Saturday, August 8, 2015

የአስመራ ሰዎች በአዲስ አበባ – (ዜና ትንታኔ)

ቻላቸው ታደሰ ለዋዜማ ራድዮ እንደዘገበው: 

ኤርትራ በ1990 ዓ.ም ኢትዮጵያን በወረረች ማግስት መንግስት በረፊረንደሙ የተሳተፉና ለብሄራዊ ደህንነት አደገኛ ናቸው ያላቸውን በሽዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን በጅምላ ከሀገር ማባረሩ ይታወሳል፡፡ ሰዎቹ ሲባረሩ ያፈሩት ሃብትና ንብረት በአግባቡ ሳያደላድሉና በህጋዊ መንገድ ለተወካዮቻቸው ሳያስተላልፉ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ይህ የግብር ይውጣ እርምጃ ብዙ ዓለም ዓቀፍ ወቀሳም አስከትሎ ነበር፡፡ 

የሁለቱ ሀገሮች የድንበር ጦርነት ምንጭ ሳይደርቅና ዕርቀ ሰላምም ሳይወርድ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ከአምስት ዓመት በፊት ባወጣው ደንብ በወረራው ወቅት የተባረሩ ኤርትራዊያን እንደገና በኢትዮጵያ ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ እንዲያገኙ፣ የቀድሞ ንብረታቸው ከፈለጉም ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው እንዲመለስላቸው ብሎም ከሀገሬው ሰው እኩል ንብረት ማፍራት እንዲችሉ ፈቅዷል፡፡ መታወቂያና የእርሻ ቦታም ሳይቀር ተስጥቷቸው ከሀገሬው ሰው ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ በባንክም ተቀማጭ የነበረ ገንዘባቸውም ተመልሶላቸው እንደማንኛውም የውጭ ዜጋ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ፣ የማህበራዊ ግልጋሎቶችን ደግሞ ከዜጎች ጋር በእኩል እንዲያገኙ አድረጓል፡፡ ስለሆነም የዚህ ፖሊሲ መነሻና ግብ ምንድን ነው? ፖሊሲውስ በኢኮኖሚ በተዳከመችውና ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጡንቻዋ በተመናመነባት ኤርትራ ላይ ምን ዓይነት የፖለቲካ፣ ፀጥታና ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች ይኖረው ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች መመርመር ተገቢ ነው፡፡ 

በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራዊያኑ ስደተኞች ላይ ፖሊሲውን ማስተካከል ያስፈለገው የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦችን ለማቀራረብና ግንኙነታቸውንም ለማደስ አስቦ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲ ከሰብዓዊነትና ወንድማማችነት መርሆዎች ባሻገር ሌላ ዓላማ እንዳለው መታዘብ አይከብድም፡፡ 

መንግስት ለበርካታ ኤርትራዊያን ስደተኛ ወጣቶችም የከፍተኛ ትምህርት ስኮላርሽፕ በመስጠት በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ተመዝግበው በነፃ እንዲማሩ እያደረገ ነው፡፡ የተማሪዎቹን ጉዳይ ምፀታዊ የሚያደርገው ግን ከጦርነቱ መቀስቀስ በፊትም በርካታ ኤርትራዊያን በሀገራችን ነፃ ትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው ይማሩ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ መንግስትም ከዜጎቹ በላይ ለኤርትራዊያኑ ተማሪዎቹ ደህንነትና ምቾት አብዝቶ ይጨነቅ እንደነበር የዚህ ሪፖርት አዘጋጅ ሳይቀር በኣካል ያየው ሃቅ ነበር፡፡ ሆኖም ተማሪዎቹ በወረራው ማግስት ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ከሀገር ከመባረር አልዳኑም፡፡ 


ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ በጅምላ መሰደዳቸው የኢትዮጵያን መንግስት ያስደሰተ ይመስላል፡፡ መጠኑ ይለያያል እንጂ መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ ቱርክ በሶሪያዊያን ስደተኞች ላይ ከምትከተለው ጋር ይመሳሰላል፡፡ የኤርትራው መንግስትም ጅምላ ስደቱ ሀገሪቱን በሰው ሃይሏ በተለይም በወጣቶች የማራቆት (emptying the nation) ፀረ-ኤርትራ ሴራ መሆኑን ይናገራል፡፡ በእርግጥም ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በርካታ ኤርትራዊያን ከሀገር ተሰደዋል፡፡ መንግሰት የሚተገብረው ፖሊሲም ስደተኞችን በጣም ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በየቀኑ ከ70 ያለነሱ ስደተኞች ድንበሩን እያቋረጡ ይገባሉ፡፡ ሀገራችንም በአሁኑ ጊዜ ከ93 ሽህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞችን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ከሶሪያዊያን ቀጥለው በአውሮፓ በብዛት ሁለተኛዎቹ ኤርትራዊያን ስደተኞች እንደሆኑም የዓለም ዓቀፍ ስደተኞች ድርጅት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲ ግቦች የኤርትራን ወታደራዊ አቅም ማዳከም፣ ከውጭ የሚገባው የገንዘብ መጠን በዜጎች ስደት ሳቢያ እንዲመናመን ማድረግ፣ ኢኮኖሚዋም እንዲዳከምና ውስጣዊ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ማድረግ እንደሆነ ይገመታል፡፡ 

