ሰማያዊ ፓርቲ “ሊታረድ ነው”
* ሕዝብ ዋስትናና መተማመን አጥቷል
ረቡዕ ዕለት ኢህአዴግ በጠራው ሰልፍ ዜጎች ስሜታቸውን ሲያንጸባርቁ የተሰጣቸው ምላሽ ሽብርን በአሸባሪነት አመጣጥኖ የመመለስ አይነት እንደሆነ ተጠቆመ፡፡ የሰላማዊ ሰልፉ አጠቃላይ ገጽታና የሕዝብ ስሜት በአገሪቱ የዋስትና ማጣት ስሜት እየገዘፈ መሄዱን የሚያሳይ ሆኗል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ሊታረድ ነው፤ በሰሜን አሜሪካ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ባሉት ይልቃል ላይ እዚያው እንዲቀሩ ተጽዕኖ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በአይሲስ የታረዱትና የተረሸኑትን “ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እያጣራሁ ነኝ” ሲል የነበረው ኢህአዴግ እንዴት እንዳጣራ ለሕዝብ ባያሳውቅም ወዲያው ሕዝባዊ ለመሆን በመመኘት በአገሪቷ ላይ የሐዘን ቀን ከማወጅ በተጨማሪ ሕዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጣ ጥሪ አድርጎ ነበር፡፡ አንድ የጎልጉል አስተያየት ሰጪ “ሕዝቡ ለ24 ዓመታት በሐዘን ላይ ነው ሦስት ቀንማ ምን አላት” በማለት እንደተሳለቁት የተሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ ሕዝቡ ገና ከጠዋቱ ጀምሮ ተንቀሳቅሷል፡፡ በየቦታው የኢህአዴግ ካድሬዎችና ፖሊሶች መሰለፍ የሚገባውን ከማይገባው ለመለየት ሙከራ ቢያደርጉም በእጅጉም አልተሳካላቸውም፡፡
ይህንን ሰላማዊ ሰልፍ ከሕዝቡ በተጨማሪ ኢህአዴግ የደፈነባቸውን የፖለቲካ ምህዳር በራሳቸው እያሰፉ የሚንቀሳቀሱት ጥቂት የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ድጋፍ ሰጥተውታል፡፡ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን እንደሚያከብሩ ድጋፍም እንደሚሰጡ በይፋ ባወጡት መግለጫዎች አስታውቀው ነበር፡፡ ይህም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚደረገውን ሽብር የሚቃወሙ መሆናቸውን ለሚያሸብራቸው ኢህአዴግ በአገራዊ አጀንዳ ላይ አብረው እንደሚቆሙ ኅብረት ያሳዩበት እንደሆነ በብዙዎች ተስተውሏል፡፡
ይሁን እንጂ ሰልፉ ኢህአዴግ ቀደም ሲል በቀላጤው ሬድዋን አማካኝነት የሞቱት “ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው” ዕውቅና ነፍጎ በሰጠው መግለጫ የተቆጣው ሕዝብ የሰልፉን ዓላማ ኢህአዴግ ከተመኘውና ከፈለገው ውጪ አድርጎታል፡፡
ከለቅሶ ቤት ጀምሮ “መንግሥትን አንፈልግም” በማለት ቁጣ የተሰነዘረ ሲሆን አብዛኞች ግን “መንግሥት የለንም” ሲሉ ድርብ ሃዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
ገዳዩ ባለካራው አሸባሪ ድርጅት ለፈጸመው ወንጀል ይሉኝታ ሳይዘው እንደ ታላቅ ገድል በቪዲዮ አስደግፎ ሲያቅራራ ዓለም ምስሉን ባደባባይ አይቷል፡፡ ሚዲያዎችም ተቀባብለውታል፤ መንግሥት ነን ብለው የተቀመጡት እነሬድዋን እንደ አንድ ሰው ሚዲያዎችን ተከታትለው መረጃውን አግኝተውታል፡፡
በኢህአዴግ ቋንቋ “ህገወጥ” የሚባሉት ሥራ ፈላጊዎች ድንበር አቋርጠው ሲወጡ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ የላቸውም፡፡ ኢህአዴግ በሊቢያ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የለውም፡፡ አፈቀላጤውና “የፌስቡኩ ሚ/ር” ዶሮ እንኳን የሞተች ሳይመስላቸው “እውነት ኢትዮጵያውያን ሞተው እንደሆነ እናጣራለን” በማለት የተናገሩት ከካራም በላይ የሕዝብን ስሜት ያረደ ስለመሆኑ አብዛኞች ይስማማሉ፡፡ የረቡዕ ተቃውሞና ቁጣም ብዙ የተከማቹ መነሻዎች ቢኖሩትም አስኳሉ ጉዳይ ግን ክህደቱ እንደሆነ ይታመናል፡፡
“ያገር አንበሳ የውጭ ሬሳ”፣
“እግዚአብሔር ነው ለእኛ ኃይላችን አንመካም በጉልበታችን”፣
“ደማችን ይመለስ፣ ይታፈስ”፣
“አቤት ቆሻሻ”፣
“አይሲስ በካራ እናንተ በዱላ”፣
“አትመጣም ወይ መንጌ አትመጣም ወይ”፣ …
