July 29, 2015
ይገረም አለሙ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ምኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት በሰላማዊ ምርጫ የተመረጠ ብለዋል በሚል ከተለያየ አቅጣጫ ተቃውሞና ነቀፌታ እየተሰነዘረባቸው ነው፡፡ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ባደረጉት ንግግር ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ ተካሂዷል ይህ ማለት ግን ዴሞክራሲያዊ ነው ማለት አንዳልሆነ ከአቶ ኃይለማሪያም ጋር መነጋገራቸውን ስም ጠቅሰው ተናግረዋል፡ ምርጫ ግዜ እየጠበቁ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ነጻና ፍትሀዊ መሆን አንዳለበትም አስረግጠው ገልጸዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረቱ ንግግራቸው እስካሁን ተቃውሞ አልተሰማበትም፡፡
የዚህች ጽሁፍ አላማ ኦባማ ስለተናገሩት ማውሳት አይደለም፤በተለይ ሀገር ቤት ያሉ ተቀዋሚዎች ሰላማዊ ምርጫ የሚለውን አገላለጽ ሲቃወሙ አንድም ትናንትን የረሱ ሁለትም በሚቃወሙት ድርጊት ውስጥ የእነርሱ ድርሻ መኖሩን ያልተገነዘቡ ሆኖ ስለተሰማኝ ይህን ለማመለከት ነው፡፡ ትናንትን መርሳትና ራስን ነጻ አድርጎ ሌላውን መውቀስና መኮነን ስር የሰደደ ችግራችን ነው፡፡ ከዚህ መላቀቅ ካልቻልን ደግሞ ለውጥ ናፋቂ ሆነን መኖራችን አይቀሬ ነው፡፡
ወያኔ የምርጫ 97 ሽንፈቱን የቀለበሰው በጠመንጃው ብቻ ነው ብለን እናምን ይሆናል፤ነገር ግን አይደለም፤ ቅድመ ምርጫም ሆነ ድህረ ምርጫ የአሜሪካ ረዥም እጅ ነበረበት፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቅንጅት ስልጣን ቢይዝ በወያኔ የምታገኘው ጥቅም መቀጠሉ ለአሜሪካ አጠራጣሪ ነበርና ነው፡፡አሜሪካ በግልጽ የማይታወቁ ብዙ ነገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ አሏት፡፡ የአርባ ምንጩን የሰው አልባ አውሮፕላን ጣቢያ አንድ አሳ ጎርጓሪ ጋዜጠኛ እስከሚያጋልጠው ድረስ ማን ያውቅ ነበር?
ስለሆነም ለጥቅሟ መቀጠል የወያኔ በሥልጣን መቆየት አስፈላጊ ነበርና ቅንጅት እንዳያሸንፍ ብቻ አይደለም ከዛ በኋላ አንደ ፓርቲ አንዳይቀጥል የማድረጉ ስራ የተሴረው በወያኔ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል፡፡ከእስር የተረፉት አዲስ ቅንጅት የሚባል ፓርቲ እንዲመሰርቱ፤የአዲስ አበባን መስተዳድር እንዲረከቡ ፤ፓርላማ አንዲገቡ ወዘተ በአሜሪካ ኤምባሲ በኩል የተሰራውን ሁሉ መርሳት ለተዳጋጋሚ ሽንፈትና ስህተት ይዳርጋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም እየተወገዘም ማእቀብ እየተጣለበትም ወያኔ በሥልጣኑ አንዲቆይ አሜሪካ በግልጽም በስውርም ብዙ ሰርታለች፡፡
