ኀዳር ፭(አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዘንድሮ የሚጠናቀቀው የኢህአዴግ የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን የተለጠጠ ዕቅድ በግብርና ዘርፍ መዳከም ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን ኢህአዴግ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ አመነ፡፡
ኢህአዴግ «አዲስ ራዕይ» በተሰኘው በርዕዮተ ዓለም ልሳኑ የመስከረም- ጥቅምት 2007 ዓ.ም ዕትም ላይ የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአራት ዓመታት አፈጻጸም አስመልክቶ ባሰፈረው ሐተታ እንደጠቆመው ለጥጦ የያዘውን ዕቅድ ማሳካት እንዳልቻለ በማስቀመጥ አባላትና ደጋፊዎቹን አጽናንቷል፡፡
ግንባሩ ባለፉት አራት ዓመታት በግብርና ፣በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ዘርፎች አመርቂ ውጤት መገኘቱን በደፈናው ካስቀመጠ በሃላ ግንባሩ የተለጠጡ ዕቅዶችን አንግቦ የተነሳና ለማሳካትም ወቅቱ የፈቀደውን ያህል የተንቀሳቀሰ
ቢሆንም ከሞላ ጎደል መሠረታዊውን የዕድገት ምጣኔ እንጂ በተለጠጠ አኳሃን የነደፈውን ግብ ማሳካት ሳይችል መቅረቱን አምኗል፡፡ «በራሳችን ተነሳሽነት ለጥጠን ያስቀመጥነው ግብ ላይ ባለመድረሳችን ዛሬም የምንቆጭና ለነገ በእልህና በላቀ ወኔ መነሳሳት እንዳለብን የምንገነዘብ ቢሆንም በአራቱ ዓመታት በርብርብ የተመዘገበው ውጤት የሚያኮራ ነው» ሲል ይጠቅሳል፡፡