ይህ የተናጥል ፖሊሲ ግን ምን ያህል ውጤታማና አዋጭ ነው? በኤርትራ ላይስ ምን ዓይነት ተጨባጭ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የፀጥታና ማህበራዊ አንድምታዎች ይኖሩት ይሆን? የሚሉት ጥያቄዎች መነሳት ያለባቸው ናቸው፡፡ በንብረት ጉዳይ ላይ ተወሰነው ውሳኔ ሀገራችንን ብዙ ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀርም፡፡

 ለዚህም ተጠያቂ የሚሆነው የቀድሞው የመንግስት ዝርክርክና የተቻኮለ አሰራር ይሆናል፡፡ ፖሊሲው ወደፊት የሚያመጣው የደህንነት ስጋት ካለም ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ መንግስት ግን ወደ መሃል ሀገር የሚገቡት ኤርትራዊያንና የደንቡ ተጠቃሚ የሚሆኑት የደህንነት ስጋት የማይፈጥሩ መሆናቸው ተረጋግጦ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሆኖም ግን በሚስጥራዊነቷና በመገለሏ “አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ” በምትባለው ኤርትራ ውስጥ ሃቁን በምን መልኩ እያጣራው እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች ነው፡፡ 

ስደቱ የኤርትራን መንግስት ፖለቲካዊ ዋጋ ቢያስከፍለውም የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲ ግን ምን ያህል የኤርትራዊያንን ልብ ማሸፈት ይችላል የሚለው ወደፊት የሚታይ ቢሆንም ከድሮም እጁ አመድ አፋሽ የሆነው መንግስት ወጥነትና ግልፅነት ከጎደለው ፖሊሲው እምብዛም ትርፍ ያገኛል ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው፡፡

 ከኤርትራ በኩል ሲታይ ደግሞ በእርግጥ በርካታ ዜጎች በፈለሱ ቁጥር ከውጭ በሪሚታንስ (remittance) መልክ የሚገባው የገንዘብ መጠንም መቀነሱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ በውጭ ምንዛሬ ላይ ለሚተማመነው መንግስት የራስ ምታት ይሆንበታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ለዚህ ነው ባላንጣውን በቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት ከመምታት ይልቅ በኢኮኖሚ ማዳከም የመረጠው፡፡ የኤርትራ መንግስት በገጠመው የምንዛሬ እጥረት ምክንያት ካናዳና እንግሊዝን ጨምሮ በተለያዩ ሀገሮች የሚገኙ ኤርትራዊያን የሁለት በመቶ አስገዳጅ ህገ ወጥ “ዲያስፖራ ታክስ” (diaspora tax) እንዲከፍሉ በማድረጉ ከመንግስታቶቹ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ መግባቱ በተደጋጋሚ በሜዲያ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ስለሆነም አሁን በኢትዮጵያ የሚኖሩ ስደተኞችም በውድም በግድም የዚሁ ግዴታ ሰለባ ላለመሆናቸው ዋስትና የለም፡፡

 ሀገሪቱ ከህዝብ ብዛቷ አንፃር ሲታይ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝቧን ያስታጠቀችና ወታደራዊ ስልጠና የሰጠች (militarised state) እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ቀደም ብሎ ስለ ግዙፍነቱ ይነገርለት ከነበረው የኤርትራ ጦር ሃይልም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ወታደሮች እየከዱ ወደ ኢትዮጵያና ሱዳን መሻገራቸው በእርግጥም የሀገሪቱን ወታደራዊ አቅም ከማዳከምም አልፎ ደህንነቷንም አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ 

በዚህም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ከሶስት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ድንበር ዘለል ወታደራዊ ጥቃት ሲፈፀምበት ጦር ሰራዊቷ ምላሽ መስጠት ያልቻለው፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታም ከኢትዮጵያ ጋር ፊት ለፊት ጦርነት የመግጠም እድሉ አናሳ ነው፡፡ የመንግስት ፖሊሲ ከሀገር የሚሸሹትን ባሉበት እንዲገደሉ የሚያዝ ቢሆንም የጦር ሰራዊቱ አመራሮች ግን በሰው በሽዎች የሚቆጠር ናቅፋ እየተቀበሉ ስደተኞችን ወደ ጎረቤት ሃገር በማሻገሩ ወንጀል እንደተዘፈቁ ዓለም ዓቀፉ የግጭት ጥናት ተቋም (International Crisis Group) ይገልፃል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውሎ አድሮ ጦር ሰራዊቱም ሞራሉ እየላሸቀ ስለሚሄድ በጣሙን የመዳከም አደጋ አንዣቦበታል ማለት ይቻላል፡፡ 

