Sunday, August 24, 2014

መነሻ ገጽ - ዜና - በቅርስነት የተመዘገበ ሕንፃ በልማት ምክንያት እንዲፈርስ መታዘዙ ተቃውሞ አስነሳ

በቅርስነት የተመዘገበ ሕንፃ በልማት ምክንያት እንዲፈርስ መታዘዙ ተቃውሞ አስነሳ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘውንና በቅርስነት የተመዘገበውን ታዋቂው ሎምባርዲያ ሬስቶራንት ያለበትን ሕንፃ ጨምሮ፣ በ10.6 ሔክታር ላይ የሚገኙ ግንባታዎችን ለማፍረስ ለተነሺዎች የመጨረሻ
ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያው ባለፈው ዓርብ አብቅቷል፡፡ በተለይ የሕንፃው ባለቤት የሆነው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲና የሕንፃው ተከራዮች የአስተዳደሩን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡ 
ተቃውሞ አቅራቢዎቹ ሕንፃው በቅርስነት የተመዘገበ ሆኖ ሳለ እንዲፈርስ መወሰኑ አግባብ አይደለም እያሉ ነው፡፡ 
ሕንፃው በ1921 ዓ.ም. የተገነባ ሲሆን፣ ሕንፃውን የገነቡት የመናዊው ታዋቂ ነጋዴ ሼክ አህመድ ሳላህ አልዛህሪ ናቸው፡፡ ሕንፃው ከ85 ዓመታት በላይ ከማስቆጠሩም በተጨማሪ የሥነ ሕንፃ ቦርድ በቅርስነት አስመዝግቦታል፡፡ 
የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት በጻፈው ደብዳቤ፣ በተመሳሳይ በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የሼክ አህመድ ሳላህ ቤት በአዲሱ ማስተር ፕላን ላይ በቅርስነት እንዲመዘገብ መደረጉን አስታውቋል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪም የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሕንፃው በቅርስነት ስለመያዙ፣ እንዲሁም የሚመለከተው አካል ለቅርሱ ጥበቃ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ 
ነገር ግን የልደታ ክፍለ ከተማ፣ የከተማ ማደስና መሬት ባንክ ጽሕፈት ቤት ለዚህ ማሳሰቢያ ትኩረት እንዳልሰጠ ታውቋል፡፡ 
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ለምለም ገብረ ሚካኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕንፃው ቅርስ መባሉ አያሳምንም፡፡ ይልቁኑም በአካባቢው በሚካሄደው መልሶ ማልማት ከ40 እና ከ50 ፎቅ በላይ ከፍታ ያላቸው ሕንፃዎች ስለሚገነቡ መፍረሱ አግባብ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ግንባታዎች በማዕከላዊው የከተማው ክፍል ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች እንዲገነቡ በተያዘው ዕቅድ መሠረት የሚካሄዱ ናቸው፤›› ሲሉም አቶ ለምለም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚያካሂደው መልሶ ማልማት ከብዙ ቅርሶች መፍረስ በኋላ፣ ልማቱ ቅርሶችን ታሳቢ ባደረገ መንገድ እንዲከናወን በቅርቡ መመርያ ማስተላለፉ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን አሁንም የሚካሄዱ ልማቶች መንግሥት በቅርስነት ላስመዘገባቸው ግንባታዎች ትኩረት ገና አልሰጠም ሲሉ በርካታ ባለሙያዎች ይተቻሉ፡፡

