Tuesday, June 18, 2013

ጥቂት ስለ ኢትዮጵያ እስር ቤቶች

በአለማየሁ ጥበቡ
 ክፍል አንድ
 በምንም ተከሰስ ከመታሰር አትድንም ፡፡ ህግና ህገመንግስት በወረቀት ላይ ቢኖርም በትክክል አይሰራበትም ላም አለኝ
በሰማይ ልትለው ትችላለህ ፈፅሞ እንዳታስብ ሰባዊ መብት ምን እንደሆን እዚህ ምድር ላይ አይታወቅም ፡፡በየጉራንጉሩ
ያሉ እስርቤት ሳይሆኑ መታጎርያ ቤቶች ቁጥራቸው ሀገሪቱ ላይ ካሉ ሆስፒታሎችና መስርያ ቤቶች ይበልጣሉ፡፡ በነዚህ
መታጎርያ ቤቶች ታስሮ ምንም ሳይሆን ከነጤናው የወጣ ሰው በጣም እድለኛ ምናልባትም የፈጣሪ ሸሪክ ነው ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ እስር ቤቶች በሁለት ይከፈላሉ እነሱም ፡-
1...ፈዴራል መንግስት ስር ያሉ እስር ቤቶች 1.
- ቃሊቲ ማረምያ ቤት
- ዝዋይ ማረምያ ቤት
-ሸዋ ሮቢት ማረምያ ቤት
- ድሬደዋ ማረምያ ቤት
2... በክልል መንግስት ስር ያሉ ቁጥራቸው የትየለሌ የሆኑ እስር ቤቶች ናቸው 2.
አዲስ አበባ ላይ ወንጀል የሰራም ያልሰራም ቢሆን ብቻ የመታሰር እጣ የወጣበት ሰው እንደወንጀሉ የሚታሰርበት ቦታ
ይለያያል ከዚህ በታች ያሉት እስር ቤቶች ጊዛዊ እስር ቤቶች ናቸው ፡፡ከፍተኛው ፍርድ ቤት /ልደታ ያለው ከፍተኛ ችሎት /
እስክትቀርብ ድረስ ጊዛዊ ምርመራ የሚደረግባቸው ናቸው
/ ሀ ፤ለ እና ሐ በደንብ ተመልከት/
ሀ.... ለምሳሌ ጫማ ሲሰርቅ የተያዘ ሰው /የአንድ እግር ጫማም ሊሆን ይችላል/ የሚታሰረው በየቀበሌው ባለ እስር ቤት ነው ፡
፡ቀላል ወንጀሎች ስርቆት፤ስድድቦሽ ፤ወዘተ እንደወንጀላቸው መጠን በየወረዳው ባሉ ዳኞች ይዳኛሉ ፡፡ ዋስ ቶሎ ያገኛሉ
ይገባሉ ይወጣሉ ይህ አይነቱ ወንጀል እና ወንጀለኛ መንግስትን ፈፅሞ አሳስቦት አያቅም ፡፡
ለ.... ወንጀሉ ከበድ ያለነው ከተባለ ለምሳሌ ሰው መግደል ፤ከባባድ ስርቆቶች ፤አስገድዶ መድፈር፤ በቼክ ሰውን ማጭበርበር ፤
ከባባድ ማታለሎች ወዘተ የመሰሉት ወንጀሎች ላይ የተሰማራ ሰው የሚታሰረው ሶስተኛ የሚባለው እስርቤት ነው ይህ እስር
ቤት ግማሽ አካሉን ለማእከላዊ ሰጥቶ ፕያሳ ምድር ላይ የሚገኝ ዘግናኝ እና አስፈሪ እስር ቤት ነው ፡፡ ያረከውንም
ያላረከውንም በዱላ ብዛት የምታምነበት ቤት ይሄ ነው፡፡ በቀላል በበሩ ትገባለህ መውጫዋን ግን አታቀውም፡፡ በትንሹ
ምርመራ ላይ እስከ ስድስት ወር ልትቆይ ትችላለህ፡፡ለይስሙላ ፍርድ ቤት ይወስዱሀል ያመጡሀል ምክንያቱም ህገ
መንግስቱ ላይ
አንቀጽ 19 /የተያዙ ሰዎች መብት/