የመድረኩ አመራር ፕ/ር መረራ ጉዲና አንደ ፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያነታቸው ከዚህም አልፈው ማወቅና መተንበይ ሲገባቸው ርሳቸው ግን በምርጫ 2007 ዋዜማ ኢህአዴግ ሁለት ምርኩዞቹን (ምርጫ ቦርድንና ጠመንጃን) ከጣለ አያሸንፍም ነበር የሉት፤ የአሜሪካ ምርኩዝነት አልታያቸውም፡፡ትናንትን መርሳት ይህ ነው፡፡
አሜሪካ በምርጫ 2007 ሶስት ነገር ትሻ አንደነበር ለማወቅ ጠንቋይ ቀላቢ መሆን አይጠይቅም፡፡አንድ የወያኔን አሸናፊነት፤ሁለት በምርጫው ዋዜማ መባቻም ሆነ ማግስት ምንም ኮሽታ እንዳይኖር(ምርጫ 97 የሆነው እነርሱንም ያባንናል)ሶስት ተቀዋሚዎች ትንሽ ወንበር አግኝተው ዴሞክራሲያዊ እንዲመስል፡፡ የወያኔን በስልጣን መቆየት የምትሻው አሜሪካ እንደ 97 አይነት የተቃውሞ እንቅስቃሴና የግድያ ርምጃ አንዳይኖር ትፈልግ ነበርና ተቀዋሚዎችን እየሰለለችና የልብ ምታቸውን እያዳመጠች ወያኔንም እየመከረችና እያስጠነቀቀች ሂደቱን በቅርብ ትከታተል ነበር፡፡ ለዚህም ነው ወያኔ በምርጫው ዋዜማ ሰላማዊ ምርጫ የሚል ነጠላ ዜማ ለቆ ጠዋት ማታ ሲያደነቁረን የነበረው፡፡ በመጨረሻም ከአሜሪካ ፍላጎት ሁለቱ ተሳካ፡፡ ወያኔ አሸነፈ ውጤት ተገለጸ ኮሽ ያለ ነገር አልነበረም እናም ፈጥና ሰላማዊ ምርጫ በማለት መግለጫ ሰጠች፡፡ልብ በሉ ዴሞክራሲያዊ አላለችም፡፡ ይህን ካረሳን በስተቀር ኦባማ የደገሙት ይህንኑ ነው፡፡
ወያኔ በምርጫ 2007 ሁለት ነገሮችን ማለትም ሙሉ ለሙሉ ለማሸነፍና ምንም አይነት ጫጫታም ሆነ ኮሽታ አንዳይኖር ለማድረግ መስራት የጀመረው በምርጫ 2002 ማግስት ነው፡፡ በአንጻራዊ መልኩ የተሻሉ የሚባሉትን ፓርቲዎች በሙሉ በጸረ ህገ መንግሥትነት የወነጀለው ወያኔ በምርጫው ማግስት አዲስ ራዕይ በተሰኘው ልሳኑ ላይ አቶ መለስ እንደጻፉት በሚገመት ጽሁፍ :# ጸረ ሕገ መንግሥታዊ አቋማቸውን እስካልቀየሩ ድረስ መብታቸውን በጥብቅ አክብረን በማያቋርጥ ዴሞክራሲያዊ ትግል አሁን ከደረሱበት ደረጃ እንዳያልፉና እንዳያንሰራሩም በርትተን መስራት ይጠበቅብናል፡፡”በማለት ነበር የገለጸው፡፡ ከዛን ግዜ ጀምሮ ጉልበት ከሥርአት እየተጠቀመ የወሰዳቸው ርምጃዎች ሁሉ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ነበር፤ አሳካ፡፡
ተቀዋሚዎችስ ፤ተቃዋሚዎች ቢያንስ ሶስት ነገር ይጠበቅባቸው ነበር፡ አንድ፣ምርጫው ሌላው ቢቀር በኢትዮጵያ ደረጃ ነጻና ፍትሀዊ የሚመስል እንዲሆን የሚያስችሉ ነገሮች እንዲኖሩ መታገል፤ ሁለት ለማሸነፍ የሚያስችል ብቃት መፍጠር፤ሶስት ምርጫው ቢጭበረበር ለመቃወም መዘጋጀት፡፤ ነገር ግን አንዱም አልታየባቸውም፡፡
ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኛ አይደለም፤የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል፤ነጻነት ለፍትሀዊ ምርጫ ወዘተ እያሉ እነዚህ በሌሉበት ወደ ምርጫ ገቡ፡፡አባሎቻችን እጩዎቻችን ታዛቢዎቻችን ማስፈራሪያ ደረሰባቸው ተንገላቱ ታሰሩ፤ያቀረብናቸውን እጩዎች ቦርዱ አልመዘግብ አሉን ወዘተ እያሉ ጠቧል ያሉት ምህዳር ጨርሶ መቸንከሩን፤ለፍትሀዊ ምርጫ ያሉት ነጻነት ለመኖርም መታጣቱን፤ ገለልተኛ አይደለም ያሉት ምርጫ ቦርድ ለይቶለት ወያኔ መሆኑን ወዘተ እየነገሩን በምርጫው ቀጠሉ፡፡
ዛሬ የባራክ ኦባማን ንግግር ከተቃወሙት አንዱ የመድረኩ ፕ/ር መረራ በምርጫው ዋዜማ ወያኔ ሁለቱን ምርኮዞች ከጣለ አያሸንፍም ሲሉ አልጣለምና አይሸነፍም ማለታቸው ነበርና ይህ እየታወቀ በምርጫው መቀጠል ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ማንሳት አግባብነት አለው፡፡ ምክንያቱም ምርጫው ሰላማዊ እንዲባል ካበቁት ምክንያቶች አንዱና ዋናው ተቀዋሚዎቹ በአጃቢነት አብረው መዝለቃቸው ነውና፡፡
ሁለተኛው የኦባማን ንግግር የተቃወሙት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ናቸው፤ፓርቲው ነጻነት ለፍትሀዊ ምርጫ የሚል ዘመቻ ጀምሮ እንደነበረ ይታወቃል፡ ታዲያ በምርጫው የቀጠለው ለነጻ ምርጫ የሚያበቃ ነጻነት መኖሩን አረጋግጦ ነው ወይ ብለን እንዳንጠይቅ በወቅቱ ይሰጡ የነበሩ መግለጫዎች የሚያሳዩት ምርጫው ሲቃረብ ቀደሞ የነበረው ውስን ነጻነት ሁሉ እንደታጣ ነው፡፡ 400 እጩ አቅርበን ምርጫ ቦርድ የመዘገበልን 200 ብቻ ነው ሲባልም ሰምተናል፡፡ የእጩዎቻቸው ቁጥር በምርጫ ቦርድ ይሁንታ እስከመወሰን ከደረሰ ከዛ በኋላ የፓርቲው በምርጫው መቀጠል ያስገኘው ፋይዳ ካለ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጠናቀቀ መባልን ነው፡፡
ተቀዋሚ ፓርቲዎች ኡ ኡ እያሉ፤አባሎቻቸው እየታሰሩና እየተገደሉ በምርጫው እስከ መጨረሻው መዝለቃቸው፤ ከዛም በኋላ መቶ መቶ በመቶ የወያኔን አሸናፊነት ያረጋግጠ ውጤት ሲገለጽ ተቃውሞ ላማሳየት አለመመኮራቸው (ለዚህ ዝግጅት ስላልነበራቸው) ምርጫውን ሰላማዊ አሰኝቶታል፡፡ ስለሆነም ወያኔ መቶ በመቶ ያሸነፈበት ምርጫ ሰላማዊ እንዲባል ያበቁት እነርሱም ናቸውና መስተዋቱን ወደ ራሳቸው ማዞር ይገባቸዋል፡፡ሌላ ሌላውን ማድረግ ባይቻል ከምርጫ ራስን ማግለል የሚገድ አልነበረም፡፡እስቲ ይታያችሁ አንድነት ፈርሷል፣መኢአድ ተተራምሷል፣ በዚህ ሁኔታ ሰማያዊና መድረክ ከምርጫ ቢወጡ ኖሮ ያ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ የተካሄደ ሊባል ይበቃ ነበር! አይመስለኝም፡፡ እናንተው አጅባችሁ በሰላም ለድል አብቅታችሁ አሁን ሰላማዊ ምርጫ ሲባል መቃወም አያምርባችሁም፡፡ያለፈው አልፏል ለነገው ተማሩ፤ትናንትን አትርሱ የራሳችሁንም ተጠያቂነት አታለባብሱ፡፡ይሄ ሲሆን ነው ማደግ የሚቻለው፡፡
No comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.