Saturday, August 23, 2014

የውሸት አባት 2ኛ ሙት ዓመት

ግንቦት 20፣ 1983ዓም መለስ ወይም ለገሠ ወይም አስረስ ወይም ዜናዊ ወይም … ትክክለኛ ስሙን በውል የማናውቀው ከነጭፍሮቹ ቤተመንግሥት ገብቶ ራሱን አጼያዊ ፕሬዚዳንት፣ ቀጥሎም አጼያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ … በማድረግ ከሾመበት ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኦፊሴል እንደ ሻማ ወይም እንደ ኩራዝ ተለኩሷል።
አቀጣጣዮቹ ምስለኔዎች ከሻማና ከኩራዝ ከፍ ብለው ብርጭቆ የለበሱ ፋኖሶች ሆነዋል። ለመለስና ለጭፍሮቹ የሚያበሩ ፋኖሶቹም (ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ …)፣ ኩራዞቹም፣ ሻማዎቹም የበራላቸው ማሾዎች (ህወሃቶች) ሁሉም በአንድነት ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ለኳሹም ተለኳሹም እያበሩ የአስለኳሹን ሁለተኛ ሙት ዓመት “እያከበሩ” ነው። በሌላ አነጋገር ለሙት መንፈስ እሣት አንድደው እየሰገዱ ነው። ተገድዶ እየነደደ ያለውን ሕዝብ፣ አዳዲሶቹ አስለኳሾች (የኃይለማርያም ደቦ አስተዳደር) ሕዝብን ሻማ ላደረገውና ከስሙ ጀምሮ በውል ማንነቱ ላልታወቀው ግለሰብ “ሻማ አብሩ” አሉለት።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለሁለተኛው ሙት ዓመት “የውርስ መታሰቢያነት” ከዚህ በታች ያለውን የመክብብ ማሞን ጽሑፍ ሲያቀርብ በመለስ ሞት ላዘኑ ሁሉ ለሃዘናቸው መጉመጥመጫ እንዲሆን በማሰብ ነው። “የውሸት አባት” መለስ ነፍስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ስዩመ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አጼ አድርጎ ራሱን በመሰየም ሕዝብን እንደሻማ ባነደደበት ዘመናት ከአንደበቱ ሲወጡ የተመዘገቡ ውሸቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም።
በተለይ ግን በ1997ቱ ምርጫ ሰሞን ሕዝብ እንደ ሻማ ከመቃጠልና ከመንደድ የራሱን መሪ እንዳይመርጥ የዋሸው ውሸት ከዚህ በታች ሰፍሯል። ታዲያ ሕዝብ እንደ ሻማ ከመቅለጥ የሚያድነውን እንዳይመርጥ ለገደበ ግለሰብ እንዴት ሻማ ይበራለታል?!
“ማሾዎቹ” ደረት ቢደቁ፣ ከበሮ ቢደልቁ፣ ፈንዲሻ ቢበትኑ፣ አሸንዳ ቢዘሉ፣ ሠርግና ምላሽ ቢያደርጉ፣ “አንጓይ ፍስስ” ቢሉ፣ … ምክንያት አላቸው። እንደ ዱር አውሬ “የአገር ቅርስ” ሲሉት ውለው ቢያድሩ ከልካይ ሊኖራቸው አይችልም። በሚሊዮን ሕዝብ ችግር ላይ ቆመው ለሙት መንፈስ ቢንደባለሉ ደንታ የላቸውም። ሚሊዮኖች በሚያዝኑበት አገር፣ እስር ቤትና ማጎሪያዎች ውሥጥ የታፈኑት ሲቃ በሚያሰሙበት አገር እነርሱ ሙት ዓመትን አስረሽ ምቺው ቢያደርጉት ማን ተዉ ሊላቸው ይችላል?! ምክንያቱም ብርሃን ይፈልጋሉ፤ ለዚያ ደግሞ ነዶ የማያልቅ ሻማ ያስፈልጋል።
ለማንኛውም መጪው የምርጫ ጊዜ ነውና የወደፊቱን ውሸት ከዚህ በታች በሰፈረው የመክብብ ማሞ ጦማር እያጣቀሳችሁ የ… ዜናዊን ሙት ዓመት አክብሩ። ለኢትዮጵያ እውነተኛ ስም ያለውና ለዘመናት በዚያው ስሙ የሚጠራ መሪ ይስጣት።