ቁጥር 3 ‹‹የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰአት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው ፡፡››
ይላል ስለዚህ ትሄዳለህ መርማሪው ምርመራዬን አለጨረስኩም ተጨማሪ ቀን ይሰጠኝ ይላል ዳኛውም የተቀመጠው ለዚሁ
ነው ተጨማሪ ቀን በደንብ ይሰጠዋል፡፡በደንብ ትታሻለህ መረጃው ሲደልብ ከፍተኛ ፍርድቤት ፋይልህ ይላካል አቃቢ ህግ
ጥሩ አንቀፅ ከፍቶ ዳኛ ፊት ያቀርብሀል፡፡ በስድስት ወር ምርመራ ምንም ካላገኙብህ በነፃና ካሳ ሰጥተው አይሸኙህም እንዲህ ካደረጉማ ኢትዮጵያም ትከስራለች ሀገሪቷ ላይም ህግ የለም ይባላል ስለዚህ በመታወቅያ ዋስ ይፈቱሀሀል ይህ ማለት ምን
ማለት ነው እስከግዜው ተፈተሃል ማለት ነው፡፡
ሐ.. . . ሌላኛው እስር ቤት ማዕከላዊ የሚባለው ነው
ከመንግስት ጋር ተቃርነሃል? የሀገርን ጥቅም እነሱ እንደሚሉት ለሌላ ሀገር አጋልጠሀል ?ፖለቲከኛነት ተጠናውቶሀል ? እቺን
የጥጋብና የፈንጠዝያ ሀገር ደሃ ናት ብለሃል? የዜጎች መብት አለተከበረም ብለሀል ? የመናገር መብቴ ይከበርልኝ ብለሀል?
ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመሀል ?
በነፃ ፕሬስ አለ ባይነት መንግስትን ወይ ባለስልጣኑን ተችተሀል? እነዚህንና የነዚህን ተዛማች ተግባሮችን ካረክ የትም
አትታሰርም እድሜ ለማዕከላዊ እስር ቤት ፡፡ ምርመራህ እስኪያልቅና ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እስትቀርብ ጥፍርህ
ይነቀላል ብልትህ ይመግላል አካልህ በዱላ ብዛት ይበጣጠሳል ቶርች ትገለበጣለህ ይሄ ሁሉ እናት ሀገርህ ምድር ላይ ነው
የሚሆነው ያውም ባንተው ዜጎች ፡፡
በ ሀእና ለ /የ ሐ አላቅም/ እስር ቤቶች ካቦዎች አሉ /እስረኛን የሚያስተዳድሩ እስረኞች / እንደገባህ ያስቀምጡህ እና በምን
እንደታሰርክ ይጠይቁህ እና አይዞህ ብለው የቤት መዋጮ ስጥ ይሉሀል ካለህ እስከ ሶስት መቶም ልትሰጥ ትችላለህ ይሄ ብር
ልቃ አጣቢዎች ለቤት አፅጂዎች ለሽንት ደፊ ቅጥረኛ እስረኞች የሚሰጥ ነው ይልሀል ካቦው ፡፡ ሽንት ዲፋዎች ማለት
እስረኞቹ ለሊት በትልቅ ባሊ ሲሸኑ ያደሩትን ሽንት መደፋ ማለትነው ለዚህም አገልግሎቱ ይከፈለዋል፡፡ ካቦው ሲጠይቅህ
ገንዘብ ከሌለህና ጠያቂህ ሲመጣ ተቀብለህ የማትሰጥ ከሆነ እስረኛው የበላበትን እቃ ታጥባለህ ሽንት ትደፋለህ ቤት
