ለእሥራታችን መታሰቢያችን ናት።” ልንላቸው እንችላለን። ይኸ የደፋሮቹ ጋዜጠኞች – የጀግኖቹ የፖለቲካ መሪዎችና ገበሬዎች የተባበረ ድምጽ ነው። በሬሳችን ላይ የሚጨፍሩበት፣ በመቃብራችን ላይ የሚያሽካኩበት፣ ቤትና ንብረት አሳጥተው ለስደት ያበቁንና በዚህ ደስታ የሚሰክሩበት በዓላቸው- የእኛ የልቅሶ ዕለት፣ የእኛ የመከራ ቀን መታሰቢያ ነው።
በመጨረሻም እንደገና ለአሜሪካ በማቀርበው ጥያቄ ላይ ይህችን ነጥብ እደግማለሁ። ይህ መንግስት ኢቭል የምትሉት አይነት ነው? ወይስ አሸባሪ? የወያኔ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች ላይ የሚፈጽሙትን እልቂት፣ የወያኔ አማራዎች (እነበረከት አምሮች ከተባሉ) በኢትዮጵያውያን አማሮች ላይ የሚያካሄዱትን መጠነ ሰፊ ድምሰሳ፣ የወያኔ ሙስሊሞች በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እያደረሱ የሚገኙትን ወከባና ወደር የሌለው ጥቃት፣ ሟቹ የመለስ የሃይማኖት የይስሙላ ፓትርያርክና እንደ ሩሲያዊው ራስፑቲን የሚቆጠረው አባ ጳውሎስ በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያካሄደውን ሥቃይ አሜሪካ ከእኛ በላይ እንደማያውቀው ለዴሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብትና ነፃነት ስትል ርምጃ ለመውሰድ አቅዳለች? አጤ ኅይለሥላሴ በቀድሞው የመንግሥታት ማኅበር ጉባኤ ላይ ያደረጉትን ንግግር ለመጥቀስ እገደዳለሁ – “ታሪክና ትውልድ ፍርዳችሁን ይጠባበቃሉ!”
እነሆ ዛሬ በኢትዮጵያ የሰው ዘር ጠላት የሆነ ሥርዓት አለ። የሒትለርን ፀረ ሕዝብነት ለመረዳት የፖላንድ መወረር፣ የሃምሳ ሚሊዮን ሕዝብ ማለቅ፣ የስድስት ሚሊዮን አይሁድ መጨፍጨፍ መጠበቅ ይገባል? ታሪክ አላስተማራችሁምን? በአሜሪካ ላይ ስንት ክህደትና ቸልታ እንቁጠር? በፋሺስት ወረራ ዘመን ሩዝቬልትና ሴክሬተሪ ሐል ያሳዩን ክሕደትና ቸልታ አይረሳንም። አሜሪካ የበለጠ ትናገር! እግዚአብሔር ሁላችሁንም ይጠብቃችሁ!!

Link:- http://ecadforum.com/Amharic/archives/11399/
Posted by:- Bethel Solomon