ትናንት ሲያቀብጠኝ ከአንድ ጓደኛየ ሞባይል እነዚያ አይሲስ የሚባሉ ጉግማንጉጎች እነዚያን 21 ክርስቲያን የግብፅ ዜጎች በሊቢያ አንድ የባሕር ዳርቻ ላይ አንገታቸውን ሲቀሉ የሚያሣይ ቪዲዮ አየሁ – እስከመጨረሻው መዝለቅ አልቻልኩምና ግን ዋናው ባራኪ በግራ እጁ የያዘውን ጩቤ ወደ እኛ ወደተመልካቾቹ ዘርግቶ እያስፈራራ ሲዝት አጠፋሁት፡፡
የሰው ልጅ በሰው ልጅ ላይ እስከዚህ መጨከኑ የሚያመላክተን ዋና ቁም ነገር የዚች ምድር ሰዎች የደረስንበት አጠቃላይ መንፈሣዊና ኅሊናዊ ኪሣራ ሊቀለበስ ወደማይችል ከፍተኛ የመጨረሻ ደረጃ መድረሱን ነው፡፡ ለምግብነት የተፈቀዱልንን እንስሳት እንኳን ስናርድ የሚዘገንነንና በዚህም ምክንያት የማናርድ ብዙ እንስፍስፍ ሰዎች አለን፡፡ ሰውን የሚያህል ክቡር ፍጡር ሊያውም በሚከተለው ሃይማኖት ምክንያት ብቻ በስለት አንገቱን ቀንጥሰው ጀርባው ላይ ሲያስቀምጡ ሊሰቀጥጣቸው ይቅርና በደስታ የሚፈነጥዙ “ሰዎች”ን በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስናይ በሰዎች ተፈጥሮ መለያየት እጅግ እንገረማለን፡፡
“A Message Signed with Blood, to the Nation of the Cross” ይላል የቪዲዮው መግቢያ፡፡ አስፈሪ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በያዙት የመስፋፋት ሂደት ከቀጠሉ ሌሎቻችንም ይህ አስቀያሚ ዕጣ የሚቀርልን አይመስለኝም፡፡ ነገሩ “የፋሲካው በግ በገናው በግ ይስቃል” እንዳይሆን ያሰጋል – እየሆነም ነው እንጂ፤ ከመካከለኛው ምሥራቅ የተነሣ እሳት አፍሪካ ጫፍ ሊቢያና የመን ሲደርስ አያድርስ ብሎ ከመጸለይ ውጪ እኛስ ምን ዋስትና አለን? ይህን ቪዲዮ ከተመለከትኩ በኋላ ለረጂም ጊዜ ሥራየን በአግባቡ መሥራት አልቻልኩም፡፡ ሰው ሆኖ የመፈጠር ዕዳ የቀሰቀሰብኝ የተስፋ መቁረጥ ስሜት መላ ሰውነቴን ወረረው – በአካልም፣ በመንፈስም፣ በኅሊናም እየኮሰመንኩ ስሄድ በምናቤ ይታየኝ ጀመር፡፡ አለመፈጠሬን የመረጥኩበት አንዱና ትልቁ አጋጣሚ ይህን ዘግናኝ ቪዲዮ በከፊልም ቢሆን ያየሁ ጊዜ ነው፡፡
ይህ በአስቀያሚነቱ ወደር የማይገኝለት ዓለም አቀፍ ክስተት በረድ እያለልኝ ሲመጣ ግን የሀገራችን አይሲስ ነጋዴዎች ታወሱኝና ስለነሱ አብዝቼ መጨነቅን ያዝኩ፤ ሁለቱ ተመሳሰሉብኝ፡፡ ደረጃውና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ጭካኔ ሁሉ መጠሪያውም ሆነ ጎራው ያው ጭካኔ ነው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያጵያውያን ኢይሲሶች የምላቸው በወያኔ የተፈጠሩ የዘመናችን ኅሊና ቢስ ነጋዴዎችንና ኑሯችንን ያመሰቃቀሉትን የሙስና አበጋዞችን ነው፡፡ ከወያኔ ቀጥለው የሀገራችንን የቀብር ሥነ ሥርዓት እያፋጠኑ የሚገኙት እነዚህ የቀን ጅቦች ናቸው፡፡