ታፀዳለህ ይሄን እናዳታደርግ ከ 50 ብር ጀምሮ ለካቦው ስጠው ፡፡ካቦው ተሰሚነት አለው፡፡ከሱ ጋር መጣላት የለብህም፡፡
እንግዲህ ከሶስቱም እስር ቤቶች ማለትም ከ ሀ፤ለ እና ሐ ግዚያዊ እስር ቤቶች ምርመራህን ጨርሰህ ወደ ከፍተኛ ፍርድ
ቤት ከቀረብክ በኃላ በዛኑ ቀን አልያም በማግስቱ ወደ ቃሊቲ ማረምያ ቤት ትላካለህ እድለኛ ከሆንክ ፤ገንዘብ ካለህ ፤ ጥሩ
ዘመድ ካለህ ምንም ወንጀል ስራ ‹‹ ገንዘብ ሲናገር ህግ ዝም ይላል›› ይባላል ከነተረቱ ስለዚህ ዋስትና ይፈቀድልህና ቃሊቲ
ሳትወርድ ከውጪ ሆንሀ ክስህን ትከታተላለህ ፡፡ የኔ ብጤው ምስኪን ይህን እድል በጆሮው ከመስማት በቀር ሆኖለት
አያቅም ቃሊቲ መውረድ ግድ ነው፡፡
ቃሊቲ ማረምያ ቤት /የፈዴራል መንግስት እስር ቤት/
የሚገኘው ቃሊቲ ነው ፡፡ በሰፊ መሬት ላይ የተሰራ ሲሆን አሁን ያለው መመንግስት ነው የሰራው ፡፡ ደፋር እስረኛ ካለ አጥሩ
አያሳስብም ህብረት ካለ እስር ቤቱ ለማምለጥ ቀላል ነው ፡፡ ግን ህብረት የለም አንድነት በዘፈን ካልሆነ አይታወቅም አንዱ
አንዱን ይፈራል ፡፡እንዴት አንፈራራ ? በስንት ዱላ እና ቶርች ከግዚያዊ እስር ቤት ወደዚህ የመጣ ምስኪን ታሳሪ ባይፈራ
አይገርምም ፡፡
ቃሊቲ ብዙ ዞኖች አሉት ዝሆን ስል እንስሳውን እንዳይመስልህ ቀጠናዎች /ግቢዎች /አሉት በአንዱ ቃሊቲ ውስጥ ሌላ
ስድስት ወይ ሰባት ግቢዎች አሉት እያልኩህ ነው፡፡ አንደኛው ጊቢ የሴቶች ክልል የሚባለው ሲሆን የተቀሩት የዎንዶች ነው
እኔ ከቃሊቲ ልለቅ አካባቢ ሌላም ዞኖዎች ሳይጨመር አይቀርም ፡፡ትንንሽ ግቢዎችም እንዳሉት ሰምቼያለሁ፡፡በአንድ ቀን
ግቢውን ዞረህ አጨርሰውም፡፡
ከሀ፤ከለ፤ከሐ ጊዛዊ እስር ቤቶች ወደ ቃሊቲ በመኪና ትወሰዳለህ ግቢው ጋ ስትደርስ አጥሩ የሽቦ ሆኖ በሩ በትልቅ ግንብ
የተሰራ ነው በትላቅ አርማም ቃሊቲ ማረምያ ቤት የሚል ከበሩ ላይ ተሰቀሏል ፡፡ እንደገባህ ከመኪና እየሰደቡና እየገላመጡ
ትወርዳለህ ስትወርድ ደሳሳ ቢሮዎች ትልልቅ እንጨት የያዙ ቦታዎች ታያለህ ይህ በስተቀኝ እና ፊት ለፊት ያለ ሲሆን
በስተግራ ያንበሳ አጥር የመሰለ በሽቦ አጥር የተከለለ ቦታ ታያለህ አይዞህ እዚህ ውስጥ አትታሰርም ይሄ የታጠረ ቦታ
በቀጠሮህ ቀን ፍርድቤት ልትሄድ ስትል የምትሰበሰብበት ቦታ ነው፡፡ተቆጥረኽ ከዚህ ቦታ መኪና ላይ ተጭነህ ፍርድቤት ትሄዳለህ ስትመለስም ከዚሁ ቦታ ተቆጥረኽ ትገባለህ ፡፡በዚህ ለአይን በሚያደክም ግቢ ውስጥ ት/ቤቶች ፤ትንሽ ክሊኒክ፤የምግብ ማብሰያ ቤቶች ፤ ወርክ ሾፖች አሉ፡፡ከመኪናው እንደወረድክ እቃህን አሲዘው አሰልፈው በየተራ በስተቀኝ ካለ
