‹‹በማላውቀው ምክንያት ፓስፖርቴን ተነጥቄ ጉዞዬ ተስተጓጉሏል›› ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር


በአሜሪካ ከሚገኙ የሰማያዊና የአንድነት ለፍሕትና ለዴሞክራሲ (አንድነት) ፓርቲ አባላት ጋር በተለያዩ ስቴቶች ለመወያየት ወደዚያ ለማቅናት ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ያመሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ባላወቁት ምክንያት ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ጉዟአቸው እንደስተጓጎለ ገለጹ፡፡ 
መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ወደ አሜሪካ ለመብረር ሁሉን ነገር አሟልተው ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸውን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ የአውሮፕላን መሳፈሪያ ሰዓት እስከሚደርስ ሊሸኟቸው አብረዋቸው ከነበሩ ጓደኞቻችው ጋር ሲጨዋወቱ አምሽተው ወደ ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
 የመጨረሻውን ፍተሻ አልፈው ወደ አውሮፕላን መግቢያ በር ለማምራት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ፍተሻ ጋ ሲደርሱ ፓስፖርታቸውን ሰጥተው የይለፍ ማረጋገጫ ለማግኘት እየተጠባበቁ ሳሉ የኦፕሬሺን ሠራተኛዋ ‹‹ከዚህ ቀደም ሌላ ፓስፖርት ነበረዎት?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበችላቸው ገልጸዋል፡፡ እንደነበራቸውና ከዚህ በፊትም ወደ አሜሪካ ለመሄድ እዚያው ፍተሻ ላይ ሲደርሱ ‹‹ከፓስፖርትዎት መካከል አንድ ገጽ ጎድሏል፤›› ተብለው መመለሳቸውን እንደነገሯት አክለዋል፡፡ ለ20 ደቂቃ ያህል በኢንተርኔት ላይ አንዳንድ ነገሮችን ስታነብ የነበረችው ሠራተኛዋ፣ ‹‹አለቆቼን ላነጋግር›› ብላቸው ወደ ቢሮ መግባቷንና ወዲያው በፍጥነት ተመልሳ ሥራዋን በመቀጠል ‹‹ይጠብቁ እያዩት ነው›› እንዳለቻቸውና ለ50 ደቂቃዎች ያህል መጠበቃቸውን ኢንጂነር ይልቃል ገልጸዋል፡፡