የሚሉ መፈክሮችን በኢህአዴግ ቁልፍ የአስተዳደር ቦታዎች አጠገብ ሰልፈኞች ሲልፉ ማሰማታቸውና በተለይ “ደማችን ይታፈስ” ሲሉ የጮኹት ዛሬ የተወለደ መፈክር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ስለ አሸባሪ ከመስማታቸው ውጪ አሸባሪ መሆኑ በታወቀ ድርጅት ኢትዮጵያ ጥቃት ደርሶባት አያውቅም፡፡ ዊኪሊክስ ምስጋና ይድረሰውና ማን አሸባሪ እንደሆነ፣ ማን እንደሚያፈነዳ፣ ማን አንደሚያስፈነዳ፣ ማን ቀጣሪ እንደሆነ፣ በግልጽ ታክሲ ውስጥ ማን ቦምብ እንደሚያፈነዳ በግልጽና ማስተባበያ ሊቀርብበት በማይችልበት መልኩ አስቀምጦታል፡፡ ሐቁ ይህ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ካዝናው በጎደለ ቁጥር ኢትዮጵውያንን እየማገደ ከአሸባሪዎች ጋር የገባው እሰጥ አገባ የሰላማዊ ነዋሪዎችን የዋስትና ስሜት ከድህነቱ ጋር አብሮ ሰልቦታል፡፡
ሚያዚያ 26፤ 2006ዓም (ሜይ 4፤ 2014) አንድነት በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ “ለሥራ ብለን አባል አንሆንም” እያሉ ያዜሙት ሰላማዊ ሰልፈኞች በገሃድ እንዳስታወቁት የስደቱ ምንጭ ድህነት ነው፡፡ ጥቂቶች ሲበሉ አብዛኞች የገንዳ ውስጥ ትራፊ እንኳን ስላረረባቸው ነው፡፡ መረራ ጉዲና እንዳሉት “የራበው ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል” ነውና ነገሩ ይህ ሕዝብ ወደ በቀል ከመሄዱ በፊት ቢሳደብ በምን መስፈርት ጥፋተኛ ይባላል? አረመኔያዊ በሆነ ስሜት ሊቀጠቀጥና አስፋልት ላይ እንዲጎተት ይፈረድበታል? ስለምንስ በጅምላ ይታሰራል? እንዲህ ያለው ሽብርን ባሸባሪነት የመቃወም ስሜት ቁጣውን ያበርደዋል ወይስ ይጨምረዋል? ሕዝብ ስሜቱን እንዲገልጽ ተጋብዞ የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ መቀጥቀጥና መጨፍጨፍ ካራን በዱላ የመቀየርና አይሲስ የሚለውን ስም ኢህአዴግ በሚለው ለውጦ ሕዝብን ከማሸበር በምን ይተናነሳል? ሕዝብን ለተቃውሞ ውጡ ብሎ ጋብዞ በጭስ እያፈኑ እንደ እባብ መቀጥቀጥ የቦታ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር አዲስ አበባ ላይ የተቀጠቀጠው ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ሊቢያ ከታሰሩትና ከታገቱት በምን ይለያል?
ሁልጊዜ እንደሚባለው የማስተዋልና የሕዝብን ስሜት ጠብቆ የመጓዝ ነገር ለእኛ አገር እርም ሆኗል፡፡ ከዛሬ 24ዓመት ጀምሮ የሕዝብን ብሔራዊ ስሜት፣ ብሔራዊ ኩራት፣ ብሔራዊ ማንነት፣ የእምነት መከባበር፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ቀስ በቀስ ሥሩን እየበጣጠሰ በቂምና በቁርሾ በመተካት እዚህ ያደረሰን ኢህአዴግ ትላንትና የተመሠረተውን የሰማያዊ ፓርቲ ለዚህ ዓመጽ ተጠያቂ ማድረጉ ከፌዝ በላይ ፌዝ መሆኑን አብዛኛዎች ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችን ቅርጫ ሲያደርገው እንደጸና የቀረውን የሰማያዊ ፓርቲን ኢህአዴግ ሊያርደው ቢላውን ስሎ መጨረሱን በቀላጤው አማካኝነት ይፋ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፓርቲው መሪ በሰሜን አሜሪካ በሥራ ጉብኝት ላይ በሚገኙት ይልቃል ጌትነት ላይ ተጽዕኖ በማድረስ እዚያው እንዲቀሩ የማድረጉን ሥራ ኢህአዴግ ከወዲሁ መጀመሪ ጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኢህአዴግ ተቀናቃኞቹን ከፊቱ በማራቅ የተካነ እንደመሆኑ እምቢ ያሉትን እስር ሲወረውር ሌሎችን አስፈራርቶ ወይም አበስ አድርጎ አገር ለቅቀው በመሄድ ከፊቱ እንዲርቁ ሲያደርግ የኖረበት አሠራር ነው፡፡
መቼ እንደሚባረሩና ከኢህአዴግ ጋር ያላቸው የሥራ ጊዜ እስከ መቼ እንደሚዘልቅ ያላወቁት አቶ ሬድዋን ሰማያዊ ፓርቲን የማረዱን ሥራ አረጋግጠዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚያወጣ የሚጠበቅ ቢሆንም የአፈቀላጤ ሬድዋን ዛቻ “በሉ ተብለው” የታዘዙበት እንደሆነ ግን ግልጽ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.