ቢሮአቸው /ቆርቆሮ በቆርቆሮ/ ውስጥ ትገባለህ አንድ ከማርጀት አልፈው የሻገቱ ሰውዬ ከውስጥ ይጠብቁሀል እንደቆምክ
ስምህን ይጠይቁሀል ለመፃፍ ስለሚቸግራቸው ስምህን ደጋግመህ መናገር ግድ ነው፡፡ ታጋይ ስለሆኑ መሰለኝ ጡረታ
ያልወጡት፡፡ በተለይ ለመፃፍ አስቸጋሪ ስም ካለህ ትሰደባለህ ከዛም በድሮ ካሜራ የእውነት ይሁን የውሸት አላቅም ፎቶ
ያነሱሀል፡፡እዚህ ቢሮ ውስጥ የመጨረሻው ነገር ሎሚ የሚያክል መዳኒት መዋጥ ነው፡፡ እንዳትኮረሽም ይሉሀል ያን ትልቅ
መድሀኒት መዋጥ ግደታ ነው፡፡ባረጀ ጣሳ ውሀ ያቀብሉሀል እየዘገነነህ መዳኒቱ ከጉሮሮህ እንዲወርድለህ ስትል በዛ አስቀያሚ
ጣሳ ውሀውን ትጠጣለህ፡፡ በፖሊሶች እየተመራህ ወደ ዞን ሶስት ትሄዳለህ ፡፡ ይህ ዞን ማንኛውም እስረኛ ቃሊቲ ሲወርድ
በመጀመርያ ያርፍበታል፡፡እዚህ ካላረፈ ግን አንድ ነገር አለ ማለት ነው ፡፡ምን አልከኝ ምን መሰለህ ከመንግስት ጋር ንክኪ
ኖሮታል ለብቻው መታሰር አለበት አለበለዚያም ሚድያ ያናፈሰው እና ህዝብ የሚያወቀው ከሆነ ለብቻው ይታሰራል ከነዚህ
ውጪ ግን ገንዘብ ያላቸው ሰዎችና ዞን ሶስትን ጠንቅቀው የሚያቁ ሰዎች ለመዳቢው ፖሊስ ጠጋ ብሎ በጆሮው አንድ ነገር
ይነግረዋል ፡፡አንተ ጠጋ ብለህ በጆሮው ያልነገርከውን ምስኪኑን እየነዳ ካሉት ሰባት ዞኖች መሀል ዞን ሶስት ይከትሀል፡፡
ካለነሱ ፍቃድ ሌለውን ዞን ምን እንደሚመስል አታይም፡፡ማየትም የተከለከለ ነው፡፡ግራውንድ ስርም የሚታሰሩ አደገኛ
እስረኞች አሉ፡፡
ዞን ሶስት /ግቢ ሶስት/
በዚህ ዞን ውስጥ አምስት ትልልቅ ቤቶች ይገኛሉ አንድ ቁጥር ቤት፤ሁለት ቁጥር ፤ሶስት ቁጥር፤አራት ቁጥር፤ አምስት ቁጥር
፡፡ የተሰሩት ቆርቆሮ በቆርቆሮ ሲሆኑ አንደኛው ቤት ካንደኛው በቆርቆሮ ግድግዳ ይያያዛሉ ፡፡ አዲስ እስረኛ ቀጥታ አንደኛ
ክፍል ይገባል ወደሌላ ክፍል ወይም ዞን የምትዘዋወረው ከአንድ ሳምንት በኃላ ነው ፡፡ይህ ቁጥር አንድ ክፍል ከሌሎቹ
ክፍሎች ጠባብ ነው ለራስህ ካልሳሳህ እዚህ ክፍል ውስጥ ላለመኖር እራስህን ታጠፋለህ ፡፡በዞን ሶስት የሚገኙ ሌሎች
ክፍሎች እያንዳንዱ ክፍል ስፋት /40 በ 20/ ያክል ሲሆን እነዚህ ቤቶች ሻወር እና ሽንት ቤታቸው ከቤት ውስጥ ነው
የሚገኘው ፡፡በያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ከ 200-350 እስረኛ ይኖርባቸዋል ደልቶህ እንደማትኖር እርግጠኛ ነኝ፡፡ጥቂት