አዲስ አበባ ያሉት የአቶ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ተቃዋሚዎች ትጥቅ ትግል ስለማያደርጉ ኤርትራዊያን ስደተኞቹን የማደራጀትና የመመልመል ስራ አይሰሩም፡፡ በእርግጥ ኤርትራ የኢትዮጵያን መንግስት በነፍጥ የሚፋለሙ ሓይሎችን ብትደግፍም ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ግን ተመሳሳይ ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡ መንግስት ይህንን የማያደርገው ግን በኤርትራ ላይ ከሚከተለው ዋናው ፖሊሲ ጋር የሚጋጭበት ስለሆነ አይደለም፡፡ ምን ያህሎቹ ኤርትራዊያን ስደተኞች መንግስታቸው በሃይል እንዲወገድ ይፈልጋሉ? የሚለው ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኤርትራ መንግስት በሃይል ቢገረሰስ ሀገሪቱን ሊረከብ የሚችል አስተማማኝ አማራጭ ሃይል እንደሌለም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ 

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ኤርትራዊያን በመንግስታቸው ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ከማድረጋቸው ውጭ ኤርትራዊያን ስደተኞች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተባበረ መንገድ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለማጋለጥ ሲጥሩ አይታዩም፡፡ ምናልባት ሀገር ውስጥ ላሉ ቤተሰቦቻቸው ደህንነት ስለሚሰጉ ይሆናል፡፡ በጦር ሰራዊቱ ውስጥም ቢሆን ከሶስት ዓመታት በፊት አስመራ ላይ ከታየው የጥቂት ወታደሮች የአጭር ጊዜ መጠነኛ አመፅጥ (mutiny) በስተቀር ምንም የአመፅ እንቅስቃሴ አይስተዋልም፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ ያገኘው ፖለቲካዊ ድል የለም ማለት ይቻላል፡፡ 

ኤርትራዊያን በብዛት የሚገኙባቸው አፍሪካዊያን ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን እያቋረጡ በብዛት ወደ በአውሮፓ ከመግባታቸው ጋር በተያያዘ ኤርትራ በቅርቡ መልካም ዜና ሰምታለች፡፡ የአውሮፓ ህብረት የኤርትራ መንግስት ፍልሰቱን እንዲቀንስ 313 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ እርዳታ ሊለግስ ቃል ገብቷል፡፡ በእርግጥ የህብረቱ ውሳኔ ተግባራዊ ከሆነ በኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲ ላይ በረዶ የሚቸልስ ይሆናል፡፡ በአንፃሩ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ለሚሰቃየው የኤርትራ መንግስት ደግሞ ከሰማይ የወረደ መና እንደሚሆንለት አይካድም፡፡ የኤርትራ መንግስትና ሰራዊት ዋነኛ ኢኮኖሚያዊ ዋልታ የሆነውን የማዕድን ዘርፍ ሊያነቃቃው እንደሚችል ታዛቢዎች ይገምታሉ፡፡ ይህ ተግባራዊ ከሆነ በሂደትም በመንግስቱ ላይ የተጣሉ አንዳንድ ማዕቀቦች ሊነሱም ይችላሉ፡፡ ይህንን ሚስጢራዊ የተባለ ስምምነት ለመተግበርም የተለያዩ የህብረቱ ባለስልጣናት ኤርትራን ሲጎበኙ ሰንብተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ አውሮፓ ህብረት የስደቱ ዋነኛ መንስዔ ኢኮኖሚያዊ ነው ብሎ ማመኑን ያሳያል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎም እንግሊዝ ለኤርትራዊያን ስደተኞች ጥገኝነት መስጠት የቀነሰች ሲሆን ህገወጥ ኤርትራዊያን ስደተኞችንም ከሃገሯ ለማስወጣት በመዛት ላይ ስለመሆኗ የእንግሊዙ “ዘ ጋርዲያን” ጋዜጣ በቅርቡ ዘግቦ ነበር፡፡ የህብረቱ ውሳኔ ግን ከተባበሩት መንግስታትና ዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል፡፡ በሀገሪቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር መካድ ባይቻልም ስደቱ በመብት ጥሰት ሳቢያ የመጣ መሆኑን ዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይገልፃሉ፡፡ በቅርቡም የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚቴ የኤርትራን መንግስት በአስከፊ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክፉኛ መከስሱ ይታወሳል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው በጥቅሉ ሲታይ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲ በኢሳያስ መንግስት ላይ ጠንካራ ፖለቲካዊ ንቃቃትን መፍጠር አልቻለም፡፡ ታዛቢዎችም በኤርትራ በኩል ተመሳሳይ አወንታዊ እርመጃ ሳይኖር የኢትዮጵያ መንግስት የተናጥል እርምጃ መውሰዱ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም አያስጠብቅም በማለት ይተቻሉ፡፡ አሁንም ቢሆን ስደተኞችን መንከባከብ ተገቢ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግስት አካሄድ በድምሩ ሲታይ ግን ከወረራው በፊት የነበረውን ሁኔታ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ የሚፈልግ አስመስሎበታል፡፡ በእርግጥም የፖሊሲው ዓላማ በህዝቦች ወንድማማችነት ሽፋን በኤርትራው መንግስት ላይ የበቀል እርምጃ መውስድ ዋነኛ ታሳቢው ያደረገ ነው ማለት ይቻላል፡፡

 - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45694#sthash.tniSikWX.dpuf

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.