ወያኔ የዘራው ትልቁና መሠረታዊው ችግር የሀገር ብሔራዊ ስሜትን ማጥፋቱ ነው፡፡ ከዚህ በተያያዘም ሰብዓዊነትን ከሀገር አጥፍቷል፡፡ በምትኩ የተስፋፋው ዘረኝነት በወንዝ ልጅነትና በጎጥ፣ በቋንቋና በቤተሰብ መሳሳብ የጥቅም ትስስርን አንግሦ ጥቂቶች በሀብትና በሥልጣን ሽቅብ ሲመነደጉ አብዛኛው ሕዝብ እንጦርጦስ እየወረደ ነው፡፡ ወያኔ ዘረኝነትን በማስፋፋት ብቻ አልተወሰነም፡፡ ለሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳነት እንደ አያያዥ ስሚንቶ ይቆጠሩ የነበሩ ሃይማኖትን፣ ባህልን፣ የሞራል ዕሤቶችን፣ መተሳሰብን፣ መፈቃቀርን፣ መቻቻልን፣ አብሮ መብላት መጠጣትን፣ … በጥቅሉ አንድን ሰው ሰው ሊያስብሉት የሚችሉ ሰብኣዊና ተፈጥሯዊ ክሮችን በጣጥሶ አንድያውን ሁላችንንም እንደራሱ ዐውሬ እያደረገን ነው፡፡ ከዚህ በሀገር ደረጃ ከታወጀብን የጥፋት ውርጅብኝ ለማምለጥ የምንውተረተር ዜጎች በጣም ጥቂቶች ነን፡፡ ዛሬ የብዙ ሰው መፈክር “ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ” ሆኗል፡፡ አንድ ማስታወቂያ ነበር – “መጀመሪያ ራስህን አድን ለጫማው በኋላ ይታሰብበታል” የሚል፡፡ እኛም “‹ሀ› ራስህን አድን” በሚለው የራስ ወዳድነት መርህ እየተመራን አንዳችን አንዳችንን በልተን ልንጨረስ የቀረን ጊዜ ኢምንት ነው፡፡ በጩቤ አለመተራረድ ብቻውን ከአይሲስነት ተፈጥሮ ነፃ አያወጣም፡፡ “እሳት ካየው ምን ለየው” ነውና በምንም ይሁን በምን የዘመናችን የጭካኔ መገለጫ አይሲስ ሆኗልና ነጋዴዎቻችንና ጃዝ ባዮቻቸውም የንግዱ ዘርፍ አይሲስ ናቸው – ሥውር አራጆች፡፡
ኑሮ በአዲስ አበባ ምን ይመስላል? ሰዎች ለምንና በምን ብልሃት፣ እንዴትስ ብለው በሀብት ይከብራሉ? ብዙኃኑስ ለምን በሀብት ይደኸያሉ? የሀገራችን የሀብት ክፍፍል ምን ይመስላል?አብሮ መኖር ሲቻል መጠፋፋትን ምን አመጣው?
በአሁኑ ወቅት “ሀገራችን ወዴት እያመራች ነው?” ብሎ መጠየቅ ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ ይልቁንስ “በጉዞዋ የት ደርሳለች? በብርሃን ፍጥነት እያስነካችው ያለችውን ጉዞ ጨርሳ ወያኔና ታሪካዊ ጠላቶቿ ወዳቀዱላት የመጨረሻ ግብ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ ይቀራታል?” ብሎ መጠየቅ ይመስለኛል አግባብ የሚሆነው፡፡ እንጂ ዕድሜ ለወያኔ ካሣለፍነው የሃያ አራት ዓመታት የጥፋት ጉዞ በመነሣት ወዴት እያመራን እንደሆነ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ጉልህ ክስተት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ስል በመላዋ ኢትዮጵያ እንደማለትም ቢቆጠርልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ለውጥ ሊኖር ቢችልም እንኳን ያን ያህል የጎላ አይደለምና፡፡ እናም በሀገራችን ኑሮ በአሁኑ ወቅት እጅግ የሚሰቀጥጥ መሆኑን በመጠኑ እንመልከት፡፡
በደመወዝ ብቻ መኖር ከቀረ ብዙ ጊዜ አለፈን፡፡ ደመወዝ ስልህ ደግሞ ይግባህ – የመንግሥትንና በሲፒኤ ደንብ የሚተዳደሩትን ማለቴ ነው፡፡ ትላልቅ ደመወዞችን አይመለከትም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከፈላቸው አሉና እነሱ የኑሮ ግርፋና ሰቆቃው አይነካቸውም፡፡