ተደራራቢ አልጋዎች በየክፍሉ ሲኖሩ መሬት ላይ የሚተኙት ይበልጣሉ፡፡ገንዘብ ካለ ችግር የለውም አንድ አልጋ እስከ
1000ብር ልትገዛ ትችላለህ፡፡የምትገዛው አልጋ በወረፋ ከደረሰው ሰው ነው፡፡በድብቅ ይሰራል ቢባልም አንዳንድ ፖሊሶች
ተሳታፊ መሆናቸውን ታያለህ፡፡ይሄን ያህል ብር የሌለው እስረኛ ደቦቃ መተኛት ይጠበቅበታል፡፡
ደቦቃ ማለት ቦታ ለማብቃቃት የሚተኛ መኝታ ሲሆን የአንዱ እግር ሌላው ፊት ላይ ያደርገዋል የዛኛው ሰው እግር
እዚህኛው ፊት ላይ ይሆናል አስቀያሚ መኝታ የማትገላበጥበትና ለሽንትህ የማትነሳበት ለሊትን ትጋፈጣለህ፡፡ቆርቆሮ
በቆርቆሮው የሆነው ቤት ይግላል ያዣል፡፡አልጋ ላይ ያለው ቁልቁል ወደታች ይሄን ትይንት እያየ ያዝናል፡፡ ፍራሽ ወደ
ቃሊቲ ስትወርድ ይዘህ ካሌድክ ባዶ መሬት ላይ ትተኛለህ፡፡ቃሊቲ እንደገባህ ኪኒን እንጂ ፍራሽና ብርድልብስ አይሰጥህም፡፡
እዚህ ዞን ውስጥ አንድ ትንሽ ካፌ ፤ሁለት ፀጉር ቤቶች፤አንድ ህግ ማማከርያ ቢሮ፤በጣም ትንሽ ላይብረሪ ገፅ ከሌላቸው
መፅሀፍት ጋር፤ሶስት ከረንቡላዎች፤በጣም ትንሽ የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስትያን በጣም ትንሽ ባዶ መሬት ኳስም እጅ ኳስም
የሚጫወቱበት ቦታ ፤የእንጨት ስራ የሚሰሩበት ትንሽ ቤት፤ በጣም የሚያስቅ ጉሊት፤ ሲጋራና ሀሺሽ በድብቅ የሚሸጡ
ሰዎች፤ እብዶች፤ሊያብዱ የተዘጋቹ ሰዎች፤አዋቂዎች ፤ ኢ-አዋቂዎች ብቻ የሰው አይነት ይገኛል ፡፡ሁሉም ዞን ላይ ይሄ
እንደሚኖር ገምት፡፡
ኮሚቴዎች ከስረኞች ይመለመላሉ በየክፍሉም አሉ
የምግብ ኮሚቴ /ምግብ ከተሰራበት ቦታ አምጥተው የሚያድሉ /
የጤና ኮሚቴ /የተማመሙትን መዝግበው ነጭ ጋዎን ለሚያደርጉ ሀኪም ተብዬዎች የሚወስዱ/ የፅዳት ኮሚቴ /የቤቱን ፅዳትን በተመለከተ የሚቆጣጠር ሲሆን ሁሉም እስረኛ በየወሩ አንድ አንድ ብር ያዋጣና የቤቱንውበት ለመጠበቅኦሞ ሳሙና ሌሎች ነገሮችንም ይገዛሉ /
የመኝታ ኮሚቴ /እስረኛው እንዲተኛ ቦታ የሚሰጡ ባይተኛም ለቂጡ ቦታ እንዲያገኝ የሚያረጉ/
የስፖርትና መዝኛኛ ኮሚቴ /በቤት ውስጥ ያለውን ቴሌብዥን እንደየቤቱ ስፋት ይለያያል አንዳንዱ ቤት ሁከት ተቪ ሊኖር
ይችላል ይሄን ተቪ የሚቆጣጠሩ የሚከፍቱ የሚዘጉ ናቸው ለሊቱን ሙሉ ፊልም ይታያል/
ሶስት የቤቱ አስተዳደሮች /ጠቅላላ የቤቱን ሁኔታዎች የሚቆጣጠሩ ሲሆኑ እንደገባህ ማስጠንቀቅያ ይሰጡሀል ከዛም ፎቶህየሌለው መታወቅያ ይሰጡሀል / በጥቂቱ ኮሚቴዎች እነዚህ ናቸው
ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.